ከሕዝብ የሚደበቁ ጉዳዮች መጠናቸው ይለያይ እንደሆነ እንጂ በየትኛውም የመንግሥት ስርዓት ላይ መከሰታቸው ግልጽ ነው፤ የሚጠበቅም ነው። ይሁን እንጂ በአንዳንድ መንግሥታት ላይ ደግሞ በእርግጥም ከሕዝብ የሚደበቁት ጉዳዮች ብዛት ምናልባትም ሕዝቡ በመንግስት በኩል ምን እየተደረገ እንዳለ እስካለማወቅ ድረስ የሚዘልቅም ድብቅነት ይስተዋላል። ሕዝብን ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምንም ሲሉ የማይደመጡት መንግስታትም ይህን ተከትሎ ለሚከሰተው የተዛባ መረጃ እና ሕዝቡ ዘንድ ለሚደርሱት መረጃዎች ችግሬ ምንድነው ሲሉም አይታይም።
በተለያዩ ጊዜያት ከመንግሥታት ድብቅነት እና ይህንንም ምክንያት በማድረግ በተዛቡ መረጃዎች ወደ ሕዝብ መድረስ ከፍተኛ ቀውስ በአገራት ውስጥ መፍጠራቸው ትልቁ እና ዋነኛው አጋጣሚም እንደሚሆንም ይታወቃል።
በኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ የመጀመሪያ ወራቶች ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሕዝብ ብቅ ብለው በሰጡት ንግግር በመንግስት በኩል የስለጣን ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ደብቆ የሚሰራ ምንም አይነት ጉዳይ እንደማይኖር እና ሁሉም ነገር ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ቃል ገቡበት አጋጣሚ የሚረሳ አይደለም። እንዲያውም ከዚህ ጋር አያይዘው ጠቅላይ ሚንስትሩ ሲናገሩ በየጊዜው የሚካሔደው የፓርቲ ስብሰባዎች እና ሚተላለፉት ውሳኔዎች በቀጥታ ለሕዝብ የሚተላለፉ እንደሆኑም ቃል ኪዳናቸውን አስፍረው ነበር። ነገር ግን እየሆነ ያለው ጉዳይ እና እስካሁንም ሲሆኑ የታዘብናቸው ከዚህ በተቃራኒው ሆኖ ውሳኔዎች ሲተላለፉ ምስማቸው በድንገቴ አቀባበል ነበር።
በቅርቡ ኢትዮጵያ በሰሜኑ በኩል የሕግ ማስከበር እርምጃዎችን በተመለከተ በርካታ ኹነቶች እንደተከሰቱባት የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህንንም ተከትሎ በትግራይ ክልል የተቋረጡ ግንኙነቶች ተመልሰው በከፊል እስኪስተካከሉ ድረስ ከአሉባልታ እና መንግስት በቁጥብነት ከሚሰጣቸው መግለጫዎች በላፈ ሕዝብ የሚውቀው ምንም አይነት መረጃ አልነበረውም። በተለይ ደግሞ በአሉባልታ በኩል የሚነዙት እና የሚሰራጩት መረጃዎች ሕዝብ እና መንግስት መሐል ያለውን ግንኙነት በትልቁ እንዲላላ የሚደርግ እንደሆነም እና እንደነበርም ለመታዘብ ተቻለ ጉዳይ ነው። የፌደራል መንግስት በይፋ የሕግ ማስከበሩ ሒደት ከጊዜያት በፊት መጠናቀቁን አስመልክቶ መናገሩም ይታወሳል። ይሁን እንጂ ግንኙነቶች ካለመመለሳቸው ጋር ተያይዞ እና በከፊል የተመለሰባቸው አካባቢዎችም በሚመጡ መረጃዎች መሐል አገር እና ከአገር ውጭ ያለው ዜጋ የሚደርሰው ተለያየ አይነት መረጃ ለውዝግብ ዳርጎታል።
ይህ ደግሞ ሕዝብ በአገር ውስጥ እየተደረገ ያለውን ጉዳይ የማወቅ መብቱን የሚነፍግ ነው። ከሕግ ማስከበሩ ጋር በተያያዘ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸው ሲገለጽ እንደነበር እና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በአንዳንድ አካላት በአካባው ያለውን የከፋ ችግር እየተሰራጨ ይገኛል። ረሐብ፣ ቸነፈር፣ እና የክፉ ገጠመኞች ሁሉ መደራረብ በክልሉ መከሰቱን እየተናፈሰ የሚገኘው መረጃ ያመላክታሉ። ይሁን እንጂ በአንጻሩ ደግሞ የአደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በኢትዮጵያ ከ1977 በኋላ ረሐብ እንዳልነበር በግልጽ መናገራቸው ተነግሯል።
የተመድ የዓለም ምግብ መርሃግብር እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ የረሃብ አደጋ ተደቅኗል ብለዋል። የውጭ ሀገር ሚዲያዎች የዓለም ምግብ ድርጅትና የውጭ እርዳታ ድርጅቶችን ጠቅሰው በትግራይ ክልል የረሃብ አደጋው በህፃናት ላይ የጠና ነው ሲሉ አስነብበዋል።
በብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የኮሚኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ደበበ ዘውዴ ፥ “የምግብ እህሎች በትግራይ ሆነ በቤኒሻንጉል አካባቢ ለተፈናቃዮች እየደረሰ በመሆኑ በአሁን ሰዓት ‘ረሃብ’ እየተባለ የሚነገረውም ሆነ ተርቧል የሚባል ሰው የለም” ብለዋል። ከማንም በላይና በፊት በኢትዮጵያ ላለ ሰው ሰራሽ እንዲሁም የተፈጥሮአዊ አደጋ የኢትዮጵያ መንግስት ነው ለዜጎቹ የሚጨነቅ ሲሉም ተናግረዋል።
ከ2008 ጀምሮ ከፍተኛ የድርቅ አደጋዎች እንዲሁም ሰው ሰራሻ አደጋዎች ሲደርሱ ነበር ከማንም ቀድሞ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት ነው ብለዋል። መንግስት ያለውን ችግር የሚደብቅበት ነገር እንደሌለው እና ለችግሮች በአስቸኳይ እንደሚደርስ ገልፀዋል። በአሁን ሰዓት በትግራይ ክልል 485 ሺህ ተፈናቃዮች አሉ ያሉ ሲሆን የምግብ እርዳታ መንግስት በየወሩ እያቀረበ መሆኑን ተግረዋል።
ጥር 3/2013 ላይም ስንዴ፣የስንዴ ዱቄት፣ ዘይት፣ፓስታ፣ሩዝ፣ መኮሮሪ በድምሩ 80,480 ኩንታል ድጋፍ መላኩን ገልፀዋል። በተጨማሪ ህፃናት እና አጥቢ እናቶች ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ በማሰብ 438 ካርቶን የዱቄት ወተት፣ 214 ካርቶን ብስኩት ልከናል ብለዋል። እነዚህ ኹለት ተራራቁ ጉዳች ባሉበት መንግስት ከሚዲያ የራቀው እና ከፓርቲ እና ከመንግስት የዜና አውታሮች በላቀ ለግል የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ክፍት በማድረግ ችግሩ ወደ ሕዝብ እንዲቀርብ እና ትክክለኛውን ነገር ሕዝብ አይቶ እንዲፈርድ አዲስ ማለዳ አጥበቃ ትሻለች። ከምንም አይነት ተጽዕኖ በአንጻሩ ነጻ ናቸው የሚባሉ የመገናኛ ብዙኃን በስፍራው ሄደው ለመዘገብ መንግስት የጸጥታ እና የሁኔታዎችን እንዲያመቻችም በጽኑ ታሳስባለች።
ከለውጡ በፊት የነበሩትን የፕሮፖጋንዳ እና ሕዝብን የመሸወድ አካሔዶችን ሕዝብ አሁንም ከልቡ ስላላወጣቸው በመንግስት ላይ ሚኖረው አመኔታን በሚገባ ለመገንባት ከመንግስት በኩል የሚዲያ የራቁ ጉዳዮች ግልጽ ሆነው ወደ ሚዲያ እንዲቀርቡ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በእርግጥ በትግራይ ብቻም ሳይሆን መንግስት በየጊዜ እየሰራሁ ነው የሚለው ዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ላይም ግችቶች ተነስተውባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ላይ መንግስት የሚዲያ አካላትን በመጋበዝ የተሰሩትን ስራዎች ከስፍራው ከነዋሪዎች በመታዘብ የመገናኛ ብዙኃን የዜና ሽፋን እንዲሰሩ ማድረግም ይኖርበታል። ከላይ ያነሳነው የትግራይ ክልልን ብቻም ሳይሆን በመተከል፣ በኮንሶ፣ በጉራፈርዳ፣ በወለጋ እና በሌሎ ስፍራዎች ያሉትን የአገሪቱን ነባራዊ ጉዳይ ነጻነእና ገለልተኛ የተባሉ ሚዲያዎች በማቅናት ዘገባ እንዲሰሩ መንግስት ነገሮችን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል።
ከፌደራል መንግስት ወደ ተጎጂዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚላከው እርዳታም በተገቢው መንገድ ለታሰበላቸው እና በትክክል ለሚገባቸው ሰዎች መድረሱን እና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች የተያዙበትን አያያዝ በተመለከተም ሕዝብ ጉዳዮን ማወቅ ይኖርበታል።አንደኛ ከሚሰራጩት ውዥንብሮች ይነጻል በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስትም ላይ ሚኖረው አመኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። የስልጣን ባለቤት ነው የሚባለው ሕዝብ መንግስት በትክክል ምን እያደረገ እደሆነ ካላወቀ እና እንዲያውቅ ካልተደረገ ስልጣኑ መነፈግ ብቻ ሳይሆን የመረጃ ማግኘት መብቱም ነው አብሮ የሚነፈገው። በመሆኑን መንግሥት ከሚዲያ ማለትም በተዘዋዋሪ ከሕዝብ የተሰወሩ አገራዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች በአስቸኳይ ወደ ሕዝብ አይን እና ጆሮ ሊደርሱ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታሳስባለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013


