የዘንድሮው የብሔራዊ ስፔሻሊስት ፈተና ቅሬታ አስነሳ

ከ20 በላይ ጥያቄዎች ቀድመው ወጥተዋል

ታህሳስ 26/2013 ለጠቅላላ ሐኪሞች የተሰጠው የብሔራዊ ስፔሻሊስት ፈተና ዘርፈ ብዙ ችግር አለበት ሲል የኢትዮጵያ ጤና ሙያ ተማሪዎች ማህበር (ኢጤሙተማ) ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ጤና ሚኒስትር በየዓመቱ ከ 1 ሺሕ ለሚበልጡ ሐኪሞች ብሔራዊ የስፔሻሊስት ፈተና በመስጠት ለከፍተኛ የሕክምና ትምህርት ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲዎች በመላክ እንደሚያስተምር የሚታወቅ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት በተሰጠው የብሔራዊ ስፔሻሊስት ፈተና ላይ ግን በርካታ ተፈታኝ ተማሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ጤና ሙያ ተማሪዎች ማህበር (ኢጤሙተማ) ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲሳይ አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዶክተሩ የተፈታኝ ተማሪ ሐኪሞችን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ለማጣራት እንደሞከርነው ከ20 በላይ ጥያዎቄች ቀድመው እንደወጡ ለማወቅ ችለናል ብለዋል። ፈተናው ከመሰጠቱ ከአንድ ቀን በፊት ቴሌግራም በተሰኘ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የኢትዮጵያ ሐኪሞች ሕብረት በሚል ሥም በተከፈተ የቴሌግራም ገጽ ላይ ቀድመው ወጥተዋል የተባሉ ከ20 የሚበልጡ ጥያቄዎች ተለጥፈው ተገኝተዋል ሲሉ ዶክተር ሲሳይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመልስ መስጫ ወረቀት ላይ ያሉ መለያ ቁጥሮች ላይም የተፈጠረ ችግር እንዳለም ቅሬታች ደርሰውናል እያጣራንም እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል። ለጤና ሚኒስትር ጥያቄያችንን አቅርበን እየተጠባበቅን እንገኛለን ሲሉም ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ለስፔሻሊቲ የሕክምና ትምህርት ፈተና በአማኝ 200 ያህል ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ እና ዋና ከሆኑ የሕክምና የትምህርት ዓይነቶች በርከት ያሉ ጥያቄዎች እንደሚዎጡ እንዲሁም ከንዑስ የትምህርት ዓይነቶች ደግሞ የተወሰኑ ጥያቄዎችን እንደሚያካትት አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ጤና ሙያ ተማሪዎች ማህበር (ኢጤሙተማ) ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲሳይ አክለውም ከሐኪሞች ቅጥር ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ሕክምና ያጠኑ ተማሪዎች ተመርቀው ያለ ሥራ እንደተቀመጡ ተናግረዋል። ለዚህ እንደምሳሌ ባለፈው የአማራ ክልል ለ20 ሐኪሞች ባወጣው የስድስት ወር የኮንትራት የቅጥር 322 ያህል ሐኪሞች ተመዝግበው ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።የጤና ሚኒስትር ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ጋር በመሆን ለተጨማሪ ትምህርት ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የሚላኩ ጠቅላላ ሐኪሞችን ደምወዝ እየከፈለ በምትካቸው የክልል ሆስፒታሎች ሐኪም የሚቀጥሩበትን አሰራር ከሦስት ዓመት በፊት እንደዘረጋ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። አሁንም ድረስ ግን ይህ አሰራር መሬት የወረደ ነው ለማለት ያስቸግራል ሲሉ ዶክትር ሲሳይ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንደ ማሕበር በአዲስ አበባ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በርካታ ሥራ የሌላቸው ሐኪሞች አሉ እነዚህ ሐኪሞች እየሠሩ ሞያቸውን ካላዳበሩ የተማሩት ትምህርት ይጠፋባቸዋል ሲሉ ሞያዊ አስተያየታቸውን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ የብሔራዊ ስፔሻሊስት ፈተና የወሰዱ ጠቅላላ ሐኪሞችን ባነጋገረችበት ወቅት ፈተናው ሰኞ ታህሳስ 26 ከመሰጠቱ በፊት እሁድ ታህሳስ 25 ቴሌግራም በተሰኘው የማሕበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ላይ መውጣቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳገኙ ገልጸዋል። አስተያየታቸውን የሰጡት ጠቅላላ ሐኪሞች ምናልባት በዚህ ዓመት ፈተናውን አልፈው የስፔሻሊቲ ትምህርታቸውን ካልጀመሩ ከእድሜያቸው አንድ ዓመት እንደሚቃጠልባቸው ነው የገለጹት።

የጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት አለምፀሀይ ጳውሎስ የስፔሻሊቲ የሕክምና ትምህርት ፈተና ተፈታኞች ያነሷቸውን ቅሬታዎች በኢሜል በአካል እንዲሁም በኢትዮጵያ ሐኪሞች ማሕበር በኩል እንደደረሳቸው ገልጸው ይህንን ጉዳይ የሚያጣራ ቡድን አዋቅረው እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሚኒስቴር ዴኤታዋ አክለውም ከአንድ ሳምንት ጊዜ በኋላ ቅሬታውን የሚያጠናው ቡድን ሥራውን አጠናቆ ውጤቱን እንደሚያሳውቃቸው ተናግረው የተነሱት ጥያቄዎች አግባብ የሆነ ምላሽ ተሰጥቶባቸው ተፈታኞቹ ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ እናደርጋለን ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here