የጸጥታ ችግር ባለበት አካባቢ ፈተና ለወሰዱ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጤት ታሳቢ እንደሚደረግላቸው ተገለጸ

0
986

ባሳለፍነው ሳምንት ከየካቲት 29 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2/2013 የተሰጠው የ2012 አገር ዐቀፍ የ12ኛ ክፈል ተማሪዎች ፈተና የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢ ለተፈተኑ ተማሪዎች ውጤታቸው ታሳቢ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ2012 አገር አቀፍ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ ባሳለፍነው ሀሙስ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች አገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ከተቀረው ኢትዮጵያ ክፍል ተማሪዎች ጋር እኩል ሊመዘኑ እንደማይችሉ እና ውጤታቸው ላይ ታሳቢ እንደሚደረግ ነው የትምህር ሚኒስቴር ሚንስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ) ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።ሚንስትሩ አያይዘውም በሰጡት ምላሽ በመተከልና በትግራይ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰለባ ሆነው ለተፈተኑ ተማሪዎች ውጤታቸው ታሳቢ ተደርጎ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም ተማሪዎቹ የደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና ታሳቢ ተደርጎ ውጤታቸው በልዩ ሁኔታ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

የነበሩበት የጸጥታ ሁኔታ ውጤታቸው ታሳቢ የሚደረግላቸው ተማሪዎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተመለከተውና ትኩረት የሰጠው ጉዳይ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በጸጥታ ችግር ምክንያት በስነ ልቦና ጫና ውስጥ ሆነው የተፈተኑ ተማሪዎች ውጤት ታሳቢ እንድደረግ በከፍተኛ አመራሮች ጭምር ታሳቢ ተደርጎበታል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ሚኒስትሩ በመግለጫው ላይ የፈተናው ስኬት ብለው የጠሩት ጉዳይ ላለፉት ሦስት ወራት ያክል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሕግ ማስከበር ሂደት የተለያዩ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በተሳካ ሁኔታ ፈተና መሰጠቱ ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የጸጥታ ችግር ባለበት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተከል ዞን ፈተናው ሙሉ በሙሉ ተሳክቷል ብለዋል፡፡ እንዲሁም በሁመራ፣ በወልቃይት፣ በራያ አከባቢ በየትምህርት ቤቶቹ በ18 የፈተና ጣቢያዎች ፈተና ተሰጥቷል ተብሏል፡፡ በትግራይ ክልል በመቀሌ ዩኒቨርስቲ፣ በአክሱም የኒቨርስቲና ካምፓስ፣ በሽረ ካምፓስ እና በራያ ዩኒቨርስቲ ተሰጧል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

የጸጥታ ችግር ካለባቸው መተከል ዞንና ትግራይ ክልል ወደ አዲስ አበባ የገቡ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ተጫሪ የፈተና ጣቢያ ተዘጋቶ ፈተናውን ወስደዋል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 መግባቱን ተከትሎ ፈተናው ስከተሰጠበት አስካለፈው ሳምንት ድረስ ተራዝሞ የነበረው የ2012 አገር አቀፍ የ12 ክፍል ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የሁሉም ድርሻ ከፍተኛ እንደነበረ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ እገዛ ላደረጉ አካላት፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

እንደ አገር የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ የትምህርት ጊዜ ወደ ኋላ እንዳይቀር እና የተማሪዎች የትምህርት ዘመን እንዳይራዘም መደረጉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በዘንድሮው የፈተና አሰጣጥ ስርቆትን ለማስቀረት 8 ፈተናዎችን በ 32 ስብጥር በማድረግ ኩረጃ እንዳይኖር መደረጉም በመግለጫው ተነስቷል።

የአገር አቀፍ ፈተና ውጤቱም በቅርብ ጊዜ እንደሚገለፅ እና ተፈታኞችም በዚሁ ዓመት ወደ ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ ተገልጿል። ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨረስቲ በፍጥነት ለማስገባት በአጭር ጊዜ ውጤት እንደሚገለጽ የጠቆሙት ሚኒስትሩ የተማሪዎች የትምህርት ዘመን እንደማይዘነፍ ጠቁመዋል፡፡

በተሰጠው የ2012 አገር አቀፍ ፈተናው ከ358 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ፈተና መውስዳቸውን ሚኒስትሩ ገልቷል፡፡ በ2011 አገር አቀፍ ፈተና የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ቁጥር 319 ሺሕ 264 መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here