በጎንደር ለሚከበረው የጥምቀት በዓል 500 ሺሕ እንግዶች ይጠበቃሉ

0
496

በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የሚከበረውን የከተራ በዓል እና ጥር 11 የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ለማክበር ከ 500 ሺሕ በላይ እንግዶች ጎንደር ከተማ በመገኘት ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በዓሉን ለመታደም ከአጎራባች ቦታዎች ከሰሜን ከደቡብ እንዲሁም ከምዕራብ ጎንደር 300 ሺሕ ያህል እንግዶች እንደሚመጡ እና ቀሪዎቹ 200 ሺሕ ያህሉ ከሌሎች የአገራችን ክልሎች እንዲሁም ከውጭ አገር የሚመጡ ጎብኝዎች ናቸው ሲሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ቻላቸው ዳኘው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከጥር ስድስት ቀን እስከ ጥር ዘጠኝ የኪነ ጥበብ የባህል ሳምንት እየተከበረ እንደሚገኝ አስታውቀው ጥር ስድስት የአጼ ቴዎድሮስን 202 ተኛ ዓመት የልደት በዓል በማክበር የኪነ ጥበብ የባህል ዝግጅቱ እንደተጀመረ እና ለኪነ ጥበብ ዝግጅቱ የወልቃይት ጠገዴ የባህል ቡድን ጎንደር ከተማ ከ 30 ዓመት በኋላ ተገኝቶ ዝግጅቱን አቅርቧል። የአካባቢው ነዋሪም ከ 30 ዓመታት በኋላ ጥምቀትን አብሮን ለማክበር ችሏል በማለት ኃላፊው አሳውቀዋል።

ጎንደር ከተማ የሚገኙ አቢያተ መንግሥታትን ለሚጎበኙ ቱሪስቶች በቀደምት ነገሥታት ሲከወኑ የነበሩ ተግባራትን በቃል እየነገሩ ከማስረዳት ይልቅ በተግበር ለማሳየት ዝግጅቶች ማጠናቀቃቸውንም አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። እንደ ምሳሌ የፈረስ ማደሪያ የነበሩ ቦታች ውስጥ ፈረሶችን በማሰር እና ለጎብኝዎች ለማሳየት እንደታቀደ እንዲሁም ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓልን ከተከበረ በኋላ የተዘጋጀ “የንጉሥ እራት” የተሰኘ የእራት ግብዣ በአጼ ፋሲል ቤተ መንግሥት የዕልፍኝ አዳራሽ እንደሚደረግ እና ከአለባበስ ጀምሮ የነበረውን ሥርዓት የሚያስታውስ ኹነት እንደሚኖር አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

ጥምቀት ከሐይማኖታዊ ዳራው በተጨማሪ የነፃነት በዓል ነው ለዚህ እንደማሳያ ከብት የሚጠብቁ ልጆችም ሆነ በሰው ቤት በሠራተኝነት የሚያገለግሉ እህቶች በነፃነት ከቤት ወጥተው የሚያከብሩት ጥምቀትን ብቻ ነው ብሎ ለመናገር ያስደፍራል ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

ከጸጥታ ጋር በተያያዘም ከጥር ስድስት ቀን ጀምሮ ህገ-ወጥም ይሁን ህጋዊ የጦር መሳሪያ በከተማዋ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይፈቀድ ገልጸው ያለ ፀጥታ አካለት በከተማዋ የጦር መሳሪያ ይዞ የሚቀሳቀስ ሰው ከተገኘ እንደሚጠየቅም ተናግረው ለእንግዶች ደህንነት ልዩ ጥበቃ ይደረጋል ብለዋል። እንግዶች ወደ ከተማዋ ሲገቡ ጀምሮ እስከ ማረፊያ ሆቴላቸው ድረስ ልዩ የፀጥታ ኃይል ተመድቦ ጥበቃ እንደሚደረግላቸውም ጠቁመዋል። አያይዘውም ወደ ጎንደር ከተማ የሚያስገቡ በሮች ላይ ጥበቃ እና ፍተሻ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ባለፈው ዓመት የጥምቀት በዓል ሲከበር በተፈጠረ የእንጨት ርብራብ መደርመስ ሳቢያ የደረሰውን የሰው ሕይወት መጥፋት እና የአካል ጉዳት አስታሰው በዘንድሮው በዓል ላይ 200 እንግዶች ብቻ የሚቀመጡበት ከብረት የተሠራ ርብራብ ተዘገጅቷል ብለዋል። ጥምቀተ ባህሩ ወደሚከበርበት ሥፍራ ሁሉም ሰው ገብቶ ፀበል መረጨት ስለማይችል እንዲሁም የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለማስቀረት ፓምፖችን በማዘጋጀት ሁሉም ምዕመን ፀበል መረጨት እንዲችል ማድረጋቸውን አሳውቀዋል። ትላልቅ እስክሪኖችን በመትከል እና ከበዐሉ ማክበሪያ ውስጥ ስቱዲዮ በመገንባት ታዳሚው ከውጭ ሆኖ ሥነስርዓቱን መመልከት ይችላል ብለዋል።

በአገራችን የጥምቀት በዓል መከበር የተጀመረው በአጼ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጥምቀት በዓል ከሐይማኖታዊ አንድምታው በተጨማሪ በርካታ የውጭ ጎብኝዎችን በመሳብ ይታወቃል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በሆነው(UNSCO) በአገራችን ከሚከወኑ ሕዝባዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አከባበር፣ከገዳ ሥርዓት እና ከፍቼ ጫምባላላ በማስቀጠል አራተኛው የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here