የቀድሞው ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአሁኑ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ አዲስ መዋቅር ከፍተኛ ሠራተኞችን እንጂ ዝቅተኛ ሠራተኞችን ያማከለ አይደለም፤ ደሞዛችን ዝቅተኛ ነው ሲሉ የድርጅቱ ሠራተኞች ያላቸውን ቅሬታ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
የቀድሞው ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአሁኑ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በሚከፈላቸው ደሞዝ ደስተኛ አለመሆናቸውን እንዲሁም የሥራ አድማ ማድረጋቸውን ጭምር አስታውቀዋል።
ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለፁት ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ደብረ ብርሀን የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኛ እንደተናገሩት በመስሪያ ቤቱ ላይ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ 11 የደሞዝ እርከን ላይ ያሉት ሰራተኞች በጠቅላላ ቅሬታ እያቀረብን ነው ብለዋል።
ያላቸውን ጥያቄም በተደጋጋሚ እየተናገሩ እንዳሉ እና በቅርቡም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ቅሬታቸውን ማሰማታቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም የሰራተኞቹን ጥያቄ እንዲያቀርብ ማህበር እንደነበራቸው የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢው ማህበሩ ግን ስራውን እየሰራ እንዳልሆነ እና እንደውም የማህበሩ ሀላፊ እንዴት እንደሆነ ባታወቀ ምክንያት ቅሬታ የለኝም ደስተኛ ነኝ ሰራተኛውም ደስተኛ ነው እንዳሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡት የድርጅቱ ሰራተኛ አዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን የሰራተኛው ጥያቄ አንዳልቆመ እና በመስራያ ቤቱ 92 ነጥብ ሰባት ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ሰራተኞች ደስተኛ እንዳልሆነ እንዲሁም ሰባት ነጥብ አንድ ኹለት የሚሆኑት ብቻ ማለትም ከደረጃ 12 እና ከዛ በላይ የደሞዝ እርከን ላይ ያሉት ሰዎች ብቻ ቅሬታ የሌለባቸው እንደሆኑም ይታወቃል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም በድርጅቱ ካሉ 555 ሰራተኞች መካከል 521 የሚሆኑት ሰራተኞች ጥያቄ እንዳቀረቡ እና ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣትም ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን እንዲሁም ሪፎርሙ ከተደረገ በኋላ ስራው እየተሰራ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የድሮው ሜቴክ አዲሱ አደረጃጀቱ ሙሉ በሙሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን የሚጠቅም እንጂ ዝቅተኛ ሰራተኞችን ያማከለ አይደለም ብለዋል።
ከደሞዝ በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ነው የተናገሩት። አዲስ የመጣው የሰው ኃይል መስፈርት በማያሟላ መልክ የገባ ነው ለአብነትም መሪ መሀንዲስ ስድስት አመት በኢንጅነሪንግ ልምድ ያለው መሆን እንዳለበት ይገልፃል ነገር ግን እኔ በምሰራበት መስሪያ ቤት እስከ አሁን ሰባት ተቀጥረዋል የተቀጠሩ መሀንዲሶች ግን መስፈርት አያሟሉም ብለዋል።
በተመሳሳይ በቢሾፍቱ አውቶሞቲክ የሚገኙ የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ሰራተኞችም የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የደሞዝ ጥያቄ እንዳላቸው አዲስ ማለዳ ካየቻቸው ማስረጃዎች ለማወቅ ችላለች።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ የህዝብ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ሞላልኝ ከሳቴብርሀን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የቀድሞው ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሪፎርም ስራ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል ብለዋል።
በዚህም የቀድሞው ሜቴክ ደግሞ ራሱን ፈትሾ፣ ራሱን አድሶ ፣ ትርፋማ እና ውጤታማ የልማት ድርጅት ሆኖ በመንግስት እየታገዘ ወደ ሪፎርም ስራ ውስጥ ገብቶ በመስከረም 2013 በሚኒስትሮች ምክር ቤት በአዲስ ደንብ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ በሚል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል ብለዋል።
ወደ ሪፎርም እንዲገባ ገፊ የነበሩት ምክንያቶች በብልሹ አሰራር በኪሳራ ውስጥ የነበረ መሆኑ እንደሆነ ገልፀዋል።
ተቋሙን ተወዳዳሪና ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል የመዋቅር ጥናት ተደርጎ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት (አይፒኤስ) የተባለው መንግስታዊ ተቋም የመዋቅር ጥናት አጥንቶ ወደ ትግበራ ምእራፍ ተገብቷል ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው የደሞዝ ጉዳይ ነው።ያለፉት አመታት ጠባሳዎች ግን ተቋሙን ለኪሳራና ለእዳ ዳርገውት የሄዱ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ማንኛውም በቢዝነስ ፍልስፍና የሚመራ ኩባንያ የክፍያ ሁኔታው ከገቢው ጋር የተመጣጠነ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ተቋማችን ላላፉት አመታት ከገባበት ችግር ሲወጣና ትርፋማነቱን እያረጋገጠ ሲሄድ እንደማንኛውም የቢዝነስ ተቋም ሰራተኞቹን አሁን ካለው የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013



