የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

0
1300

በቀጣዩ ግንቦት ወር ለሚካሄደው የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል ህዝበ ውሳኔን ለማካሄድ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማስረሻ በላቸው ተናገሩ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ባቀረቡት የክልልነት ጥያቄ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቦች ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ውሳኔ ማስተላለፉንና ውሳኔውንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈፅም መወሰኑን አስታውሰው ህዝበ ውሳኔው በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወንና በቅድመ ህዝበ ውሳኔ፣ በህዝበ ውሳኔ አሰጣጥና ከድህረ ውሳኔ በኋላ የሚከናወኑ ተግባራትን በአግባቡ እንዲመራ ከ6 መዋቅሮች፣ አምስት፣ አምስት በድምሩ 30 አባላት መመረጣቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 13ቱ አባላቱን በመወከል እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በህገ-መንግስት ዝግጅት፣ በህዝብ ግንኙነት ስራ፣ በሎጎ፣ በባንዲራ፣ በቋንቋ፣ በልማት ዕቅድ ዝግጅት፣ ህዝበ ውሳኔው ከተካሄደ በኋላም በአካባቢው ካሉ ማህበረሰቦች ጋር በባህል እና ነባሩን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግራትን የሚያከናውኑ አምስት ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ወደ ስራ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ኮሚቴው የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልነት ጥያቄ ሰላማዊ የሆነ ህዝበ ውሳኔ እና ሽግግር እንዲኖር ለማስቻል የተዋቀረና የፌደራል አካላትን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በቦርዱ በኩል ህዝበ ውሳኔው ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫው ጋር ለማካሄድ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ህዝበ ውሳኔ ከመካሄዱ በፊት ለህዝቡ በቂ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ በህዝበ ውሳኔው ላይ ቅር የሚሰኙ አካላትን የማወያየትና ውሳኔያቸውንም ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ፣ በህዝበ ውሳኔ ጊዜ የአስተዳደር ወሰን ችግሮ እንዳይከሰቱ ከወዲሁ መስራት እና ህዝቡ የተስማማባቸውን ምልክቶች ቢያንስ በሦስት አማራጮች አዘጋጅቶ ማቅረብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልነት ጥያቄ ህዝቡ ረዘም ላሉ ዓመታት ሲያነሳው የነበረ በመሆኑ በህዝብ ዘንድ ቅሬታ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here