ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት እና የእንስሳት አካላት ዝውውርን ለመከላከል ያስችል ዘንድ አራት አነፍናፊ ውሾች ወደ አገር እንደሚገቡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የሚገዙት አነፍናፊ ውሾችም ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ታምኖበት እንደሆነም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን ህግ ማስከበር ባለሙያ ዳንኤል ፓውሎስ እንደተናገሩት በዱር እንስሳት ሀብት ላይ ያለ ዋነኛ ችግር የሕገ-ወጥ ዱር እንስሳት እና እንስሳቱ አካላት ዝውውር መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታት አነፍናፊ ውሾችን የማምጣቱ ስራ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው እንዲሁም በአነፍናፊ ውሾች የማስፈተሸ ስራ ከሌሎች አገራት የተወሰደ ተሞክሮ እንደሆነ እና ለአብነትም ኬኒያ ፣ ኡጋንዳ ፣ ታንዛኒያ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ አነፍናፊ ውሾችን በአለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያዎቻቸው ላይ በመጠቀም በሕገ-ወጥ ዱር እንስሳት ዝውውር ዙሪያ ከፍተኛ ለውጥ ካመጡ አገራት መካከል ናቸው ብለዋል።
አነፍናፊ ውሾቹ መምጣት በአገራችን ያለውን የዱር እንስሳት እና ውጤቶቻቸው ሕገ-ወጥ ዝውውር የተሻለ ቁጥጥር እንዲኖር ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።
በዋናነት እነዚህ የሚገዙት ውሾች ለመግዛት ሆነ ከተገዙ በኋላ የሚያስፈልገው ከፍተኛ ገንዘብ እንደሆነ የጠቁሙት ዳንኤል መቀመጫውን ኬኒያ ያደረገው (African wild life foundation) ከተሰኘ ድርጅት ሙሉ ለሙሉ በገንዘብም ሆነ በስልጠና የሚሰራውን ስራ እንደሚሰራው ተናግረዋል።
በዚህም ውሾቹን ከመግዛት ፣ ከማሰልጠን ፣ የውሾቹን ተንከካቢ ሰዎች ማሰልጠን ፣ የውሾቹን ምግብ ፣ የትራንስፖር እንዲሁም የውሾቹን መኖሪያ ቤት መስራት ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ወጪውን የሚሸፍነው (African wild life foundation) መሆኑን አስታውቀዋል።
አንድ አነፍናፊ ውሻ ለመግዛት ምናልባትም እስከ 20 እና 25 ሺሕ ዶላር እንደሚያስፈልግ አክለው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በዋናነት በሕገ-ወጥ መልኩ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ እንስሳት መካከል ዝሆን ፣ አቦሸማኔ ፣ ነብር እና አውራሪስ በከፍተኛ መልኩ በዝውውሩ እየተጎዱ ነው ብለዋል።
ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እና በድንበሮች በኩል የዱር እንስሳቱ እንዲሁም ውጤቶቻቸው እንደሚወጡ ተናግረዋል።በዚህም በዋናነት የሚመጡት አነፍናፊ ውሾች በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ያለውን እንደሚቆጣጠሩ አስረድተዋል።
በቦሌ በኩል ከአገር የሚወጣውንም ሆነ ከተለያዩ አገራት መጥተው በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት አልፈው ወደ ተለያዩ አገራት የሚዘዋወረውን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለመቅረፍ አይነተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርቶች ድርጅት ፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር ከአንድ አመት በፊት አነፍናፊ ውሾቹን ለማስገባት የስራ ስምምነት ውል መፈራረሙን አስታውሰዋል።
በዋናነት ውሾቹ የሚኖሩበት ቦታ ነው የሚያስፈልገው በዚህም ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የአንድ እስታዲየም ግማሽ የሚሆን ቦታ እደተሰጣቸው እና በቀጣይ አንድ ወር ከኤርፖርት ቦታውን እንደሚረከቡ በቀጣይም የግንባታ ስራው ከኤርፖርቶች ድርጅት ከተረከቡ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አሳውቀዋል።
በዚህም ውሾቹ ከተገዙ በኋላ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት የተመረጡ ስድስት ሰዎች ታንዛኒያ በ (African wild life foundation) ማሰልጠኛ በመሄድ ስልጠና እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
በኤርፖርት ይጀመር እንጂ በቀጣይ ድንበሮች አካባቢም አነፍናፊ ውሾችን የማምጣት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እንዲሁም በያዝነው በጀት አመት መጨረሻም ሁሉም ስራ ተጠናቆ አነፍናፊ ውሾቹ ወደ ስራ እንደሚገቡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህግ ማስከበር ባለሙያ ዳንኤል ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013



