በአገራችን የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ መምህራን የዘጠኝ ወር የተጠራቀመ የደሞዝ ጭማሪ (JEG) መንግስት ቃል በገባልን መሰረት አልተከፈለንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
መንግስት የደሞዝ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ ተመልሶ የሚከፈል (ባክ ፔይመንት) ከአዲስ አበባ ውጪ ላሉ ክልሎች እንዳልተከፈላቸው አዲስ ማለዳ ያየቻቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ መምህር እንደተናገሩት በሐምሌ 1/ 2011 አመት የደሞዝ ማሻሻያ ሲደረግ ማሻሻያ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ መከፈል የነበረበት የዘጠኝ ወር ባክ ፔይመንት አልተከፈለንም ሲሉ ተናግረዋል።
በኮሮና ምክንያት የዘጠኝ ወሩ አሁን አይሰጣችሁም ተብለን ሚያዚያ 2012 ላይ ጭማሪውን የውዝፍ መልኩ ተሰጠን ከግንቦት 2012 አመት ጀምሮ በወር ደሞዛችን ላይ አካተው መክፈል ጀመሩ ነገር ግን ከሀምሌ 2011 አመት ጀምሮ እስከ መጋቢት 2012 አመት ያለው የዘጠኝ ወር ክፍያ አልተከፈለንም ሲሉ ተናግረዋል።
መንግስት ቃል ሲገባልን የዘጠኝ ወሩን ውዝፍ (JEG) በ2013 በጀት አመት ተካቶ ይከፈላችኋል ብሎ ነበር ነገር ግን እስካሁን ምንም ሳይከፈለን የበጀት አመቱ አጋማሽ ላይ ደረስን ብለዋል።
ከሐምሌ 2012 አመት ጀምሮ እየጠየቅን ነገር ግን ምንም አይነት ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ለመምህራን ማህበር እንዲሁም ክልል ፕሬዝዳንት ድረስ በመቅረብ ተናግረናል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ለሚገኙ መምህራን ሙሉ በሙሉ (JEG) ሲከፈል የሌሎች ክልሎች ግን እስከ አሁን አልተከፈለንም ብለዋል።
የላባችንን የለፋንበትን ነው የጠየቅነው ቢያንስ እንኳን ለምን እንዳልተከፈለን እንዲሁም ለምን እንደዘገየ እንኳን ምላሽ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ያላቸውን ቅሬታ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩ ሲሆን መንግስት በአፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል መጠየቃችንን አናቆምም ሲሉም አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ መምህራን የቤት አበል መሻሻልን በተመለከተ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሚያሰሙት መምህራን እደሚሉት ‹‹የምንኖረው አንድ አገር ላይ ነው የምናስተምረው የአንድ አገር ዜጋ ነው እኛም የኢትዮጵያ መምህራን ነን ስለዚህ ይህን አይነት ልዩነት ሊኖረን አይገባም›› ሲሉ ያላቸውን ቅሬታ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አበበ በክልል መምህራን በኩል የሚቀርቡት ጥያቄዎች አግባብነት ያላቸው እንደሆኑ ማህበሩ ያውቃል ብለዋል።
የመምህራን ደሞዝ ለዘመናት መንግስታት ያላዩት ሊፈቱትም ያልፈለጉት ቁጥርን እንደ ሰበብ እያደረጉ ከሁሉም ሴክተር በተለይም ከሲቪል ሰርቪስ ስር ከሚተዳደረው ሰራተኛ በታች ሆኖ ቆይቷል በዚህም የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጥናትና ምርምር ጭምር በማድረግ ከፍተኛ ስራ ሰርቶ የመነሻ ደሞዝ ማስተካከያ እንዲደረግበት ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
ሳይከፈል የቆየውን ክፍያ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው ገንዘብ ሚኒስቴር ነው በዚህም የገቢዎች ሚኒስቴር ገንዘቡን ሲለቅ ቆርጦ ከሚያዚያ 2012 አመት ጀምሮ ያለውን ለቀቀ ለምን እንደሆነ ስንጠይቅ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ስለሆነ ከግሽበት ጋር ተያይዞ ገበያው ላይ የሚፈጥረው ችግር አለ እንደተባሉም ተናግረዋል።
‹‹በመቀጠልም ኮቪድ 19 ወደ አገር መግባቱን ተከትሎ የሚፈጥረው ጫና ለማወቅ ስለማይቻል ፋይናንሱን ይዞ መቆየት እንዳለበት መንግስት ስለወሰነ በኮቪድ ምክንያት ዘገየ›› ሲሉ ተናግረዋል። መስከረም 2013 ላይ የጥያቄውን ይዘን እያንቀሳቀስን ባለንበት ወቅት መንግስት ሌላ የህግ ማስከር ሂደት ውስጥ በመግባቱ ትኩረትን ማግኘት አልቻልንም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ላይ (JEG) መከፈሉን አስታውሰው ሚመለከታቸው አካላትን ስንጠይቅ እንደሚከፈል ነው የሚነግሩን በአንድ ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎች ለአንዱ ተከፍሎ ለአንዱ የሚቀርበት አግባብ እንደሌለ ተናግረዋል ፤በዚህም መቼ እንደሚከፈል ነው እንጂ ያልታወቀው ክፍያው መፈፀሙ እንደማይቀር ጠቁመዋል።
በዋናነት ማህበሩ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የመምህራኑን ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ለማድረግ ከሚመለከተው አካል ጋር እየሰሩ እንደሆነ በዚህም መምህሩ ስራውን እያከናወነ በትግስት ይጠብቅ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በጉዳዩን በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ሰመሪታ እንደተናገሩት ጉዳዩ በበላይ አካላት እየታየ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013



