አገር የተለያዩ ዓይነት ፍቺዎች እና አገርን ለመግለጽ የሚነሱ በርካታ ግን ደግሞ ወደ አንድ መግባቢያ መድረስ ያልተቻለባቸው ጉዳዮች አሉ። አሁንም ድረስ አገር ማለት ሰው ወይም ደግሞ አገር ማለት ጋራ ሸንተረር ነው በሚል የጎራ ለይቶ ክርክሮች እና የበርካታ አመክንዮዎች ድርደራም ይታያል።
ይሁን እንጂ አንድን አገር በዋናነት አስማምቶ እና አግባብቶ የሚስቆመው ጉዳይ ግን የአንድ አገር ሉዓላዊነት ነው። አገር እንደ አገር በይፋ የሚጠራው እና አገር ተብሎ የሚታወቀው ባለው ሉዓላዊነት እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ተግባብቶ በሚቀበለው ቁመና እና መልክ እንደሆነ ይታወቃል። ታዲያ የተለያዩ አገራት ምናልባትም ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ሉዓላዊነታቸውን ያስከበሩት እና እያስከበሩም የሚገኙት በጦርነት እና በውጊያ እንደሆነም የታሪክ ድርሳናት ያስነብባሉ። አሁንም ድረስ ሉዓላዊነቴ ተደፈሩ ያሉ አገራት በወራሪ አገራት ወይም ቡድኖች ላይ ጦር ሲሰብቁ እና የጦር ወሬዎችን ሲያስነዙ ይስተዋላሉ።
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣም ከዚህ የሚለይ አይደለም። ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድም ቀን የሉዓላዊነቷን ጉዳይ ለድርድር የማያቀርቡ እና በአገራቸው ሉዓላዊነት የሚመጣን ጠላት አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተው፤ ደረታቸውን ለጦር ገብረው ከመመከት ወደ ኋላ የማይሉ ልጆች ባለቤት እንደሆነች እና ኢትዮጵያዊያን በዓለም አቀፍ መድረክ ቀና ብለው እንዲራመዱ ያደረጉ ጉምቱ አርበኞች አገርም ናት። ጀግና ወላድ አገራችን ታዲያ በተለያዩ ዘመኖቿ ከፍተኛ የሆኑ እና የታቀዱ፤ የተደራጁ ሉዓላዊነትን የመድፈር አደጋዎች ተቃጥተውባት ነገር ግን በሚሰጣቸው የአርበኝነት ግብረ መልስ በሽንፈት እንዲመለሱ ሆነዋል።
ይህ የአንድን አገር የሉዓላዊነት ጥበቃ እና ሉዓላዊነትን አስጠብቆ የመቆየት እና አገር ታፍራ እና ተከበር የመኖሯ ምስጢር ከላይ የጠቀስናቸው አርበኝነት ተግባራት እና ተጋድሎዎች ናቸው።
ከዘመን ጋር አብሮ የሚዘምነው እና ቅርጹን እንደ ወቅቱ የሚቀይረው የሉዓለዊነት ጥቃት ጉዳይ ታዲያ በዚህ ዘመን ደግሞ ቅርጹን ቀይሮ ሲቃጣ እናያለን። ከአድዋ እስከ ካራማራ በጉልህ ተጋድሎ ወራሪን ያሳፈረች አገርን በዲፖሎማሲ እና በተለያዩ መንገዶች ሉዓላነቷን ሊነጥቁ እና ሊያንበረክኩ የሚሞክሩ አገራት ጥቂት አይደሉም። ሉዓላዊነት የግድ ድንበር ጥሶ በመግባት የአንድን አገር መሬት መያዝ ብቻ ላይሆን ይችላል። በዲፖሎማሲ ጫና በመፍጠር እና ለአዳጊ አገራት የሚሰጡትን ብድር ወይም ዕርዳታን ተገን በማድረግ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የመግባት አዝማሚያ እና የጠነከረ ፍላጎት እየታየ ይገኛል። ይህ ደግሞ ዘመናዊው የሉዓላዊነት መድፈር እንቅስቃሴ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ ከወቅታዊ ኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በርካታ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በመግባት ከትክክለኛው እና አገርን በማስተዳደር ላይ ከሚገኘው መንግስት እኩል ውሳኔዎችን ለመስጠት እና አልፎ አልፎም ደግሞ በመንግስት እና ሕዝብ ላይ ጫና ለማሳደር ሲዳዳቸው ተስተውለዋል። ይህ ደግሞ አንዲት ሉዓላዊትን አገር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት በእጅጉ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባች። ይህም ብቻ ሳይሆን የትኛውም አካል የሚሰጠው ዕርዳታ ወይም አገራት የሚቀበሉት ድጋፍ ሉዓላዊነታቸውን ሰጥተው ሳይሆን በኹለቱ ወገኖች ላይ የተመሰረት መፈቃቀድ እንጂ ተረጂዎች አገራት ሉዓላዊነታቸውን ሰጥተው እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በየትኛውም ዘርፍ የበቁ እና የደረጁ ዓለም ያደነቃቸው የውጭ ግንኙነት ዲፖሎማሲ ኢትዮጵያን ከፍ አድርገው ያስከበሩ ሰዎች መፍለቂያ እንደመሆኗ መጠን በዲፖሎማሲም በኩል የትኛውም አይነት ጫና ሊደረግባት የማይገባ እና ታፍራ እና ተከብራ ልትኖር የሚገባት የኩሩ ሕዝቦች መኖሪያ መሆኗንም አገራት እና ድርጅቶች ሊገነዘቡት ይገባል።
በመሆኑም ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጫና ከወዲሁ እንዲቆም እና ዳግመኛ እንዳይሞከርም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት የምትችልበት አገራዊ ቁመና ላይ እንደመገኘቷ እና ከፍ ካለም ወደ አፍሪካ ሕብረት የሚደርስ ይሆናል እንጂ ወደ አገር ውስጥ በሚፈሰው የዕርዳታ ሰበብ ዶላር የመንግሥትን ስልጣን በገዛ አገሩ ላይ የማስተዳደር ኃላፊነቱ ላይ ግን ጫና ሊፈጠርበት አይገባል ፤አይቻልምም። ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል በቀደሙት ዓመታት ሲቀነቀን የነበረው እንቅስቃሴም አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እና ከኢትዮጰያ ጎን ሁሉም የአፍሪካ አገራት ሊቆሙ እንደሚገባም አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ይህ ብቻም ሳይሆን እንደቀደሙት አባቶቻችን ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ልዩነታችንን በማጥበብ አገርን ከሉዓላዊነት መጣስ ለመታደግ አበክረን እንድንሰራም አዲስ ማለዳ ጥሪዋን ታቀርባለች። ኢትዮጵያ ችግሮቿ በየትኛውም ዘመን ቢሆን መፍትሔዎች ከራሷ ችሎታ እና የመፍትሔ ሀሳብ በላይ ሆነውባት አያውቁም። ቅራኔዎች ቢሆኑ በቱባው የዕርቅ ባህላችን የምንፈታቸው እንጂ ዓለም አቀፍ አገራትን ሚጋብ ባለመሆኑ አገራትም ሆናችሁ ድርጅቶች ዕጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ እንድትሰበስቡ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። የቆየውን እና የኖረውን ቂማቸውን በኢትዮጰያ ላይ ለመወጣት አመቺ ጊዜ እየጠበቃችሁ ያሉ አገራት መኖራቸውም አያጠራጥርም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የሕዝብን አንድነት ለመሸርሸር እና የዘመናት የሽንፈት ቁጭታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደማይሳካ እና አሁንም የዚህ ዘመን ሽንፈታቸውን እንደሚከናነቡ አዲስ ማለዳ ለማሳሰብ ትወዳለች። የውስጥ ጉዳያቸውን ለኢትዮጵያዊያን ተውላቸው እርዳታችሁንም በሉዓላዊነት ቅድመ ሁኔታ ለመስጠት ከሆነ ውላችሁ ገንዘባችሁን በኪሳችሁ አድርጋችሁ ከኢትዮጵያ ላይ ዓይናችሁን እንድታነሱም አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች። ታሪካዊ ወዳጅ አገራትም በዚህ በኩል መመስገን እንደሚገባችሁ እና ኢትዮጵያ ያላትን አገራዊ ክብር ተመልክታችሁ ለምታደርጉት ድጋፍ እና የኢትዮጵያ ችግር በኢትዮጵያ መመለስ ይኖርታል ብላችሁ የምታምኑ አገራትም አዲስ ማለዳ አጠናክራችሁ እንደትቀጥሉ ጥሪዋን ታስተላልፋች። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ኢትዮጰያን በተለያዩ ዓለም አገራት የወከላችሁ ሚሲዮኖች፣ ቆንስላዎች እና አምበሳደሮች የዘመናዊው ዘመን የውጊያ ሜዳ ላይ ነው እና ያላችሁት አገራችሁን ቀን ከሌት በማስከበር ጸንታችሁ እንድትቆሙ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። የሚኬድበት መንገድ መራራ፤ ጫናው ከቀን ወደ ቀን የበረታ እንደሚሆን ይጠበቃል ነገር ግን ኢትዮጵያን አስከብራችሁ ከእነ ሙሉ ክብሯ ለተተኪው ትውልድ የምታስተላልፏት ሉዓላዊነቷ የተከበ አገርን ለመፍጠር መልካም ተጋድሎ እንድታደርጉ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013


