በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በንጹሀን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የደረሱ ጥቃቶች መቀጠላቸውን ተከትሎ “የመንግሥት እሽሩሩ ለታጠቁ ኃይሎች ተመችቷል።” ሲሉ የቡለን ወረዳ ኗሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
አዲስ ማለዳ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከተማ ላይ የሚገኙ ኗሪዎችን አነጋግራ የአካባቢውን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የመንግሥት እርምጃ ወደ ስጋት ተቀይሮብናል ብለዋል። ኗሪዎቹ ይህን ያሉት በመተከል ዞን በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ጥቃት የሚያደርሰው ታጣቂ ኃይል ሰሞኑን ቡለን ከተማ ለድርድር በሚል ሰበብ እየወጣ አና እየገባ ለኗሪዎች ስጋት መሆኑን በመግለጽ ነው።
አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው የወረዳው ኗሪዎች እንደሚሉት ከሆነ የታጣቂ ኃይሉ መሪ ባሳለፍነው ሳምንት በራሱ ታጣቂዎች ታጅቦ ቡለን ከተማ ገብቶ ወጥቷል ብለዋል። ኗሪዎቹ አክለውም መንግሥት ታጣቂ ሀይሉን ለማስወገድ ያሳየው ቸልተኝነት ዳግመኛ ዋጋ እንዳያስከፍል እንሰጋለን ሲሉ ጠቁመዋል።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ለማጣራት ከኗሪዎች በተጨማሪ በክልሉ መንግሥታዊ መዋቅር ሥር ቡለን ወረዳ የሚሰሩ ምንጮችን አነጋግራለች። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ታጣቂ ሀይሉ መሪ ቡለን ከተማ መግባት መውጣቱ እውነት ነው ብለዋል።
ምንጮቹ አክለውም የታጣቂ ሀይሉ መሪ ቢለን ከተማ ገብቶ መንግሥት ቢሮ እንድሰጠው ጠይቆ ቢሮ እንደተሰጠው ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። የተሰጠው ቢሮም በወረዳው አስተዳደር ቢሮ አቅራቢያ ነው ተብሏል። በተጨማሪም መኪና እንድሰጠው ጠይቆ ኹለት መኪና እንደተሰጠው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። የታጣቂ ሀይሉ መሪ ከዚህ በተጫማሪም በጀት ይመደብልኝ የሚል ጥያቄ እንዳቀረበ የአዲስ ማለዳ ምንጮች መስማታቸውን ገልጸዋል።
የታጣቂ ሀይሉ አባላት ወደ ከተማ መግባታቸው ከተማዋን አጥንተው ጥቃት እንዳያደርሱ ኗሪዎች ስጋት አላቸው። በዚህ የተነሳ የከተማዋ ኗሪዎች ካለባቸው ስጋት አንጻር ሌሊት ላይ እንደማይተኙ ተናግረዋል። ሁኔታውን ለአዲስ ማለዳ ያስረዱ የከተማዋ ኗሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በሁኔታው ቅሬታ እንደተሰማቸው ነው።
ታጣቂ ሀይሉ በአንድ በኩል ከመንግሥት ጋር በሰላማዊ ድርድር ትጥቅ እፈታለሁ እያለ በማዘናጋት በሚንቀሳቀስበት የገጠር አከባቢዎች ያገኛቸውን ንጹሀን ዜጎች እየገደለ መሆኑ በመንግሥት ላይ የነበረንን ተስፋ ወደ ስጋት ቀይሮብናል ብለዋል። ታጣቂ ሀይሉ ከመንግሥት ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመግባባትና ትጥቅ ለመፍታት ፍላጎት እንዳለው በማስመሰል በሚደርገው የማዘናጋት ድርጊት፣ ከገጠር ወደ ከተማ ገብተው የነበሩ አርሶ አደሮች ተዘናግተው ንብረታቸውን ለመሰብሰብ ወደ ገጠር በሚሄዱበት ወቅት እየተገደሉ ነው ይላሉ ኗሪዎቹ።
ባሳለፍነው የካቲት 30/2013 በቡለን ወረዳ ኤማንጅ ቀበሌ ምሽት ላይ ታጣቂ ሀይሉ ባደረሰው ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉና አንድ ሰው ላይ የመቁሰል አገዳ እንደደረሰ ምንጮች ጠቁመዋል። የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉና አንድ ሰው መቁሰል በግልጽ ቢታወቅም ጥቃቱ የተፈጸመው ምሽት ላይ በመሆኑ ሌሎች የተጎዶ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ስጋታቸውን የገለጹት ኗሪዎቹ መንግሥት ታጣቂ ሀይሉን እያባበለ ሌላ ተጨማሪ ችግር እስከሚፈጠር ከመጠበቅ፣ ከወዲሁ በጥንቃቄ በአስተማማኝነት የሕዝብ ደህንነት ለማስጠበቅ መሥራት አለበት ብለዋል።
በመተከል ዞን በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንደቀጠሉ ቢሆንም ዞኑን የሚመራው ኮማንድ ፖስት መልካም የሚባሉ ሥራዎች እየሰራ እንደነበር ኗሪዎች ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። አሁን ግን የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ከመቀጠል ይልቅ መዘናጋት እየታየ ነው ብለዋል ኗሪዎች።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ምላሽ እንድሰጥ የቡለን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ግዛቱ ነሲ የእጅ ስልክ ላይ ስልክ በመደወልና የጽሑፍ መልዕክት ብትልክም ምላሽ አላገኘችም።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013


