በአዲስ አበባ ከሚገኙ መንገዶች የእግረኛ መንገድ ያላቸው 35 በመቶ ብቻ ያህሉ ናቸው

0
1266

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ መንገዶች መካከል 35 በመቶ የሚሆነው መንገድ ብቻ የእግረኛ መንገድ እንዳለው የከፍተኛ ትምህርት የዘርፉ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር በለጠ እጅጉ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር የካቲት 25 በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ባደረገው ውይይት መድረክ ላይ ጥናታቸውን ያቀረቡት በለጠ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ መንገዶች የእግረኛ መንገድን አካተው የተሰሩት 35 በመቶ ብቻ መሆናቸውን በጥናታቸው ወቅት ማግኘታቸውን እና ይህም የትራፊክ አደጋውን ለማበራከት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የ2011 በጀት ዓመት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሪፖርት እንደሚያሳየዉ በአጠቃላይ አምስት ሺሕ 784 ኪሜ ርዝመት ያላቸው መንገዶች የተገነቡ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኹለት ሺሕ አምስት መቶ 39 ኪሜ ብቻ የአስፋልት መንገዶች እንደሆኑና ከአስፋልት መንገዶች 35 በመቶ ብቻ የእግረኛ መንገዶች ሲኖራቸዉ እነርሱም ከፍተኛ ጥገና የሚፈለጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የትራፊክ አደጋን ከሚያስከትሉ ጉዳዬች መካከል የእግረኛ መንገድ አለመኖር ከፍተኛውን ሚና እንደሚወስድ በዚህም በተለያዩ ጊዜ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል 84 በመቶ የሚሆነው የሚደርሰው አደጋ እግረኞች ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህም በ2010 በተሰበሰበ መረጃ መሰረት ከደረሰ የትራፊክ አደጋ ሦስት ሺሕ አራት መቶ 59 መካከል በእግረኞች ላይ የደረሰ አደጋ ኹለት ሺህ ዘጠን መቶ 14 እንደሆነና ከዚህ እግረኞች በእግረኛ መንገድ ላይ ሲጓዙ አራት ነጥብ አራት በመቶ ፣ የእግረኛ መንገድ በሌለበት ግራቸውን ይዘው ሲጓዙ 10 በመቶ እንዲሁም የእግረኛ መንገድ በሌለበት የመንገዱን ቀኝ ጠርዝ ይዘው በመጓዛቸው የደረሰ አደጋ 4 አራት ነጥብ ስምንት በመቶ መሆኑንም በጥናቱ አመላክተዋል።

እንደ ጥናት አቅራቢው ገለፃ ለአደጋዎች መበራከት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የመንገድ ደህንነት የተጠበቀ ባለመሆኑ ፣ ጠንካራ የሆነ የሚመራ ተቋም አለመኖር እንዲሁም የክትትል ስራ ድክመት እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህም የሚመለከተው ባለድርሻ አካል በሙሉ ይህንን ጉዳይ በተለይም እግረኞች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ከመቀነስ አኳያ በህብረት ሊሰራ እንደሚገባ እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ድርጅቶች ጋር በጥምረት ሊሰራ እንደሚገባም አክለው አስታውቀዋል።
ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሊድ መሀንዲስ የሆኑት ሂሩት ተከተል እንደተናገሩት በዋናነት ለትራፊክ አደጋም ሆነ ለመንገድ ደህንት ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራ ተቋም እንደሌለ አስታውቀዋል።

እንደ ሂሩት ገለፃ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ያለውን ስልጣን እንዳይጠቀምም ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ይጠቅሳሉ ፤ ለአብነትም በመንገድ ዳር ላይ የሚደረጉ ንግዶች በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሆነም አክለው ተናግረዋል።
በአንድ ወገን ወረዳ ላይ ያሉ አመራሮች በጥቃቅንና አነስተኛ ስም የእግረኛውን መንገድ በመከለል እንዲሁም ቁጥሮችን በመፃፍ ለነጋዴዎች ይሰጡዋቸዋል ብለዋል። ይህንንም ተከትሎ እንደ ሂሩት ገለጻ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ሄደው እንዲያነሱ በሚጠይቁበት ጊዜ ህጋዊ መሆናቸውን የሚያሳይ ወረቀት እንዳላቸው እንደሚሰጡዋቸውም አክለው አስታውቀዋል።

በዚህም ሁሉን በተገቢው መልኩ የሚመራ ተቋም እንደሚያስፈልግ በተለይም የእግረኛ መንገድ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት የሚፈልግ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።
መንገዶች ከተሰሩበት አላማ ሌላ ለሌላ አላማ እየዋሉ ነው ያሉት የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መንገድ ትራፊክ ቁጥጥር እና ኩነት አስተዳደር ዳይሬክተር ቢኒያም ጌታቸው በተለይ እግረኞች ለትራፊክ አደጋ እንዲጋለጡ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል ህገወጥ የመንገድ ላይ ንግድ እየተስፋፋ መምጣት እና የእግረኞች መንገድ በተለያዩ ቁሳቁሶች የሚዘጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ ቢኒያም ገለፃ የትራፊክ አደጋው እንዲቀንስ ከተፈለገ ሁሉም የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን መወጣት አለበትም ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የመንገድ ደህንነት ትምህር እና ግንዛቤ ዳይሬክተር ዮሀንስ ለማ እንደተናገሩት የቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ የመንገድ ትራፊክ አደጋ በከፍተኛ መልኩ ተጎጂ እየሆነ ያለው እግረኛው በመሆኑ ለዚህም ለምድን ነው የእግረኛን መንገድ ለእግረኛ መጠቀም ያልቻልነው የሚለውን የምናይበት ነው ብለዋል።

በዚህም ሁሉም ተቋማት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ወስዶ እንዲሰራ እና በቀጣይም በአገራችን ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና ያለው ነው ብለዋል።
በ2013 የመጀመሪያው ግማሽ አመቱ ውስጥ በአገር ዓቀፍ ደረጃ 20ሺሕ ስድስት መቶ 72 የመንገድ የትራፊክ አደጋ የደረሰ ሲሆን አንድ ሺሕ ስምንት መቶ ዜጎች በትራፊክ አደጋው ህይወታቸውን አጥተዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here