በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ከመተከል ሸሽተው የገቡ ታጣቂዎች በየእለቱ በንጹሐን ዜጎች ላይ የግድያና የንብረት ዘረፋ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን የአካባቢው ኗሪዎች ለአዲስ ማለዳ አረጋገጡ።
በመተከል በተደጋጋሚ የተከሰተውን የንጹሐን ዜጎች ግድያና መንግሥት በታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተከትሎ ወደ ሆሮ ጉድሩ ወላጋ የሸሹ ታጣቂዎች ከጥር 14/2013 እስከ ጥር 17/2013 ድረስ ባሉት ቀናት ብቻ 10 ሰዎችን እንደገደሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል። ጥር 14/2013 በሻምቡ ወረዳ ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ኹለት ሴቶች በታጣቂዎች ተደፍረው በሕይወት መለቀቃቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል። እንዲሁም ጥር 15/2013 በአመሩ ወረዳ ጉራ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ አምስት ንጹሐን በታጣቂዎች ተገድለዋል ተብሏል።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ ከመተከል ሸሽተው ወደ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ የገቡ ታጣቂዎች ጫጮ በሚባል ጫካ ውስጥ ምሽግ ሰርተው የአካባቢውን ማኅበረሰብ በየእለቱ እየገደሉና እየዘረፉ እንዳሉ እና ታጣቂዎቹ የሰፈሩበት ጫካ ለመዘዋወር ምቹ በመሆኑ በየቦታው እየተዘዋወሩ የአከባቢውን ማኅበረሰብ እንቅልፍ እንደነሱት ኗሪዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
በአከባቢው ኗሪ የሆኑ ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸው እንዳይጠቀስ ያሳሰቡ ግለሰብ “የማኅረሰቡን ጭንቀት የሚረዳ ሕግ ያለ አይመስልም በፈጣሪ ጠባቂነት ነው የምንኖረው” ሲሉ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ዝምታ መምረጡን ገልጸዋል። በመሆኑም በአካባቢው አሳሳቢ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ በመሆኑ የበላይ መንግሥት ከወድሁ ችግሩን እንድቆጣጠርላቸው ግለሰቡ አሳስበዋል።
አዲስ ማለዳ ከኗሪዎች አንደበት እንዳረጋገጠችው በአከባቢው እዛም እዛም የሚፈጠሩ ግድያዎችን በተመለከተ ከዞን አስከ ወረዳ ድረስ የሕዝብ ውይይት ቢደረግም ችግሩን ሊፈታ የሚችል መፍትሔ እስካሁን ድረስ እንዳልተገኘ ነው ነዋሪዎች የሚገልጹት። በሕዝብ ውይይት ወቅት ችግሩን ለማስቀረት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ተግበራዊ እንዳልሆኑም ነው ከነዋሪዎች የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው።
ጫጮ ጫካ ሰፍሯል የተባለው የታጣቂ ኃይል ለአከባቢው ማኅበረሰብ ስጋት እንደሆነ የአካባቢው ኗሪዎች ለመንግሥት አካላት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን የመንግሥት አካላትና በአካባቢው በጸጥታ ሥራ ላይ የተሰማሩ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ምንም ልናደርግ አንችልም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ኗሪዎቹ ተናግረዋል። የአከባቢው የመንግሥት አካላት ችግሩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን በመግለጽ የአከባቢው ማኅበረሰብ እራሱን ከጥቃት እንዲከላከል አሳስበዋል ተብሏል።
የክልሉ ልዩ ኃይል ጫጮ ጫካ የመሸገውን ታጣቂ ኃይል ለመፋለም ሙከራ ቢደርግም ሙከራው አለመሳካቱን ኗሪዎች ጠቁመዋል። በመሆኑም በአካባቢው የተሰማራው ልዩ ኃይል ጫካ የመሸገውን ታጣቂ ለመከላከል የመከላከያ ኃይል ያስፈልጋል የሚል ምላሽ ለኗሪዎቹ እንደሰጣቸውም ኗዋሪዎች ጨምረው ገልጸዋል።
የአከባቢው ኗሪዎች ጫካ የመሸገውን የታጠቀ ኃይል መከላከያ ገብቶ ሰላማቸውን እንዲያስጠብቅላቸው ጠይቀዋል።
እንዲሁም በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ጥቃቶች ከቤት ንብረታቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም በመንግሥት በኩል ምንም አይነት ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ አለመሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። ንብረታቸው የወደመባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መንግሥት ድጋፍ እንዳደርግላቸው ቢጠየቁም ከመንግሥት የተገኘ ድጋፍ ባለመኖሩ በሕዝብ ትብብር እየተረዱ ነው ተብሏል።
አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ በንጹሐን ዜጎች ላይ የግድያ፣ የእገታና እና የንብረት ዘረፋና ቃጠሎ ተግባሮች እንደሚፈጸሙ መዘገቧ ሚታወሰ ነው። ይሁን አንጅ የጥቃቱ ሰላባ የሆኑ ንጹሐን ዜጎች አሁንም ድረስ የሰሚ ያለህ እያሉ ነው።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ምላሽ ለማግኘት ለምክትል ኃላፊ ግዛቸው ገቢሳ ስልክ ብትደውልም ጉዳዩን ከቦታው አጣርተን ምላሽ እንሰጣለን ቢሉም አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ብትደውልም ስልክ አልመለሱም።
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013



