የፌደራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ ፈጠራ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባካሄደው ውይይት ስድስት ሚሊዮን የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቋል፡፡
በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በበጀት ዓመቱ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች፤ በግማሽ ዓመቱ ደግሞ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ገልፀዋል።
ዕቅዱ በዘርፎች ሲከፋፈል በግብርና 44 በመቶ፣ በኢንዱስትሪ 32 በመቶ፣ በአገልግሎት 24 በመቶ እንደሆነ ዘርዝረዋል። ከዚህም ውስጥ 80 በመቶው ቋሚ፣ 20 በመቶ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መሆኑንም አስረድተዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራው የጾታ ስብጥር ለወንዶችና ለሴቶች እኩል 50 በመቶ መሆኑንም አክለዋል። ከዚህ አንጻር በአገራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር የዓመቱን ዕቅድ 56 በመቶ መፈፀም ተችሏል ብለዋል።
አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 49 በመቶ ጭማሪ አለው ተብሏል። አፈጻጸሙ በዘርፍ ሲታይም በግብርና 30 በመቶ፣ በኢንዱስትሪ 26 በመቶ፣ በአገልግሎት ደግሞ 44 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ተብራርቷል።
ከዚህ ውስጥ ቋሚ የስራ ዕድል 62 በመቶ ሲሆን ጊዜያዊ 38 በመቶ እንደሆነም በሪፖርቱ ተመላክቷል። በጾታ ስብጥር በወንዶች የዕቅዱ 65 በመቶ ሲሳካ በሴቶች 35 በመቶ ማሳካት ተችሏል።
የዕቅዱ አፈጻጸም በአጠቃላይ ሲታይ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ከዕቅድ በላይ ማሳካታቸው ተገልጿል። የደቡብ፣ የሲዳማና የሀረሪ ክልሎች ከፍተኛ አፈጻጸም ሲያስመዘግቡ የድሬዳዋ አስተዳደርና የሱማሌ ክልል መካከለኛ አፈጻጸም ያሳዩ ናቸው። የቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ የጋምቤላና የአፋር ከልሎች ደግሞ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ መሆናቸው ተገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013



