በአንድ አገር ውስጥ የሕግ መከበር እና ለመኖርም ሆነ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ አገር ትጎለብታለች በማኅበራዊ፣ በምጣኔ ሀብታዊ እና በፖለቲካዊ ረገድም የዕድገት ግስጋሴዋ ሳይገታ እንደተሰለጠ ይቀጥላል። በዚህ ሂደት ታዲያ በርካታ ባለድርሻዎች ቢኖሩም እና በርካታ ስራዎች ለመሰራታቸው ግዴታ ቢሆንም ቅሉ በዋነኝነት ግን አገርን የሚያስተዳድረው መንግስት የሚጠበቅበት ኃላፊነት ሰፊ ነው።
መንግሥትን በአንድ አገር ውስጥ መንግሥት የሚያስብለው ጉዳይ ቢኖር ሕግን አስከብሮ የዜጎችን እኩልነት በሚገባ በማረጋገጥ እና አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነት ሳይኖረው ወይም የተለየ ተጠቃሚ ሳይሆነ በአንድ አገር ሐብት ላይ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። ከዚህም ባለፈ እና በዋናነት የመንገስት ጥንካሬው እና ድክመት የሚለካው ደግሞ የሕግ በላይነትን ባስከበረ እና ባረጋገጠው ልክ እደሚሆን ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በዚህ ሒደት ላይ መንግሥት ሕዝብን ለማስተዳደር አደራ የተጣለበትን ያህል ታትሮ እና ተግቶ በመስራት ሕዝብን የሚያገለግልበት አቅም ማጎልበት ይኖርበታል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ግን መንግስት ሕዝብን ለማገልገል እና ሕግን ለማስከበር በሚንቀሳቀስበት ወቅት ደግሞ በመጀመሪያ የሕግ ማክበሩ እንቅስቃሴ መከበር ያለበት በራሱ በመንግስት መሆን እንዳለበት እና ለሌላውም አርአያ መሆን እንደሚኖርበት አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
ባለፉት ጊዜያት ከመንግስት በኩል የሚደረጉ ድርጊቶች በእርግጥም ሕግን የሚጻረሩ እንደነበሩ መንግሥትም አውቆ በይፋ የተናገረባቸው እንደነበሩ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ አካሔዶች ከለውጡ መንግስት ወዲህም በሰፊ ሲከናወኑ እና ሲታዩ ይስተዋላል። የተፎካካሪ ፓርቲዎችን መግለጫ ከመከልከል እስከ ጋዜጠኞች እስር እና እንግልት ድረስ በመንግስት በኩል ሲፈጸሙ መታየታቸው ሕግን በመጣስ መንግስትም ተሳታፊ እንደሆነበት ማሳያ እንደሆነ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።
በቅርቡ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ጠቅላይ ሚንስትሩን እና መንግስታቸውን ለመደገፍ በሚል ሰላማዊ ሰልፎች መካሔዳቸው የሚታወስ ነው። ይህ ሒደት በየትኛውም መስፈርት የሚደገፍ እና ሰዎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ዲሞክራሲያዊ መብታቸው መሆኑን ማሳያ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ትስማማበታለች። ይሁን እንጂ የሰላማዊ ሰልፉ የተካሔደበት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የባልደራስ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ከመንግስት ፈቃድ መከልከሉ ከታወቀ በጥቂት ቀናት ልዩነት መሆኑ ደግሞ በእርግጥም ትዝብት ላይ የሚጥል እና በእኩል ፓርቲዎች እንዳይስተናገዱ የተደረገበት አሰራር ነው ብላም አዲስ ማለዳ ታስባለች። ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ በጤና ሚኒስቴር በኩል የተላለፈውን የኮቪድ 19 ለመቆጣጠር ወጣውን የማስክ ማድረግ እና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን በሰልፉ ላይ ካለመታየታቸውም ባለፈ ጭራሹኑ በተገላቢጦሽ በብዙ መቀራረብ እና መገፋፋት ሰልፉ ሲደረግ የተስተዋለበት አጋጣሚም ነበር። ይህ ደግሞ መንግሥት በአንድ በኩል ሕግን ያወጣል በሌላ በኩል ደግሞ ራሱኑ ሕጉን ራሱ መንግስት ሲጥሰው ይታያል።
በዚህ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ እና የተደረገውን የድጋፍ ሰልፍም ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ምንም ነገር ሳይናገሩ ነገር ግን በማድነቅ እና ምስጋናቸውን በመቸር ነበር ያለፉት። ‹‹በመላው ኦሮሚያ ስለተደረገው የአብሮነት ድጋፍ ድምጽ ከልብ አመሰግናለሁ። የመንግስት ልዩ ተልዕኮ ህዝብን ማገልገል ብቻ ነው ፤ በየደረጃው ያለን የህዝብ አገልጋዮች ከእንደዚህ አይነት ድጋፍ የምንማረው እና መገንዘብ ያለብን ሀላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ የህዝብ ጥሪና አደራ እንዳለብን ሊሆን ይገባል። ዛሬ ለታየው እና ለነበረው ሰፊ ንቅናቄ መላው የኦሮሚያ ክልል ነዋሪን ከልብ አመሰግናለሁ››። የሚል ጽሑፍ ነበረው። ነገር ግን በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆነ ሌሎች ሰልፍ በተካሔደባቸው ከተሞች ያሉ መንግስታዊ መዋቅሮች ስለ ኮቪድ የተላለፈውን በራሱ በመንግስት የተደነገገውን ሕግ ማስከበር እና እንዲከበር መልዕክት ማስተላለፍ እንደነበረባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ለምርጫ እየተዘጋጀ ያለን አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በአደባባይ ሲነቀፍ እና በአንዳድ መንግስት ባለስልጣናትም ላይ ሲንቋሸሽ እና ሲፈረጅ መታየቱ እንዲሁ መንግስት ሕግን ጥሷል ለማለት አዲስ ማለዳ ትደፍራለች። በዚህም ተነስቶ በቅርቡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድም መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። በመግለጫውም ‹‹ ቦርዱ ሠልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በዐዋጁ አንቀጽ 132 ንዑስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ሕግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነፃነት እንዳያሰራጩ ሥጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የሥነ-ምግባር ጥሠት ፈጽሞ አግኝቶታል። ከዚህም በተጨማሪ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሠነድ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሠረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር ነው። ይህ ተግባር በተለይ ቦርዱ የመጨረሻ የጊዜ ሠሌዳ አውጥቶ የምርጫ ተግባራት በይፋ መፈጸም ከጀመረ በኋላ በምንገኝበት የምርጫ ወቅት መከሠቱ በምርጫ ውድድር ላይ ፓርቲዎች በዕኩልነት የመወዳደር መብታቸውን ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ቦርዱን በእጅጉ አሳስቦታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲ አመራሮች እና በየአስተዳደር ዕርከኑ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሣተፍ እንዲቆጠቡ ያሳውቃል። ለወደፊትም በተመሳሳይ በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ-ምግባር ሕግ 1162/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሠረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ የንግግር እና ሌሎች ለሕዝብ የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከ ዕጩ መሠረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል።›› ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።
ምንም እንኳን ለውጡ የተቋም መገንባት ሂደቱን በምርጫ ቦርድ ግብረ መልስ ለማየት ቢቻልም ነገር ግን አሁንም መንግስት ሕግን ከመጣስ እና ካለመተግበር ሊታረም እንደሚገባ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች። በቀጣይም ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ ይሆን ዘንድ እንደተባለው በሚገባ እየተሰራ መሆኑን ሲገለጽ ቢታይም ከመንግስት በኩል ይበል የሚያሰኝ ሕግን ማስከበር እና የማክበር ሁኔታ እንዲፈጠርም አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች። ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ አካሔዶች ወደ አልተፈለገ አካሔድ እንደሚያመሩ እና ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍሉናልም ስትል ታስታውቃለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013


