ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ምስራቅ ሪጅን በአዳማና አካባቢዋ በሚገኙ ከተሞች የዘረጋውን የ4ጂ ሞባይል ኔትዎርክ በዛሬው እለት ሐሙስ የካቲት 11 ቀን 2013ዓ.ም አስመረቀ።የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ ኔትዎርክ በአዳማና፤ ሞጆ ፤ቢሾፍቱ ፤ገላንና ዱከም ከተሞች ፈጣን የሞባይል ድምጽና ዳታ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።
በአዳማ ሀይሌ ሪዞርት በተካሄደው የምርቃት ስነ-ስርአት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ የተዘረጋው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ ኔትዎርክ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ባለበት የደቡብ ምስራቅ ሪጅን የተቀላጠፈ የሞባይል ድምጽና የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በተለይ ከፍተኛ የሞባይል ዳታ ፍላጎት ባለበት አዳማ ከተማ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።
የአዳማ ከተማ ሞባይል ኔትዎርክ በመጀመሪያ የገነባው ኤሪክሰን ኩባንያ ሲሆን ከረጅም ጊዜ ጥረት በኋላ የማስፋፊያ ስራውን የቻይናው ዜድ.ቲ.ኢ ኩባንያ እንዳከናወነው ታውቋል።የአዳማ ከተማ ሞባይል ኔትዎርክ በተለይ የዳታ ትራፊክ መጨናነቅ እንደነበረበት ተገልጿል።የኢንዱስትሪ ዞን በሆኑት ገላንና ዱከም እንዲሁም የመዝናኛ እና ስብሰባ ማእከል በሆኑት ቢሾፍቱ እና አዳማ ከተሞች የተዘረጋው 4ጂ ኔትዎክ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተነግሯል፡
ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013



