ንግድና ኢንዱስትሪ 65 ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

0
1130

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጥራት ችግር የታየባቸውን እንዲሁም ከተፈቀደላቸው ውጪ ሲሰሩ የተገኙ 65 ድርጅቶችን በያዝነው በጀት አመት ሰባት ወር ውስጥ ንግድ ፈቃዳቸውን ማገድ እንደሁም የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል።
በዚህም ከ 65 ድርጅቶች ውስጥ 31 የሚሆኑ ከጥራት ጋር በተያያዘ ሲሆን 35 የሚሆኑት ደግሞ ከተፈቀደላቸው ውጪ ሲሰሩ የተገኙ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ከድርጅቱ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ እሸቴ አስፋው እርምጃ የተወሰደባቸው በ2013 በጀት አመት በሰባት ወራት በተደረገ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ ጥራትን በማጓደል እንዲሁም ያልተፈቀደላቸውን ስራ ሲሰሩ የተገኙ ድርጅቶች መሆናቸውንም ሚኒስቴሩ ተናግረዋል።
በዚህም አምራች ኃይሉ ከትርፍ ይልቅ ለህዝብ ማሰብ እንዳለበት የተናገሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸውን ምርቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማያመርቱ አምራቾች ላይ እርምጃ መውሰዱ ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሆነም ገልፀዋል።

በ 2013 በጀት ዓመት በፋብሪካ እና በገበያ ቦታዎች ላይ በአካል በመገኝት የገበያ እና ፋብሪካ ክትትልና ቁጥጥር ከተደረገባቸው 189 ደርጅቶች ውስጥ በ 65 ድርጀቶች ላይ ወካይ ናሙናዎችን በመውሰድ የፊዚካል ኢንስፔክሽን እና የላብራቶሪ ፍተሻ በተደረገው ወጤት መሰረት 34 ደርጅቶች የተቀመጠውን የጥራት ደረጃ ያሟሉ ሲሆን 31 ድርጅቶች ምርት ጥራት ከደረጃ በታች የምርት ጥራት ሰርተፍኬት እና የብሄራዊ ደረጃ ምልክት የመጠቀም ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ የንግድ ፍቃዳቸውን ማገዱን ሚኒስቴር መስራያ ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

አንድ መቶ 24 ደርጅቶች ላይ በተደርገው በግንባር ዕይታ/physical inspection/ስራዎች መሰረት በተቀመጠው ደረጃ መስፈርት መሰረት እየሰሩ መሆኑ እንደተረጋገጠ ለማወቅ ተችሏል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የገበያና ፋብሪካ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሬ ዳይሬክተር ተከተል ጌቶ እንደተናገሩት በ2013 ዓመት በሰባት ወራት በተደረገው የቁጥጥር ስራ የተወሰዱ እርምጃዎች 65 የሚሆኑ ድርጅቶች ንግድ ፍቃድ ከታገደባቸው መካከል የውሀ አምራቾች ፣ የሳሙና ፣ ሳታይዘር ፣ ባትሪ ድንጋይ ፣ ቆርቆሮ ፣ ብሎኬት ፣ ጨው እንዲሁም ሚስማር አምራቾች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የ2013 በጀት ዓመት ሰናት ወራት አፈጻጸም በአንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የገቢ እቃዎች እና በኹለት መቶ 50 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የወጪ ምርቶች ላይ በጉሙሩክ ጣቢያዎች የኢንስፔክሽን ሥራ በማከናወን በላብራቶሪ እንዲፈተሹ በማድረግ በፍተሻ ውጤት መሰረት የኢትዮጲያን ደረጃ ያሟሉ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እና ከሀገር እንዲወጡ ፈቃድ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

እንዲሁም በተደረገው የቁጥጥር ስራ የኢትዮጵያ ደረጃዎችን ያላሟሉ እንዲሁም በኢትዮጵያ መመርመሪያ ላብራቶሪ የሌላቸውን የአለም አቀፍ ጥራት ማረጋገጫ ያላመጡትን ወደመጡበት አገር ተመላሽ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።
በዚህም የተወሰዱ እርምጃዎች 302 ካርቶን የባትሪ ድንጋይ፣ ስድስት ካርቶን የታሸጉ ምግቦች፣ 16 ነጥብ 24 ሜትሪክ ቶን የሶላር ቴክኖሎጂ ምርት 331 ነጥብ አራት ሜትሪክ ቶን የቤት ክዳን ቆርቆሮ ፣ ኹለት ሺህ ስድስት መቶ ኹለት ሜትሪክ ቶን ጋልቫናይዝድ ጥቅል ቆርቆሮ፣ ሦስት ሺሕ ስምንት መቶ 40 ከረጢት የስንዴ ዱቄት፣ 49 ሜትሪክ ቶን የዱቄት ሳሙና፣ አምስት ሺሕ ኹለት መቶ 32 ካርቶን የምግብ ዘይት፣ ኹለት ሺሕ አራት መቶ 50 ካርቶን የታሸገ ጁስ የኢትዮጵያን አስገዳጅ ደረጃ መስፈርት ባለማሟላታቸው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ከታገዱ ምርቶች መካከል መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ በላብራቶሪ አቅም ውስንነት ምክንያት መፈተሽ የማችሉ ምርቶች የሶስተኛ ወገን አለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያቀርቡ የሚደረግ ሲሆን ከነዚህ ምርቶች ውስጥ የሶላር ቴክኖሎጂ ምርቶች የውሃ ፓምፕ እንደሚገኙበት አክለው አስታውቀዋል።

በዋናነት ከቻይና እና ከዩክሬን ሀገራት የሚመጡ የአርማታ ብረት ምርቶች እንዲሁም ከቻይና ሀገር የሚመጡ የቆርቆሮ ምርቶች የጥራት ችግር ይስተዋልባቸዋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የአምራች ዘርፉ ከትርፍ ይልቅ ጥራት ላይ መስራት እንዳለበት ያስገነዘቡ ሲሆን እቃዎችን ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚወጣ በዚህም ጥራቱን ያልጠበቀ ሆኖ ተመላሽ ሲሆን የውጭ ምንዛሬን እንድናባክን ያደርገናል ብለዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here