በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች ከፌደራል ጀምሮ የተላለፈውን መመሪያ በመተግበሩ ረገድ በአንጻራዊነት አመርቂ ስራዎችን ሲሰሩ ለመመልከት ተችሏል
በየዕለቱ ሞት እና ከባባድ የሕመም ደረጃዎችን እንድናስተናግድ እያደረገን የሚገኘው ኮቪድ 19 ወረርሽኙ ከዓመት በላይ በዓለም ላይ ከመቆየቱ ጋር ተዳምሮ በሰዎች ዘንድ መላመድ ሰዎች በወረርሽኙ ላይ የሚያሳዩት ጸባይ እየሆነ ለመምጣቱ በርካታ አካባቢዎችን መታዘብ ይቻላል። አዲስ ማለዳ ከሰሞኑ ወደ ምስራቃዊው ክፍል አፋር ክልል የተለያዩ ከተሞች አቅንታ በነበረበት ጊዜም መታዘብ የቻለችው ይህንኑ ነበር። በአፋር ክልል ርዕሰ ከተማዋ አመራን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ይታይ የነበረው እንቅስቃሴ በሙሉ ከጥንቃቄ ጉድለት ጋር የተያያዘ እና ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረጉ ቅድመ ሁኔታዎች እና ጥንቃቄዎችን ማየት በጣም ከባዱ ጉዳይ ነበር።
በእርግጥ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች ከፌደራል ጀምሮ የተላለፈውን መመሪያ በመተግበሩ ረገድ በአንጻራዊነት አመርቂ ስራዎችን ሲሰሩ ለመመልከት የተቻለበት አጋጣሚ ነበር። ከአዲስ አበባ በእጅጉ ባነሰ መልኩ የሚተገበር ቢሆንም ነገረ ግን አዲስ ማለዳ በተዘዋወረችባቸው የክልሉ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች አንጻር ከፍጸኛ ሚባል አተገባበር ለመታዘብ ተችሏል። ከሎጊያ እስከ ሰመራ፣ ከሰርዶ እስከ ጋላፊ ድረስ የአፍ እና የፊት መሸፈኛን ያደረገ ሰው ካገኛችሁ እርሱ የመንግስት መስሪ ቤት ኃላፊ ነው ወይም ደግሞ በአንድ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ሚሰራ ሙያተኛ ነው ማለት ነው። አሁንም ኮቪድ ተዘንግቶባቸው ያሉ ስፍራዎች ከመዲናችን አዲስ አበባ ውጭ ያሉ አካባቢዎችን እና የክልል ከተሞችን እንደሆነ አዲስ ማለዳ ለመታዘብ የሞከረችው ጉዳይ ነው።
በአፋር ክልል ያለው በኮቪድ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ አዲ ማለዳ በታዘበችው መጠን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የፊት እና የአፍ መሸፈኛ ጭንብልን ከአካባቢው ሞቃታማ የአየር ንብረት ጋር ተያይዞ አብዛኛው ሰው ሲጠቀም አይስተዋልም። የዕጅ ንጽህና መተበቂያ ሳኒታይዘር አዲስ ማለዳ በክልሉ ቆይታዋ ውስጥ ከሰመራ ሱልጣን አሊሚራህ አንፍሬ አውሮፕላን ማረፊያ ውጭ ማየት አልተቻለም። በመዝናኛ ስፍራዎች፣ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና በገበያ ስፍራዎች ላይ የአፍ እና ፊት መሸፈኛ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሰው ጥቂት መሆኑ እንዴት ነው እዚህ አካባቢ ገና የወረርሽኙ ግንዛቤ በስፋት አልተዳረሰ ይሆን እንዴ የሚያስብል ነው። በአፋር ክልል በአብዛኛው ሕዝብ በአርብቶ አደር እና በከፊል አርብቶ አደርነት የማህበራዊ መሰረት ስላለው በእርግጥም ወረርሽኙን በሚመለከት በመንን መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዴት እንደተሰራ ለማወቅ አዲስ ማለዳ ያደረገችው ሙከራ በታሰበው መልኩ ሳይሳካ ቀርቷል። ይሁን እንጂ በየትኛውም የክልሉ አቅጣጫ አዲስ ማለዳ በተንቀሳቀሰችበት ገተር ቀበሌዎች እና ወረዳዎች ላይ የሚታይ የጥንቃቂ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ግን መታዘብ ይቻላል።
ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ ክልሉ ከጎረቤት አገራት ጋር ኢትዮጵያ የምትዋሰንበት እንደመሆኑ መጠን በሕገ ወጥ መንገድ ክልሉን ረግጠው ድንበር የሚሻገሩ እና ከስደትም ሚመለሱበት አካባቢ እደመሆኑ መጠን የወረርሽኙ በስፋት ለመሰራጨት ትልቅ ስፍራ እንደሚሆን ይጠበቃል። ነገር ግን እርምጃው በተለይም ደግሞ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው ጉዳይ ከዚህ በተቃራኒው ያለ ሲሆን እንዲያውም ስለ ኮቪድ 19 ፍጹም የተዘነጋበት ሁኔታ ነው ያለው።
አስከፊ ነገር ከአገር የሚወጡት ሰዎች ኬላዎችን በረጅም ርቀት ለማለፍ ሲሉ ሚሔዱባቸው አካባቢዎች አርብቶ አደሩ የሚንቀሳቀስባቸው ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ምንም አይነት ጥንቃቄ ስለማይደረግ ወደ አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ በሽታው መግባት አዝማሚያው ከፍኛ እንደሆነ በአፋር ክልል የሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ይናገራል። ይህ ደግሞ አርብቶ አደሩ አኗኗር ዘየው በእጅጉ የተቀራረበ እና በአንድ ቤት ውሰጥ በርካታ ሰዎች ከመኖራቸው ጋር ተዳምሮ አንድ ቤተሰብ አባል ሲታመም በሽታው በቀላሉ ወደ ቀሪው ሕብረተሰብ እንዲዛመት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይታወቃል።
አሁንም ሕብረተሰቡ ዘንድ መሰራት ያለበት ጥብቅ ጉዳይ እንደሆነም አዲስ ማለዳ በጉዞዋ ለመታዘብ ችላለች። ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ አገር ጥለው ሔደው ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ደግሞ በዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኑ ዜጎችም ጉዳይ ከዚሁ እምብዛም የተለየ አይደለም። አዲስ ማለዳ በጋላፊ የፖሊስ ካምፕ ውስት ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ በካምፑ ውስጥ የተጠለሉ ተመላሾች ቁጥር 40 ሲሆን አንዳቸውም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው እና ርቀታቸውን ጠብቀው ሲቀመጡ አይታዩም። በለይቶ ማቆያው ውስጥ የሚገኙት ተመላሾች በአንድ ስፍራ ይሁኑ እንጂ የኮቪድ ምርመራ ውጤታቸው እስኪታወቅ ድረስ እንጂ ወደ መጡበት ቀየ መመለሳቸው እሙን ነው። ነገር ግን ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት ሰዎች ውጤታቸው ሳይታወቅ እንደዛ ባለ ሁኔታ ላይ መገኘታቸው ትንሽ ግርታን የሚፈጥር ነበር።
በእርግጥ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማንሳት የሚያስፈልገው እና ይበለስ የሚያሰኘው ጉዳይ፤ በኢትዮጵያ መጨረሻዋ የመንግስት መዋቅር የሆነችው በአፋር ክልል የምትገኘው የአሊደሀር ወረዳ ጽሕፈት ቤት አዲስ ማለዳ ወደ ስፍራው ከገባች ጀምሮ ምንም አይነት ስራም ሆነ እንቅስቃሴ አፍ እና አፍንቻ መሸፈኛ ጭንብል ሳይደረግ እንደማይከወን ታዝበን በዚሁ ይቀጥል በርቱ ብለንማል።
በቅርቡ በአፋር ክልል ያደረግነውን የመስክ ምልከታ እንደመነሻ አደረግነው እንጂ በአዲስ አበባ ጀምሮ ዙሪያ ያሉ ከተሞች እና ሌሎች ክልሎችም ውስጥ ለወረርሽኙ የሚሰጠው ትኩረት እና ጥንቃቄ በእጅጉ ያነሰ ስለሆነ ትኩረት የተነፈገው እስኪመስል ድረስ መዘናጋቶች የበዙበት ጊዜ ለመሆኑ መታዘብ ይቻላል።
በአንጻሩ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች በወረርሽኙ የተጠቃው ሰው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እና ከዚህም ባለፈ ደግሞ ወደ ጽኑ ሕሙማን ማዕከል የሚገባውም ቁጥር በዛው ልክ ማሻቀቡን የሚገልጹ ማስታወቂያዎች እየተነገሩ ይገኛሉ። ይህን ሰው እየሰማ እንዲሁ የማይተገበርበት አግባብ በመኖሩም እንደመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ውስጥ ኮቪድ 19 ወራቶች ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል መደረጉ አማራች ሌለው እርምጃ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሰዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በውስን አገራት ላይ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የክትባት ጉዳይ ደግሞ ሕብረተሰቡ በተለይም ደግሞ በመዲናዋ አዲስ አበባ ላይ ለመዘናጋቱ ዋነኛ ምክንያት እየሆነ ለመምጣቱም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሰዎች ይስማማሉ።
ከዚህ ቀደም በጤና ሚኒስቴር እና በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት ወረርሽኙ ሕብረተሰቡ ዘንድ መግባቱ ከተነገረ ወዲህ መጠነኛ ድንጋጤ ያውም ለጥቂት ቀናት ከሆነ በኋላ ነባራዊው ሁኔታ መጀመሩ ይታወሳል። በወቅቱ የተለያዩ ራስን ማጽናኛ ንግግሮች እየተነገሩ እና እየተስተጋቡ ነበር ይህም ምን ያህል ዋጋ እዳስከፈለን የሚታወስ ነው። ሐይማኖታዊ እና ብሔራዊ በዓላትን ተከትሎ በርካታ ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው አጋጣሚዎች የወረርሽኙ መዛመት ፍጥነት በቅጽበት ጨምሮ ምን ያህል ቁጥር በቀጣይ ቀናት እንደሚገኝበት ይታወቃል። ነገር ግን አሁንም ጉዳዩ በእጅጉ ከባድ እየሆነ መጥቷል፣ በተቃራኒው ደግሞ ግድየለሽነት እና ትኩረት መነፈጉ ደግሞ በዝግመት የሚመጡችግሮች ሳይሆኑ ዛሬ ላይ የምናየው ችግር እንደሚሆን በሚገባ ተረዳነው አይመስልም።
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013



