ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።
ሶለን ገመቹ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
ባለፉት ኹለት ዐሥርተ ዓመታት ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ጉዳይ በፖሊቲካ ሳይንስና በልማት (‘ዴቨሎፕመንት’) አጥኚዎች ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል። ይህ የሆነበት ምክንያት የሲቪል ማኅበራት ለዲሞክራሲና ለልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ስለሚታመን ነው። በዚህ ጽሁፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ለልማትና እና ለዲሞክራሲ ያላቸውን ሚና ለመቃኝት ይሞከራል።
ሲቪል ማኅበረሰብ የሚለውን ሐረግ ብዙ ጊዜ በአካዳሚና በፖሊሲ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ይጠቀሙበታል። ይሁን እንጂ በትርጉሙ ላይ የጠራ ስምምነት የለም። የተለያዩ የፖለቲካ እና የዲቨሎፕመንት አጥኚዎች ለሲቪል ማኅበረሰብ (Civil Society) የተለያየ ትርጉም ይሰጡታል። ይህም ከሆነበት ምክንያት አንዱ መሠረት ያደረጉት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፍልስፍና ላይ ያለ ልዩነት ነው። ጥንታዊ የግሪክና የሮማ ፖለቲካ ፈላስፋዎች እንዲሁም በዘመናችን የሊበራል ዲሞክራሲ እና የማርክሲስት ዐቀንቃኝ የሆኑ ምሁራን የሲቪል ማኅበራትን የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ነው። የሲቪል ማኅበራት ጽንሰ ሐሳብ ውስብስብነት የሚመነጨው የፖለቲካ ፈላስፋዎች የሲቪል ማኅበራትን ከተለያየ አቅጣጫ ስለሚያዩ ነው። ለምሳሌ እንደ ሄግል፣ ማርክስ፣ እና ኤንግልስ የሲቪል ማኅበራትን ቁስ አካላዊ አድርገው ይመለከቱታል። እንደ ቴይኳቬሌ ያሉት ደግሞ የሲቪል ማኅበራት ከዲሞክራሲያዊ አደራጃጀት ጋር ያያይዙታል።
ፖለቲካዊ የሲቪል ማኅበራት ጽንሰ ሐሳብ በዓለማችን ላይ የበለጠ ተቀባይነት ያገኘውና በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሲቪል ማኅበራት ጽንሰ ሐሳብ አረዳድ ከምዕራብያውያን የሌበራል ዴሞክራሲ ኀልዮት የተቀዳው እና የሲቪል ማኅበራትን ከአውሮፓ እና አሜሪካ ሀገር እንዳሉት አድቮኬሲ ግሩፕ (Advocacy Group) መሆንን እንደዋነኛ የሲቪል ማኅበራት መገለጫ አድርጎ የሚያየው ፖለቲካዊ የሲቪል ማኅበራት ጽንሰ ሐሳብ ነው። በተለይ የሲቪል ማኅበራት የሚለውን ሐረግ መንግሥታዊ ያልሆነ የእርዳታ ድርጅት (NGO) ማለት እንደሆኑ አድርገው የሚናገሩ ብዙ ዓለም ዐቀፋዊ የእርዳት ድርጅቶች መኖራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘ አረዳድ አድርጎታል።
እነዚህ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሲቪል ማኅበራትን የሚያዩበት መንገድ በዓለም ላይ የእነሱን ዓይነት ዲሞክራሲ እና ልማት የማምጫ ዓይነተኛ ፕሮጀክት አድርገው ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለ የዲሞክራሲ ባህል ያልዳበረበት ሀገር የሲቪል ማኅበራትን አቅም መገንባት ዓለም ዐቀፋዊ የዲሞክራሲ ግንባታ አካል መሆኑን ያምናሉ። ለምሳሌ ዓለም ዐቀፍ የሲቪል ማኅበራት ኅብረት (Internaltion Civll Society Network) ዓላማው ዓለም ዐቀፋዊ እና ብሔራዊ የሲቪል ማኅበራት አቅም መገንባት ነው።
በዚህ ታዋቂ የሲቪል ማኅበረሰብ አረዳድ መሠረት የሲቪል ማኅበረሰብን፥ የሲቪል ማኅበረሰብ የሚያሰኘው መደበኛ አደረጃጀት ኖሮት ሲገኝ ነው። በዚህ የሲቪል ማኅበረሰብ አረዳድ መሠረት የሲቪል ማኅበረሰብ የሚከተሉትን መመዘኛዎች ሟሟላት አለበት።
1) ከማኅበረሰቡም ሆነ ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ መሆን (autonomy)፣ 2) የፖለቲካ ፓርቲ ውግንና የሌለው መሆን (No intention to govern the polity)፣ 3) የማኅበረሰቡን ጥቅምና ፍላጎት ለማሳካት የማኅበራዊ እንቅስቃሴ (collective action) የመፍጠር አቅም መሆኑ ናቸው።
ይህን የተለመደ የሲቪል ማኅበራት አረዳድ ትኩረት አንድ ማኅበረሰብ ፍላጎቱን ለማሟላት የተደረጀ መዋቅር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። በሌላ አማርኛ መደበኛ የሲቪል ማኅበር ማለት ቀድሞ በወጣ የሲቪል ሕግ መሠረት ለመሥራት ስምምነት ያደረገና በመከባበር መርህ ላይ የተመሰረተ ድርጅት ነው። ስለዚህ ድርጅቱ ሕግን፣ ልዩነትን እና ሌሎች ድርጅቶችን የሚያከብር መሆን አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ ሎረን ዋይትሄድ በሰጠው የሞራል አስተያየት የሲቪል ማኅበራት አቅም በወጣ ሕግ ብቻ መወሰን የለባቸውም። በአንጻሩ የሌሎች ሐሳብ እና ፍላጎት በማክበር ላይ መመስረት አለባቸው።
ከላይ የተጠቀሱት መደበኛ የሲቪል ማኅበረሰብ መመዘኛዎች ፖለቲካዊ የሲቪል ማኅበረሰብ አረዳድ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ጠባብ የሲቪል ማኅበረሰብ ጽንሰ ሐሳብ ያደርገዋል። ይህ የሲቪል ማኅበረሰብ ግንዛቤ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ‘የሲቪክ’ ድርጅቶች ብቻ ያካተተ ነው። በዚህ ምክንያት ፖለቲካዊ የሆነው የሲቪል ማኅበረሰብ ግንዛቤ እንደሲቪልነት፣ በጎ ፍቃደኝነት፣ የኢኮኖሚ ነጻነት፣ ዜግነት፣ መብቶች፣ የሕግ የበላይነት እና የዲሞክራሲያዊ ውክልና ሐሳቦች ላይ ይመሰረታል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት ከመታወቃቸው በፊት የተለያዩ ኢ-መደበኛ ተቋማት ለማኅበረሰቡ በኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አገልግሎት እየሰጡ እንደነበሩና እንዳሉ ይታወቃል። ይሁንና ከላይ የተገለጸውን ፖለቲካዊ የሆነው የሲቪል ማኅበራት ግንዛቤ እነዚህን ኢ-መደበኛ የሲቪል ማኅበራት አያካትትም። ምክንያቱ ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን የሲቪልነት መመዘኛ ስለማያሟሉ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው አገር በቀል አደረጃጀት ከበጎ ፍቃደኝነት ይልቅ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነው። አንዳንድ ምሁራን እነኚንህን በግንኙነት ላይ የተመሰረተ የጎሳ እና የሃይማኖት አደረጃጀቶች ሲቪልነት ስለሚጎላቸው ለሲቪል ማኅበራት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳላቸው ይናገራሉ። ስለዚህ መደበኛውን የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የሲቪል ማኅበረሰብ ለማዳን እንደ ዓለም ባንክ (World Bank) እና የአሜሪካ መንግሥት ተራድዖ ድርጅት (USAID) ያሉ ድርጅቶች የሲቪል ማኅበራት አቅም መንባት እንዳለባቸው ይመክራሉ።
ለዚህ ተግባር መሠረት ተደርጎ የተወሰደው የዲሞክራሲ እሴቶችን ማስተዋወቅ ነው። በዚሁ መሠረት በአሜሪካ እና በአውሮፓ እንደሚደረገው የኢትዮጵያ መደበኛ የሲቪል ማኅበራት በመደበኛ መዋቅራቸው አማካኝነት አባላቶቻቸው የማኅበረሰቡን ፍላጎት የማስተዋወቅ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ያምናሉ። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲን ባህል ለማዳበርና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ዓይነተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ ተብሎ ይታመናል።
ይህ ፖለቲካዊ የሲቪል ማኅበረሰብ አረዳድ የተለያዩ ችግሮች አሉበት። አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሲቪል ማኅበራት በዚህ መረዳት ላይ በመመስረት የትኛው ሲቪል እንደሆነ የትኛው ቅድመ-ሲቪል እንደሆነ፣ የትኛው ድግሞ ሲቪል ያልሆነ፣ የትኛው ደግሞ ድኅረ ሲቪል አደረጃጀት እንደሆነ መተንተን አስቸጋሪ ነው። ኹለተኛ – ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢ-መደበኛ የሲቪል ማኅበራት እና ባህላዊ አደረጃጀቶች ከመደበኛው የሲቪል ማኅበረሰብ የተገለሉ በመሆናቸው በእነሱ የሚወከል የኅብረተሰብ ፍላጎች አብሮ እየተገለለ ነው። ዲሞክራሲ ማለት ዓለም ዐቀፋዊ የዜጎች አስተዳደራዊ ተሳትፎ ማለት ከሆነ የብዙኀኑን ማኅበረሰብ አደረጃጀት እና ፍላጎት የሚያገል የሲቪል ማኅበረሰብ ዲሞክራሲን ሊያመጣ አይችልም።
ዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ውጤት በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለው የፖለቲካ ሥልጣን አያያዝና አጠቃቀም ነው። ከዚህ አንጻር የሲቪል ማኅበራት ሕዝባዊ መሠረት ሊኖራቸው ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮት ሆኖ ሊጠቀስ የሚገባው መንግሥት ያለውን ኀይል በመጠቀም ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግርን በማዛበት የሚወክለውን ጠንካራ የማኅበረሰብ ክፍል ፍላጎት እያሟላ መቀጠሉ ነው። ስለዚህ ዲሞክራሲ ወዳድ የሆኑ የሲቪል ማኅበራት ራሳቸው ሕዝባዊ መሠረት ሊኖራቸው ይገባል። ምንም እንኳን በውጪ ሀገር ለጋሾች ላይ ጥገኛ የሆኑ የሀገራችን መደበኛ የሲቪል ማኅበራት የማይናቅ ሚና ቢኖራቸውም የጎላ ማኅበራዊ መሠረት አላቸው ለማለት ግን አያስደፍርም። ስለዚህ በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር እና ዲሞክራሲ በዘላቂነት የማስፈን ጥረት በመደበኛ የሲቪል ማኅበራት ጥረት ብቻ ሊመጣ አይችልም።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈለገውን የመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ስርዓት ለማምጣት የመደበኛ የሲቪል ማኅበራት ብቻቸውን በቂ ስላልሆኑ የሲቪል ማኅበራት እሳቤ ሰፋ ብሎ ኢ-መደበኝ የሆኑትን ሀገር በቀል ማኅበራት በትንተናው ውስጥ ማካተት አለበት። ኢ-መደበኛ የሆኑት ሀገር በቀል ማኅበራት የሲቪልነት ሕግን ለመቀበል ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የሃይማኖት እና የጎሳ ማኅበራት የጨዋታውን ሕግ ካከበሩ ከመንግሥት የሚያገኙት ማበረታቻ እንዳለ ሲያስቡ አደረጃጀታቸውን በሕጉ መሠረት ሊያደርጉት ይችላሉ። ስለዚህ ሲቪል ያልሆነ ባህሪ እንዳይታይ የሚያደርገው ሀገረ-መንግሥቱ የተለያዩ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ፍላጎቶች ማስታረቅ ሲሳነው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ለማምጣጥ የሲቪል ማኅበራት ያላቸውን ሚና በበለጠ ለመረዳት የሲቪል ማኅበራት አረዳድ ሰፋ ማለት አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ሀገር በቀል የሆኑ ኢ-መደበኛ የሃይማኖት፣ የጎሳ፣ እና የሙያ ማኅበራት የሲቪል ማኅበራት ትንታኔ ውስጥ መካተት አለባቸው። ይህን ለማድረግ የሲቪል ማኅበራት ፖለቲካዊ ትርጉም ወደ ማኅበረሰብ ሳይንስ (Sociological) ትርጉም ቀይረን ባህላዊ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራትን በማካተት የሲቪል ማኅበራት ለመልካም አስተዳደር እና ለዴሞክራሲ ያላቸውን ሚና መተንተን ይኖርብናል።
የሲቪል ማኅበራት የማኅበራዊ ሳይንስ ትርጓም (‘ሶሲዮሎጂካል’ ትርጓሜ) ዘርፈ ብዙ የማኅበረሰብ ቡድኖችን ይጨምራል። በዚህ አረዳድ የሲቪል ማኅበራት ከመንግሥትና ገበያ ውጪ የሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማስከበር የሚሠሩ ሁሉን ዓይነት ማኅበራት እና ድርጅቶች ይጨምራል። ይህ የማኅበረሰብ ሳይንስ (Sociological) የሲቪል ማኅበራት ግንዛቤ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ የሲቪል ማኅበራትን ያጠቃልላል። ይህ ግንዛቤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የሲቪል ማኅበራት ሚና ለመተንተን ከፖለቲካዊው የሲቪል ማኅበራት ግንዛቤ የበለጠ ጠቃሚ ነው።
የማኅበራዊ ሳይንስ የሲቨል ማኅበራት ግንዛቤ የተመሰረተው በሦስቱ የማኅበረሰብ ዘርፎች ግንዛቤ ላይ ነው። በዚህ ዕይታ ሦስቱ የማኅበረሰብ ዘርፎች ማለትም መንግሥት፣ ገበያ እና የሲቪል ማኅበራት እውቅና ተሰጥቷቸዋል። እያንዳንዱ ዘርፍ ሕግ የማውጣት እና የማስፈጸም ሚና፣ የንግድ ልውውጥ የሚደርግበትን ቦታ፣ ጊዜ እና ሁኔታ የመወሰን እንዲሁም በጋራ ጉዳዩች ላይ የመወያያ እና የመከራከሪያ መድረክ አለው። እያንዳንዱ ድርጅት ከዘርፉ ጋር አብሮ ለመሄድ የሚያስችለው ድርጅታዊ መዋቅር አዳብሯል። ለምሳሌ መንግሥትና የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የሀገረ መንግሥቱ ድርጅታዊ መዋቅር ናቸው። የንግድ ድርጅቶች፣ ኢንርፕርይዞች ወይም የአክሲዮን ማኅበራት የገበያ ድርጅታዊ መዋቅር ናቸው። የሲቪል ማኅበራት ደግሞ የማኅበራዊ ጥቅምና የጋራ ፍላጎቶች፣ አደረጃጀት መዋቅር ናቸው።
የማኅበራዊ ጥቅም ድርጅቶች የሚቋቋሙት የማኅበረሰቡን የጋራ ጥቅም ለማስከበር ሲሆን ተልዕኳቸው የራስ ተነሳሽት ባላቸው ዜጎች የጋር ግንዛቤ እና እሴት ላይ ይመሰረታል። ድርጅቱን የሚመሩ ሰዎች ተጠያቂነት ለድርጅቱ መወቅር እንጂ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ አይደለም። ድርጅቶቹ ወይም ማኅበራቱ የሚሰሩት ስራ የሆነን የማኅበረሰብ ክፍል ጥቅም ለማስጠበቅ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የግድ የዚህ ማኅበረሰብ ክፍል ውክልና አላቸው ማለት አይደለም። በአንጻሩ ለጋራ ጥቅም የተቋቋሙ የስቪል ማኅበራት ወይም ድርጅቶች ዓላማ የአባላቱን የጋራ ጥቅም ማስከበር ነው። በመርኅ ደረጃ የጋራ ጥቅም ማኅበራት ወይም ድርጅቶች ተጠያቂነት ለማኅበሩ አባላት ነው። የማኅበሩ አባላት በማኅበሩ አመራር ላይ እምነት ካጡ የማኅበሩን አመራር የመቀየር ሥልጣን አላቸው። በተጨማሪም የማኅበሩ አመራር ጥቅም ከሌሎች አባላት ጥቅም ሊለይ አይችልም። ይሄ በማኅበራዊ ጥቅም ድርጅቶች እና በጋራ ጥቅም ድርጅቶች መካከል ያለ ልዩነት ነው።
በአጠቃላይ የሲቪል ማኅበራት የማኅበራዊ ልማት አቅጣጫ ላይ የክርክር እና የውይይት መድረኮችን ይፈጥራሉ፤ ማኅበረሰቡ መንግሥት እና ገበያ ላይ ተጽእኖ እና ቁጥጥር እንዲያደረግም ያስችላሉ። በተጨማሪም ለፖለቲካዊው ማኅበረሰብ የውይይት መድረክ በመፍጠር ሁሉንም ኅብረተሰብ ተጠቃሚ የሚደርግ እርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግ ያስችላል።
ዴሞክራሲን እና መልካም አስተዳደርን በተመለከተ በሲቪል ማኅበራት ውስጥ መሳተፍ መሰረቱ የእያንዳንዱ ግለሰብ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ መብት እንዲሁም በየጊዜው የሚደረገው የመንግሥት ምርጫ ብቻውን የማኅበረሰቡን ፍላጎት ወደ መንግሥታዊ አስተዳደር ለማምጣት በቂ ስላልሆኑ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013



