ኦፌኮ ጥያቄዎቼ ካልተመለሱልን በምርጫ አልሳተፍም አለ

0
573

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) የጠየቃቸው ጥያቄዎች ምላሽ ካላገኙ በመጪው አገራዊ ምርጫ እንደማይሳተፍ የፓርቲውን ሊቀመንበር መረራ ጉዲናን(ፕ/ር) አስታወቁ፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ባሳለፍነው ሳምነምት የጠየቋቸው ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ሁኔታ በምርጫው እንደማይሳተፉ፣ ነገር ግን ጥያቄዎቹ ምላሽ ካገኙ በምርጫ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የፓርቲው ሊቀመንበር መረራ እንዳሉት ከሆነ ፓርቲያቸው በተደጋጋሚ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ስላላገኙ እስካሁን ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አላስመዘገበም።

ጥያቄዎቹ ምላሽ ካገኙ በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት መረራ ገዢው ፓርቲ አሁን የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች በአንድ ቀን፣ ወይም በኹለት ቀን መፍታት ይችላል። ገዢው ፓርቲም ሆነ ምርጫ ቦርድ ያንን እርምጃ ከወሰዱ ምርጫውን የማንቀጥልበት ምክንያት ብለዋል፡፡

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጥሩነህ በበኩላቸው “የተሻለ አሰራር ከመጣ ነገም ቢሆን ተሳታፊዎች ነን፣ የጠየቅናቸው ጥያቄዎች ከተመለሱ እኛ ምን ችግር አለብን? እንሳተፋለን። ያልነው አንሳተፍም ሳይሆን ተገፍተን ወጥተናል ነው፣ ለመሳተፍ ብቻ አይደለም የምንፈልገው፣ የኛ ሀሳብ አሸናፊ ከሆነ አሸንፈን አገር ለመምራት ነው” ሲሉ ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደትና የቴክኒክ ሥራዎችን የተመለከተ ውይይት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አድርጓል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንትና የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደትና የቴክኒክ ሥራዎችን የተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መገናኛ ብዙኃን በተገኙበት ውይይት አድርጓል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በተገኙበት የተደረገው ውይይት በዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ላይ ያጋጠሙ የተለያዩ ግኝቶች የቀረቡበት ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደት የቀረቡ አቤቱታዎችና የተሰጡ መፍትሔዎች በዝርዝር በቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ቀርበዋል።

ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት ላይ አቤቱታዎች እንደቀረቡ በመጥቀስ ለገዥው ፓርቲ መመሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ እንዳገኙት የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ገዥው ፓርቲ ከቀድሞ ልማዶች መላቀቅ እንደሚገባው ገልጸዋል። ፖለቲካ ፓርቲዎችም ማንኛውም ዕክል ሲገጥማቸው በሰዓቱ ለቦርዱ ቢያሳውቁ በጊዜ መልስ እየሰጡ ለመሄድ እንደሚያስችል በማሳሰብ፤ ፓርቲዎቹ ቦርዱ ካዘጋጀው የጥሪ ማዕከል በተጨማሪ ይቀለናል በሚሉት መንገድ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡ ቦርዱ አፋጣኝ መልስ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል። የቦርድ ሰብሳቢዋን ሀሳብ የተጋሩት ተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ መፍትሔ አገኝተንባቸዋል ያሏቸውን አካባቢዎች በመግለጽ ያመሰገኑ ሲሆን፤ አሁንም ከፍተኛ ሥጋት አሉባቸው ያሏቸውን ቦታዎች በመግለጽ በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠማቸውን እና መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮችን፣ የምረጡኝ ዘመቻ ለማድረግ የሚያስቸግሩ ያሏቸውን ሁነቶች አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ የቦርዱ የመረጃ ማዕከል በዕጩዎች ምዝገባ ሂደት ውስጥ ያለው አሠራር በቦርዱ የኮሚኒኬሽን ክፍል ባልደረባ ሲቀርብ፤ የቦርዱ የአጭር መልዕክት መቀበያ የአሠራር ሥርዓት ደግሞ በቦርዱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ባልደረባ ቀርቧል። ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ቦርዱ ጊዜው የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም ዘመናዊ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያደርገውን ጥረት ቢያደንቁም በአፈጻጸም ወቅት ግን የተለያዩ የቴክኒክ ዕክሎች እየገጠሟቸው እንዳለ አሳስበዋል።

በጉዳዩ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ መልስ የሰጡበት ሲሆን፤ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ክፍተት በሚኖር ጊዜ መረጃውን በጽሑፍ በመሠነድ ሥራው እንደሚከናወን በማድረግ ወደ ዲጂታል ሲስተም ውስጥ የማስገባት ሥራውን በማዘግየት ሊስተናገዱ የሚችሉበት አማራጭ እንዳለ ጠቁመዋል። ከተሣታፊዎች ለተነሡት ጥያቄዎች ከቦርዱ ዋና ኅላፊ ብርቱካን ሚደቅሳ መልስ ተሰጥቶበታል።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here