በአንድ ዕጅ የሚጨበጨበው የፍልሰተኞች ጉዳይ

0
699

የሰው ልጅ በሰማያዊም ሆነ በምድራዊ ሕግ በየትኛውም አካባ ተዘዋወሩ የመኖር እና ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የመንቀሳቀስ ባለ ሙሉ መብት እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ጉዳይ ታዲያ ተለጥጦ ከሕጋዊነቱ ይልቅ ከፍተኛ ወደ ሆነው የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አድጎ የዓለም አገራት ራስ ምታት መሆን ከጀመረም ዋል አድር ብሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት 760 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ባለበት አገር ውስጥ በተወለደበት አካባቢ እንደማይኖር የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ባወጣው መረጃ ማወቅ ይቻላል። ይህ ደግሞ መዘዋወር እና ፍልሰት ምን ያህል ሰዋዊ ባህርይ እንደሆነም ማሳያ ነው። ይህ ቁጥር የፍልሰተኞች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ሲል ማለትም ድንበር ተሸግረው የሚፈልሱትን ሲገልጽ ደግሞ 275 ሚሊዮን ፍለሰተኞች እንዳሉ ይነገራል።

በአንድም ሆነ በሌላ ሰዎች ከአንድ አካባቢ ተነስተው ወደሌላ ስፍራ ለመጓዝ ምክንያቶቻቸው ይለያያሉ።አንዳንድ ጊዜ ሰው ሰራሽ ችግሮች ማለትም ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት ፣ ሽብር፣ ሥራ አጥነት እና ተስፋ መቁረጥ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተፈጥሯዊ ችግሮችም በዛው ልክ ሰዎችን ከኖሩበት አካባቢ እና ቀየ ሊያፈልስ እና በሕጋዊም ሆነ በሕገ ወጥ መንገድ ሊያሰድድ የሚችለበት አጋጣሚ በርካታ ነው። በዓለም ላይ በአሁኑ ሰዓት ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በስደተኝነት ተመዝግበው እንደሚገኙ ይታወቃል። በአህጉራት ውስጥ እና ከአህጉራት ውጭ የሚደረጉ ሕጋዊ እና ሕገ ወጥ ፍለሰቶችም እንዳሉ ይነገራል ይታመናልም። በአፍሪካ ከፍተኛ ፍልሰተኞችን በመቀበል እና በውስጧ በመያዝ ወይም በማስተናገድ ግንባር ቀደም አፍሪካዊት አገር ደቡብ አፍሪካ ናት። እንደ መንግሥታቱ የፍልሰተኞች ድርጅት ሪፖርት በደቡብ አፍሪካ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

በአገራችን ኢትዮጵያ የፍለሰተኞች እና ከፍልሰት ተመላሾች እና ተደጋጋሚ ለፍልሰት የሚዳረጉ ሰዎች ጉዳይ በዕጅጉ አሳሳቢ ሆኗል። አዲስ ማለዳ ምስራቃዊውን የፍለሰተኞች ሕገ ወጥ አካሔድን መስመር ለመታዘብ በተገኘችባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ይህን ጉዳይ ለመታዘብ ችላለች። በተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) አማካኝት ወደ አገር ቤት የተመለሱ እና በሚመለሱበት ወቅትም በሚያጋጥማቸው ችግር ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ተደረጉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ይሁን እንጂ አሁንም ከፍልሰተኞች በዛ ቁጥር አንጻር ጉዳዮ በአንድ ዕጅ የማጨብጨብ ያህል ልፋትን ከንቱ የሚያደርጉ የአቅም ውስንነት እንደሚታይበትም የተለያዩ አካባዎች በተለይም ደግሞ ፍለሰተኞች በተደጋጋሚ በሚያቋርጡባቸው ቆላማ የምስራቅ አካባቢዎች ያሉ የመንግሥት መዋቅሮችም ይናገራሉ።

ኡመር አብዱልወሀብ ይባላል በቅጡ የአስራዎቹን ዕድሜ ያልተሸረ ለግላጋ ታዳጊ ነው። ተወልዶ ካደገበት እና በወጉ ከባልንጀሮቹ ጋር ትምህርት ባይሄድም ነገር ግን ዙሪያ ገባውን ካልጠገበባት እናት ምድሩ ተነስቶ ስደትን የመረጠ ታዳጊ ነው። ዛሬ በወቅቱ የነበረበትን ሥራ አጥነት እና ድህነቱን ለማሸነፍ ድንበር አሻግሮ እንዲመለከት እና ስደትን መርጦ እንደ አማራች እንዲወስድ ያደረገው ጉዳይ ሆኖ ነበር። ይህ ታዲያ ኡመርን ከቀየው ነጥቆ ለሕገ ወጥ ፍለሰት ዳርጎታል። ከዓመት በፊት ከሚኖርበት ሐረርጌ በሱማሌ ክልል በማድረግ ወደ ፑንት ላንድ ሶማሌያ ወደብ ወደ ሆነችው ቦሳሶ ከሌሎች ከኢትዮጵያ ከተለያዩ ክፍል ከመጡ ሰዎች ጋር በመሆን አቀና። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው ኡማር ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ከየመን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በአፋር ክልል የድንበር ከተማ በሆነችው ጋላፊ ከተማ በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንከብካቤ እየተደረገለት በነበረበት ወቅት ነው።

ከዓመት በፊት ኡመር ባህር ተሸግሮ የመን ከዛም መዳረሻውን ሳዑዲ አረቢያ በማድረግ ኑሮውን ለመቀየር ነበር ስደትን አንድ ብሎ ቦሳሶ ወደብ የተገኘው። በመንገድ ላይ የሚደርስባቸው እንግልት እና ስቃይ ተወርቶ እንደማያልቅ የሚናገረው ኡመር ከሁሉ ግን የሚያንገበግበው ደግሞ በመንገዱ ላይ እና በየመን አይኑ እያየ በውሃ ጥም እና በየመን ጦርነት ከአተገቡ የተለዩበት ባልጀሮቹ፣ የበርሃ ጓዶቹ፣ የስደት ተጋሪዎቹ፣ አገር ወዝ ሲናፍቀው የሚጽናናቸው ጓደኞቹ ሕልፈት ነው። ይህ ሁሉ ሆኖ ሕመሙን በውስጡ ይዞ የልብ ስብራቱን በነገ ተስፋው አፍኖ ከዛሬ ነገ ሳኡዲ አረቢያ ገብቼ ሕይወቴን እቀይራለሁ በናፍቆታቸው የምሰቃይባቸውን ቤተሰቦቼን ደግፌ ሰው ደረሰበት ደረጃ እደርሳለሁ በሚል ነበር ግቡን ትኩር ብሎም ሲመለከት የነበረው። ይሁን እንጂ ሰው እንዳሰበው አይውልም ወይም አይኖርም እና ኡመር ከየመን መሻገር አልቻለም። ከቀየው ከተነሳበት ጀምሮ ሲቆጥረው አንድ ዓመት በላይ ይሆነዋል በስደት ሕይወት ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥም መንገድ ላይ ነው።

ምንም እንኳን በእግሩ ባይጓዝም ሳኡዲ አረቢያ ገብቶ ሰርቶ እስኪለወጥ ድረስ ግን ልቡ መንገደኛ ነበር አንድም ቀን አርፎ አያውቅም። በኋላ ላይም ከየመን መሻገር ያቃተው እና በየመን ጦርነትም ባልንጀሮቹን ያጣው ኡመር ፊቱን ወደ አገሩ ለማዞር ተገደደ። እንዲሁ በባዶ ዕጁ እንደወጣ ባዶ ዕጁን ይዞ ከየመን ወደ ኢትዮጵያ በጋላፊ ድንበር ከሰባት ቀናት ጉዞ በኋላ ኢትዮጵያ ለመግባት ችሏል። ‹‹የመኒዎች ከባድ ጦርነት ላይ ናቸው እንኳን ለእኛ የሚሆን ማረፊያ ለራሳቸው በትልቅ ድህነት እና ችግር ውስጥ ነው የሚኖሩት፤ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመሻገር ሳንችል የቀረነውም በዚህ ምክንያት ነው። ምንም እንኳን ለመሻር ብንችል ውስጥ አካላችንን ማስወሰድ የግድ ይሆንብናል ወይም ደግሞ ልንገደልም እንችላለን›› ይላል ኡመር ከአዲ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ።

ይህ ኡመር ታሪክ ወደ ሌሎች ኹለት ሴቶች እና ጓደኞማቾች ዘንድ እንድናመራ እና ያጋጠማቸውን እንዲነግሩን ጋበዝናቸው። ከጅቡቲ እንደተመለሱ እና በጅቡቱ ውስጥ የደረሰባቸውን ግፍ እና መከራ የማያባራ በሚመስለው እንደ ጅረት ከሚፈሰው እንባቸው ጋር እየታገሉ ነበር ያወሩን። በጅቡቲ ውስጥ የአረብ ምግብ ቤት እና መዝናኛ ቤት ለማስተናገድ ተብለው ለደላላ ቀጣሪያቸው ብር ከፍሎላቸው ነበር ወደ ጅቡቲ በቦሳሶ በኩል ያቀኑት። ይሁን እንጂ ቆይታቸው ከአንድ ወር በላይ መዝለቅ አልቻለም። ምክንያ ደግሞ ጅቡቲ ፖሊስ ደስ ሲለው ከስራ ላይ ወስዶ ያስራቸዋል፣ ሲያሰኘው ደግሞ ድብደባ እያካሔደባቸው ሕይወታቸውን የቁም ሲኦል ሲያደርግባቸው አገሬ ማሪን ብለው ተመለሱ። ‹‹የጅቡቲ ፖሊስ አንድ ቀን እኛን እና ሌሎች ወንዶች ኢትዮጵያዊያንን ስራ ቦታ ወስደውን አሰሩን። ባዶ አፈር ላይ እኛ ሴቶችን እንድንተኛ ካደረጉን በኋላ ወንዶችን ደግሞ ሽንት ቤት ውስጥ ነበር ያሰሯቸው›› ይሉናል ባለታሪኮቻችን። ስማቸውን ከመጥቀስ እንድንቆጠብ አስረግጠዋል እና አንተቅስም ነገር ግን ጨዋታቸው አይጠገብም ያለፉበት ችግር ደግሞ በእጅጉ ልብ ይነካ ነበር እና አጠገባቸው ረጅም ሰኣታትን ተቀምጦ ሕመማቸውን መጋራት በእርግጥ የሚያስመኝ ነበር። ‹‹የአንድ ዓመት ልጅ አለችኝ ፤እኔ ደግሞ 20 ዓመቴ ነው ድሬዳዋ ናቸው ቤተሰቦቼ ችግር ሲያጋጥመኝ እና የማደርገው ሳጣ ነው ስደትን የመረጠኩት እንጂ እኔ ልጄን ለአንድም ቀን ተለይቻት መዋል እና ማደር አልችልም ›› ትላለች ጅቡቲ ላይ ለመስተንግዶ ያቀናችው ባለታሪካችን። በልጇ ናፍቆት የምትብሰለሰለው ታዳጊ ስትታይ አንጀት ትበላለች ልጅነቷን በእናትነት እና በስደት ልትቀማ የደረሰች፣ በለጋነት ዕድሜዋ እናትነት የሚሉት ትልቅ ኃላፊነት የተጫነባት ምስኪን ሴት። በጋላፊ የፌደራ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ ያገኘናቸው እነዚህ ወንዶች እና ሴቶች ኢትዮጵያዊያን ዳግመኛ መመለስ አይደለም ገና ነገ አዲስ አንድ ብለው ስደትን ለሚያስቡ ሰዎች ከዳር እስከ ዳር እየተዘዋወርን ኢትዮጵያን በወርዷ እና ቁመቷ ስለ ስደት አስከፊነት ብንሰብክ አይወጣልንም ባይ ናቸው።

የመጀመሪያው ባለታሪካችን የነበረው ኡመር ከኦሮሚኛ ውጪ ቋንቋን አያውቅ ኖሮ በትርጁማን ነበር የሚናግረን የነበረው እና ‹‹ቢያንስ አገሬ ላይ ሰው አለኝ ሳየው መልኩን ታዝቤ እኔ ሰው እደሆነ የሚረዳኝ ፣ ሲያመኝ ቋንቋን ባይናገር ሩቅ ሳልሔድ በቋንቋየ የሚስታመኝ ሰው አለኝ›› ሲልም መመለሱን በተለይም ደግሞ በጤና መመለሱን እንደ ድል ይቆጥረዋል።

ጋላፊ በሚገኘው በፌደራል ፖሊስ ካምፕ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ተመላሾች ከተለያዩ አገራት ባለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ስራዎች በመዘጋታቸው እና ችግር ውስጥ በመግባታቸው በአፋር ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክሩ በድንበር ጠባቂዎች ተይዘው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የተደረጉ እና የምርመራ ውጤታቸው ታይቶ ደግሞ ከ1600 ብር ጋር ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚደረጉ አዲስ ማለዳ በስፍራው ተገኝታ ለማረጋገጥ ችላለች።
በለይ ማቆያው ውስጥ ታዲያ አዲስ ማለዳ በተገኘችበት አንድ ተሲያት በኋላ ላይ በግቢው ውስጥ 28 ሰዎች ሲኖሩ አራቱ ሴቶች መሆናቸውንም ለማየት ተችሏል። ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ በጊቢው መግቢያ ከጠባቂዎች ጋር በነበራት ቆይታ 12 አዳዲስ ተመላሾች ከጨቅላ ሕጻናት ጋር በመሆን ወደ ጊቢው ሲቀላቀሉ ታዝባለች።

ይህ ደግሞ በወቅቱ አስቀድሞ ነበረውን ቁጥር በአፍታ ውስጥ ወደ 40 ከፍ ያደርገዋል ማለት ነው። ዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በጋላፊ ለይቶ ማቆያ ካምፕ ውስጥ ኮቪድ 19 ከገባ ጀም ወደ 4000 ሰዎችን ተቀብሎ ያስተናገደ እና የኮቪድ 19 ምርመራ ተደርጎም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ድጋፍ አድርጓል። በዚህ ወደ አንድ ኣመት ለሚጠጋ ጊዜ ባካሄደው ስራም ራት የሚሆኑ ብቻ ሰዎች ናቸው ኮቪድ ተገኝቶባቸው የነበሩት ሲልም ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ከዚህ ሁሉ ግን አስገራሚው እና አስደንጋጩ ነገር ከፍልሰተኞች ድርጅት ማወቅ እንደተቻለው እን ድርጅቱም ምንም ማድረግ ይልቻለበት ምክንያት የፍልሰተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ነው። ተጎድተው እና አንዳንዶቹም ሕይወጣቸው በርሃ ላይ እንዳለፈ እየታወቀ ሰዎች ለስደት የሚነሱበት አጋጣሚን በምን ሁኔታ ቢሰራ መቅረፍ እንደሚቻል ድርጅቱ ውስጥ ግልጽ ነገር ማግነት አይቻልም። ለዚህ ደግሞ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት በፍልሰተኞች ጉዳይ ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት መኖራቸው ሚታወቅ ሲሆን በቅንጅት አለመሰራቱን ለመታዘብ ችላለች። ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ እና የአፋር ሰራተኛ እና ማኅበራዊ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት መዋቅር ዘንድ ተገኘው መረጃ እንደሚሚሊክተው አምስት እና ስድስት ጊዜያት ስደት ሔደው የተመለሱ ወይም ደግሞ ወደ አገር ውስጥ ተመልሰው ድጋሚ ለመሰደድ ፈልገው መንገድ ላይ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ነው።

ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት የሚጠቀሰው ወደ ቀያቸው በሚሄዱበት ወቅት የሚገቡበት እና አደራጅቶ ወደ ስራ የሚሰማሩበት ሁኔታ አለመመቻቸቱ፣ በገቢ ወላጆቻቸውን እና ራሳቸውን መደገፍ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ መሆናቸው እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ለድጋሚ ብቻ ሳይሆን ለተደጋጋሚ ስደት እንደዳረጋቸው እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።

በመጀመሪያዎቹ የኮቪድ 19 ወራት ላይ አገራት ስራዎቻቸውን በመዝጋታቸው ወደ ዘገራቸው ለመመለስ ተገደዱት ኢትዮጵያዊያን በአፋር በኩል በኹለት አቅጣጫ ነበር በገፍ የገቡት፤ ምንም እንኳን መውጫቸው ከሰመራ በሦስት አቅጣጫ ቢሆንም። ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከጅቡቲ በጋላፊ ወደ ሰመራ የሚወስደውን መንገድ የሚጠቀሙ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በታጁራ ወደብ በአፋር የኢትዮጵያ የመጨረሻዋ የመንግስት መዋቅር በሆነችው አልኤዳሃር ወረዳ አድርገው ወደ ሰመራ የሚወስደውን መንገድ ለመያዝ መሞከር ይሆናል። ታዲያ የአፋር ሰራተኛ እና ማኅበራዊ ቢሮ የስደተኞች ጉዳይን በሚመለከት የስራ ኃላፊ የሆኑት እሰማኤል አምበሳ በቀን እስከ 200 ሰዎች ከተለያዩ አገራት በጅቡቲ በኩል ወደ አገር ውስጥ ከላይ በተጠቀሱት ኹለት መስመሮች ይገቡ እንደነበርም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአልኤደሀር ወረዳ ወረዳው የጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ እንደሚሉትም ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ተመላሾችን ማስተናገድ ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ ደርሰው እንደነበርም አስታውቀዋል።

‹‹በመጀመሪያ ወቅት በቀን እስከ 200 ሰዎች ይመጡ ስለነበር ከባድ ወቅተ ነበር። በዚህም ምክንያት በአንድ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አስጠልለን ለማስቀመጥ ችለን ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ትምህርት በመጀመሩ አስወጥተን ወደ ጋላፊ እንዲዘዋወሩ አድርገናል›› ሲሉ ተናግረዋል። ወረዳው ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ እደተናገረው በጀት ከማጣቱ እና የተመላሾችም ቁጥር ከመብዛቱ የተነሳ የወረዳው ሰራተኞች ራሳቸው ከኪሳቸው ገንዘብ በማዋጣት ተመላሾችን ለመመገብ የተገደዱበት አጋጣሚ እንደነበር እና የወረዳውን መደበኛ ስራ ማስኬጃ በመጠቀም እና በመጨረስ ወረዳው ስራ እስከማቆም ደረሰበት ጊዜም እንደነበር አውስተዋል።

የአልኢደሀር ወረዳ ከጅቡቲ ጋር እንደመዋሰኑ መጠን ከፍተኛ የሆነ የተመላሾች ቁጥር የሚመዘገብበትም አካባቢ እንደሆነ ከወረዳው የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ምንም እንኳን መመለሱ በድንበር ኬላ ጥበቃዎች በኩል መደረጉ እንዲመዘገቡ እና አስፈላጊውን የኢሚግሬሽን ቅደመ ሁኔታዎች እንደሚሟሉ ቢታወቅም የስደት ጉዞው ግን እንደሚታወቀው ሕገ ወጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከኬላዎች የራቁ ናቸው። በአካባቢው ከለው ሞቃታማ ብቻ ሳይሆን በረሀማ የኤር ንበረት አንጻር እንኳን በሕገ ወጥ መንገድ ያውም በእግር ድንበር አቋርጦ ለመሰደድ ይቅርና የቅርብ ርቀት ጉዞዎችን ማድረግ ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው። በመኪና በሚደረጉ ጉዞዎች እንኳን የመኪናው ምኮቶች ከግራ እና ከቀኝ በሁሉም አቅጣጫ ተከፍቶ ምንም እንኳን ሞቃታማ አየር ቢሆንም ከምንም ይሻላል በሚል የሚከፈትበት ከባድ አየር ነው። የሰው ልጅ ሊወጣቸው ያውም በዚህ አየር ንብረት ተቋቁሞ ሊያቋርጣቸው ይችላል ተብሎ ሊታሰቡ የሚከብዱ ጋራዎችን አቋርጠው እና ከድንበር ጠባቂዎች ተሰውረው ነው ወደ ጎረቤት አገራት የሚሻገሩት። አዲስ ማለዳ ከድንበር ጠባቂዎች የፌደራል ፖሊስ አባላት ጠይቃ ለመረዳት እንደሞከረችው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ድንበር ለማቋረጥ ሲሞክሩ እንደሚያዙ እና ለቁጥር የሚያዳግቱት ደግሞ ሳይያዙ ወደ ጎረቤት አገራት እንደሚሻገሩ ለማወቅ ተችሏል።

የጸጥታ አካላትን ሸሽተው ሰው ሊደርስበት በማይችልባቸው እጅግ ፈታኝ አካባቢዎች በውሃ ጥም እና በሐረሩር ተቃጥለው ለመሳቋረጥ የሚሞክሩባቸው አካባቢዎች ፍልሰተኞችን ለሞት እንደሚዳርጋቸውም የፌደራል ፖሊስ አባላት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ከኬላዎች በራቀ ሁኔታ በአስቸጋሪ ስፍራ ስለሚጓዙ ቢጎዱ እንኳን ደርሰን ዕገዛ አድርገን እዳናድናቸው ሆነው ነው የሚጓዙት። እንዲያውም አንድ ጊዜ ተጓዦች ወደ አገረ ሲመለሱ ሳሄዱ ነበረበትን ሁኔታ ሲነግሩን በጉዟቸው ወቅት አንድ ሰው ታሞ መራመድ አቅቶት ይወድቅ እና ጥቂት ቆይቶ ሞተ፤ አፈር እንዳናለብሰው ስፍራው ድንጋይ እንጂ አፈር አልነበረም ስለዙህ ጥለነው ሔድን ሲሉም ነግረውናል›. ሲሉ ፌደራል ፖሊስ አባላት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በእጅጉ ልብን የሚነካው ደግሞ አሁንም ድረስ የበረሀ አሞራ ሲሳይ ሆኖ የቀረው የዜጎች ቁጥርን ፈጣሪ እንጂ መንግስትም ሆነ ሌሎች በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ትክክለኛውን ቁጥር አለማወቃቸው ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ለማወቅ አይከብድም።

ወደ አገር ቤት በሚመለሱበትም ወቅት በመንገድ ላይ የተደፈሩ፣ ውስጥ አካላቸው ተሰርቆ አገር ቤት ገብተው እንኳን በጤንነት እንዳይኖሩ ‹‹አተርፍ ባይ አጉዳይ›› አጋጣሚዎች ሰለባ የሆኑ ሰዎች፣ በመንገድ ላይ በወሊድ ወቅት ሞቱ እና ሌሎች የሰሚን ጆሮ ጭው የሚደርጉ ገጠመኞች የሚሰማባቸው ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ድንበር የገጠር ከተሞች ዛሬም ተመላሾችን፣ ፍለሰተኞችን እና ለዳግም ፍልሰት የሚዘጋጁትን በእቅፋቸው ይዘዋል። ‹‹በአንድ ወቅት አርብቶ አደሮች አንዲት ሴት በዛፍ ጥላ ስር ብቻዋን ሆና በአደገኛ ሕመም ውስጥ እንዳለች መልእክት ይነግሩናል። እኛም በአፋጣኝ ወደ ስፍራው ለመሄድ የግለሰብ መኪና አስነስተን ሔድን ።

በአጋጣሚ ሴቷ የነበረችበት ስፍራ በጅቡቲ ክልል ውስጥ ስለሚገኝ ከአካባቢው የጅቡቲ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረን ወደ ሴቷ መገኛ አመራን በወቅቱ እርጉዝ ስለነበረች ረጅም ሰዓት በእግሯ በመጓዟ እና የውሃ ጥም ስለነበረባት እንዲሁም ምግብም ስላልበላች አቅም አንሷት ወድቃ ነበር። እኛም ተገቢውን እርዳታ አድርገን በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም ይዘናት በመሔድ ሕይወቷን ልናተርፍ ችለናል፤ ጽንሷ ግን ሊቋረጥ ችሏል›› ሲሉ የአልኢደሀር ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። በሴቶች ላይ ሚደርሰው ጉዳት በእጅጉ የከፋ እንደሆነ እና በተለይም ደግሞ የወረዳው ሰራተኛ እና ማኅበራዊ እንዲሁም የአፋር ክልል ሰራተኛ እና ማኅበራዊ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ እንደሚናገረው በሴቶች ዙሪያ የሚሰሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቅንጅት ከእኛ ጋር አይሰሩም ሲሉም ይደመጣሉ።

በኮቪድ 19 መጀመሪያዎቹ ወራቶች ላይ ከአገር የመውጣቱ ሒደት በእጅጉ ተቀዛቅዞ እንደነበር እና ተመላሾች ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ እንደነበር የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ይናገራል። ይህን የሚጢናክረውም የአልኢደሀር ወረዳም ጅቡቲ ድንበሯን ከመዝጋቷ ገር ተያይዞ መግባት ጥብቅ ስልነበር ፍልሰተኞች በእጅጉ ቀንሰው እንደነበር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በነባራዊ ሁኔታ ፍልሰተኞች ቁጥራቸው ሚበዛባቸው እና ድንበር አቋርጠው የሚሻገሩ ሰዎች ቁጥር የሚያይልበት ወራቶች እና ጊዜያቶች እንፈዳሉም የወረዳው የኮምኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

አካባቢው እና ጅቡቲ በአብዛኛው የዕስልምና እምነት ተከታዮች በብዛት ሰለሚኖሩ የእስልምና ተከታዮች የረመዳን ጾም በሚጀምርበት ወቅት ጥበቃው ይላላል ተብሎ ስለሚታመን ደፍልሰተኞች ቁጥርም እንደሚያይል ለማወቅ ተችሏል። በሌላ በኩል ደግሞ የፍልሰተኞች እና ሰዎችን የማሻገሩ ጉዳይ በከፍተኛ መረብ የተሳሰረ በመሆኑ ውቅያኖሶች ማዕበላቸው ጋብ የሚልባቸው ወራቶች ከወደብ አካባቢ ካሉ ሰዎች ሲነገር በዛውም ልክ የስደተኞ ቁጥር እንደሚጨምር አዲስ ማለዳ ከአፋር ክልል አልኢደሀር ወረዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here