የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የራሱንና የተጠሪ ተቋማቱን በአንድ ቦታ ለማሰባሰብ የሚያስችል የጋራ ሕንጻ መገንቢያ ኹለት ሄክታር መሬት ከጉለሌ ክፍለ ከተማ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ሰኞ ጥር 10 2013 መረከቡ ታወቀ ።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ሥራ አመራር ዳይሬክተር ደሳለኝ ሳሙኤል ከጉለሌ ክፍለ ከተማ በተረከቡት ኹለት ሄክታር መሬት የይዞታ ማረጋገጫ ካገኘን በኋላ ግንባታ ከመጀመራችን በፊት አፈሩ በባለሙያ ተመርምሮ እና መሸከም የሚችለው የሕንጻ አይነት በሕንጻ ዲዛይን ባለሙያዎች ተጠንቶ እና የሕንጻ ዲዛይን አወዳድረን መገንባት እንጀምራለን ብለዋል።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ሳሙዔል ሁርቃቶ(ዶ/ር) ቦታን በተረከቡበት ወቅት ከቢሮ ኪራይ ጋር በተያያዘ ይወጣ የነበረውን ወጪ በማስቀረት፣ቋሚ የሆነ እና ሁሉንም በአንድ ያሰባሰበ የጋራ ተቋም በመገንባት አካባቢውን የምርምርና የቱሪስት መስህብ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኝውን ጥቅም ለማሳደግ ዛሬ የተደረገው የቦታ ርክክብ ወሳኝ ምዕራፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባወይ ዮሐንስ በበኩላቸው ለትምህርት ሴክተሩ በተለይም ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት በክፍለ ከተማው ቦታ በመሰጠቱ እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ማዕከል በክፍለ ከተማቸው የሚገነባ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በቀጣይም ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በስሩ በአገሪቱ የሚገኙ 51 የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እና ከ260 የሚበልጡ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንደሚያስተዳድር የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ሥራ አመራር ዳይሬክተር ደሳለኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በትምሕርት ሚኒስትር ስር ሲተዳደር ቆይቶ በ 2011 ራሱን ችሎ በተቋም ደረጃ መመስረቱ የሚታወስ ነው።
ሚኒስቴሩ የኮቪድ ወረርሽኝ በአገር ውስጥ ከተከሰተ ጀምሮ የመማር ማስተማር ሒደቱ መቋረጡን ተከትሎ አብዛኞቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለኮቪድ 19 መከላከያ የሚውል ሳኒታይዘር እና ሳሙና እንዲሁም አልኮል እንዲያመርቱ ዕገዛ ሲያደርግ መቆየቱም ይታወሳል። በቅርቡ ደግሞ በፌደራል መንግስት በተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ጋር ተያይዞ በትግራይ የሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ የትምሀርት ተቋማት ወደ ነባራዊ ሁኔታቸው እስኪመለሱ ድረስ ተማሪዎቻቸው ወደ ሌላ ዩኒቨርስቲዎች ተዘዋውረው እንዲማሩም መወሰኑ ታውቋል። በዚህም ረገድ የአዲግራት ዩንቨርስቲ የ2012 ተመራቂ ተማሪዎች በመቀሌ ካምፓሶች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔውን ማስተላለፉም ይታወሳል።
ይህም ደግሞ በሕግ ማስከበሩ ወቅት በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ጉዳት ከመድረሱ ጋር ተያይዞ ተማሪዎችን ማስተናገድ ባለመቻሉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መነቃቃቶች እና በከፍተኛ ትምህርት ዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት እየተጋ የሚገኘው ሚኒስቴሩ በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን በሳይነስ እና ቴክኖሎጂው ዘርፍም እየተገበረ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል። ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ጋር በመሆን አመርቂ ስራዎችን ለመስራትም ሚኒስቴሩ ስራ መጀመሩ ታውቋል። በዚህም መሰረት በቅርቡ ከማእድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር እና አዲስ አበባ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መካከል አብሮ ለማስራት ስምምነት ላይ የተደረሰው አንደኛው ኹነት ነው። ‘የኢትዮጵያ የማዕድን ልማት ማዕከል’ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢንጂነሪንግ ትምህርት ቤት መቋቋሙን የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን ማዕከሉ ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር ተደጋግፎ ለ10 ዓመታት የሚተገበር ይሆናል ተብሏል።
ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013



