የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በምርጫ ቅስቀሳ ባሳለፍነው የካቲት 8/2013 በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው። ከምርጫ ቅስቀሳ ጎን ለጎን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የተሰጣቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የእጭዎች ምዝገባ እንዲያካሂዱ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸዋል። ለእጩ ምዝገባ ቀነ ገደብ ያስቀመጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከየካቲት 8/2013 አስከ የካቲት 21/2013 መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ይሁን እንጂ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የእጭዎች ምዝገባ ለማድረግ በአንዳንድ አካባቢዎች ተግዳሮት አንደገጠማቸው ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ ካነጋገራቻው ፓርቲዎች ውስጥም እጩዎች ለማስመዝገብ አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟቸው እጩዎች ሳያስመዘግቡ የቀሩ ፓርቲዎችም አሉ።
የእጩ ምዝገባና የጊዜ ግብ ግብ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የእጩዎች ምዝገባን እያከናወነ እንዳለ ይታወቃል። በዚህም መሰረት የመጀመሪያ ዙር የእጩ ምዝገባ የሚከናወንባቸው ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ተለይተዋል።
ቦርዱ እጩዎች ምዝገባ በኹለት ዙር እንዲያካሂድ የተገደደው ክልሎች ማዘጋጀት የሚገባቸውን ቢሮዎች በወቅቱ ባለማቅረባቸው ነው። በዚሁ መሰረት የመጀመሪያ ዙር እጩ የሚመዘገብባቸው ቦታዎች የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ የድሬደዋ ከተማ መስተዳድር፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል፣ የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል እና ሃሪሪ ብሔራዊ ክልል፣ ለእጩዎች ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ከካቲት 8 እስከ 21/2013 ድረስ እንደሚከናወን ማሳወቁ ይታወሳል።
ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም የምርጫ ክልል ቢሮዎች ለመከፈት በመዘግየታቸው፣ የትራንስፓርት መጓተት የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ላይ የምዝገባ ቀንን በማራዘሙ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች እጩዎችን ለመመዝገብ ችግር ስላጋጠመን ይራዘምልን ብለው ጠይቀዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከላይ የተጠቀሱትን አሳማኝ ምክንያቶች በማየት የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ በጀመሩት ከላይ በተጠቀሱት ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ላይ የሚካሄደው የእጩዎች ምዝገባ ለአራት ቀናት ያህል እስከ የካቲት 25/2013 ድረስ ማራዘሙ የሚታወስ ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ተግባራትን ማከናወን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል የምርጫ ክልል ቢሮዎች ዝግጅት መዘግየት እና አስፈጻሚዎች ሰልጥነው ከተሰማሩም በኃላ ቢሆን ቢሮዎች ዝግጁ ሆነው ባለመገኘታቸው የቢሮ መከፈት መዘግየቱ፣ በተወሰኑ ክልልሎች አስፈላጊው ቢሮዎች ተዘጋጅተው ባለመጠናቀቃቸው የእጩዎች ምዝገባ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት መጀመር አለመቻሉ እና ለኹለት ዙር መከፈሉ፣ ለምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት የትራንስፖርት እጥረት እና የገለልተኛ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሂደት ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጊዜ የሚወስድ ተግባር መሆኑ ለቀኑ መራዘም ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ቦርዱ የሰጠው ተጨማሪ የእጩ ምዝገባ ጊዜ ባሳለፍነው ሀሙስ ተጠናቋል። ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቸ፣በአንዳንድ አካባቢዎች እጩዎችን በወቅቱ ለማስመዝገብ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። በዚህ የተነሳም እጩዎችን ማስመዝገብ ያልቻሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዳሉ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
ፓርቲዎቹ እጩዎችን ቦርዱ ባስቀመጠቀው የጊዜ ገደብ ለማስመዝገብ አስቸጋሪ ከሆነባቸው ችግሮች መካከል የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ገብቶ የእጩ ምዝገባ ለማድረግ በመቸገራቸው አንደሆነ ይናገራሉ።
አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) አንዱ ነው። የኢዜማ የኮሙኑኬሽን ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዘላለም ወርቅአገኘሁ ለአዲስ ማለዳ አንዳሉት ከሆነ ኢዜማ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እጩዎን አለማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ፓርቲው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በሶስት የምርጫ ጣቢያዎች እጩዎችን ለማቅረብ መቸገሩን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ሌላኛው ፓርቲው እጩዎችን ማስመዝገብ ያልቻለበት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ሲሆን ፓርቲው በዚህ አካባቢ አስር እጩዎች ማቅረብ እያለበት ማቅረብ የቻለው አራት ብቻ ነው። ይህ ማለት ማቅረብ ከሚገባው አስር እጩዎች አብላጫውን ስድስት እጩዎች ሳያቀርብ ቀርቷል። በእነዚህ አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝና ምቹ ባልሆነበት ሁኔታ በተቀመጠው ጊዜ እጩ ማስመዝገብ አስቸጋሪ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ያሳለፍነውን ሳምንት በእጩ ምዝገባ እንዳሳለፉት ተናግረዋል። ጎን ለጎን የምርጫ ቅስቀሳ መካሄድ የሚቻልበት ጊዜ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ትኩረታቸውን እጩዎችን ማስመዝገብ ላይ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ትኩረቱን የእጩዎች ምዝገባ ላይ በማተኮር የምርጫ ቅስቀሳውን በጥልቀት እንዳልጀመረ አስታውቋል። የፓርቲው ሊቀመንበር አብዱልቃድር አደም ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት ከመንግሥት ጋር በቅንጅት ሰለምንሰራ እስካሁን የገጠመን ችግር የለም ብለዋል። ፓርቲው የእጩ ምዝገባ ላይ ትኩረት ቢደርግም ወደፊት የምርጫ ቅስቀሳውን እንደሚደርግ ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለማከናወን ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ በተሰጣቸው የጊዜ ሰሌዳ የእጩ ምዝገባ እያካሄዱ መሆኑን አዲስ ማለዳ ወደ ሕትመት እስከገባችበት ሰዓት ድረስ ለማረጋጋጥ ችላለች።
የምርጫ ቅስቀሳ እንቅፋቶች
የምርጫ ቅስቀሳቸውን ከየካቲት 8/2013 በይፋ ከጀመሩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ኢዜማ አንዱ ነው። ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳውን ከሌሎች ፓርቲዎች በተሻለ እያካሄደ እንደሆነ የሚናገሩት የኢዜማው ዘላለም ናቸው።
በኮንሶ የታሰሩት የፓርቲው አባላት 11 መሆናቸው ዘላለም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የመንግሥት አካላት በኢዜማ አባሎች ላይ ባደረጉት ድብደባ ጉዳት የደረሰባቸው አባላቶች መኖራቸውን ዘላለም አክለው ገለጸዋል።
በሌላ በኩል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በጎንደር የምርጫ ቅስቀሳ ችግር አጋጥሞት እንደነበር መግለጹ የሚታወስ ነው። ችግሩ የተፈጠረው በጸጥታ አካላት ከሕግ የወጣ ድርጊት ነው ሲልም መኢአድ ገልጿል። የጸጥታ አካሉ መኪና እንዳይንቀሳቀስ አድርጓል፣ ፈቃድ አልተሰጣችሁም በሚል እገዳ አድርጓል ብሏል ፓርቲው።
ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት በርካታ ፓርቲዎች የቅስቀሳ ሂደት ላይ ያጋጠማቸውን ችግር ተናግረዋል። የእናት ፓርቲ የሀዋሳ ከተማ እጩ ተወዳዳሪ መንገድ ላይ ማስፈራሪያ እየደረሰባት ራሷን ማግለሏን ፓርቲው አስታውቋል።
በመርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፓርቲዎች የገጠማቸውን ተግዳሮት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በሙሉ አቅም ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ስላልገባን ጎልተው የሚወጡ ችግሮች አልገጠሙንም ብለዋል። ይሁን እንጅ የምርጫ ቅስቀሳቸውን የጀመሩ አንዳንድ ፓርቲዎች ተራ ማስፈራሪያ የሚመስሉ ነገሮችም መታዘባቸውን ጠቁመዋል።
በመርጫ ቅስቀሳ ጅማሮ ወቅት የታዩ ችግሮችን ከሥር ከመሰረቱ ማስቀረትን እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል።
መንግሥት በምርጫ ወቅት የለበት ኃላፊነት እንደ ፓርቲ ከመወዳደር ባለፈ ለተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ የምርጫ ሜዳ መፍጠር ነው። ከዚህ አንፃር በመጠኑም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢ የታዩ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበሩ አብዱልቃድር ጠቁመዋል።
ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም እርስ በእርስ መደጋገፍና ተባብሮ የምርጫ ሜዳውን ምቹ ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልጹት አብዱልቃድር ፓርቲዎች ካልተባበሩና የጎንዮሽ መጎሻሸም ውስጥ ከገቡ የምርጫ ሜዳው ላይ እክል ሊፈጠር ይችላል ይላል። በመሆኑም የፓርቲዎች መተባበር በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከታየ የምርጫ ሂደቱና ውጤቱ በጥሩ ሁኔታ የመጠናቀቅ እድል እንደሚኖረው አክለው ጠቁመዋል።
የኢዜማው የኮሙኑኬሽን ኃላፊው ዘላለም በበኩላቸው በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰለጠነ መንገድ ሀሳባቸውን ለህዝብ አንድሸጡ መፍቀድና ምቹ ሁኔታዎችን እየከፈቱ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን በትኩረት አንስተዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013



