ነፃ የንግድ ቀጠናውን የሚመራ ተቋም ሊቋቋም እንደሆነ ተገለፀ

0
1297

የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጠናን ራሱን ችሎ የሚመራ እና የሚቆጣጠር ተቋም ሊቋቋም እንደሆነ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። ነጻ የንግድ ቀጠናውን የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም የሚመሰረተው በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር ጀነራል ሙሴ ምንዳዬ ናቸው።

እርሳቸው እንደተናገሩት ከዚህ በፊት ይህን ተግባር ለመሥራት ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተቋቋመው ኮሚቴው ባለበት የሚቀጥል ሆኖ የነፃ ንግድ ቀጠናውን ብቻ የሚመራ ተቋም ግን አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት ተናግረዋል።
የሚቋቋመው ተቋም ዋናው ሥራም ገበያውን በመገምገም ፣ የገበያውን ሁኔታ ማጣራት ፣ የአገሮችን ሁኔታ በማየት ገበያ የለበትን መዳረሻ በመለየት ለመንግስት የጥናት ፅሁፎችን የሚያዘጋጅ እንደሆነም ተናግረዋል።

የዚህ ተቋም ዋናነት ጠቀሜታም በአፍሪካ የንግድ ቀጠና መረጃ የሚፈልግ ካለ፣ ቀን በቀን ያለውን ንግድ ለመቆጣጠር ፣ ነጋዴው የሚያጋጥመውን ችግር ማየት ፣ለመንግስት የድርድር አቅጣጫዎችን ማምጣት፣ መከፈት የሚገባቸውን ዘርፎች አጥንቶ ማቅረብ እንዲሁም ከትግበራ ጋር በተያያዘ የሚመጡ ድርድሮችን መከታተላል ነው ብለዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ውስጥ ሪጅናል ዳይሬክቶሬት የሚባል ክፍል እንዳለ የተናገሩት ሙሴ፣ ይህ ክፍል የንግድ ቀጠናውን እንዳይከታተል በርካታ ስራዎች አሉበት ለአብነትም የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስት እንዲሁም ደግሞ የምስራቅና ደቡብ የአፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ ጉዳዮች ስለሚሰራ የነፃ የንግድ ቀጠናውን የሚመራ ረሱን የቻለ ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነት አሁን ላይ ስምምነቱን ከፈረምን በኋላ ከታክስ ነፃ የሚሆኑት የፋብሪካ እቃዎች ዝርዝር ማውጣት ነው ተቀዳሚ ስራ ስለዚህም የትኞቹን እቃዎችን ነው ነፃ የምናደርገው የሚለውን ዝርዝር እያዘጋጅን ነው ምክንያቱም 90 በመቶ የሚሆነውን የታሪፍ መስመር በ10 አመት ውስጥ ዜሮ ስለሚደረግ ብለዋል።

90 በመቶ ነፃ የሚደረጉትን ዝርዝሩን ሰርተን አጠናቀን ለገንዘብ ሚኒስቴር ልከናል ያሉት ዳይሬክተሩ በመቀጠል በመንግስት ደረጃ አንድ አቋም ከያዝን በኋላ ለግል ዘርፉ ጋር የመንግስትን ፖሊሲ ይዘን ውይይቶች አድርገን ወደ አፍሪካ ህብረት እንልካለንም ብለዋል።
በዚህም ከአገልግሎት ዘርፍም ነፃ የሚደረጉ ምን ምን ለመለየት እየተሰራ እንደሆነና በዚህም አምስት ዘርፍ መካከል የንግድ ዘርፍ ፣ የገንዘብ ዘርፍ ፣ የግንኙነት ዘርፍ ፣ የትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሁም የቱሪዝም ዘርፍ መካከል የትኛው ነፃ እንደሚሆን የመለየት ስራ እየተሰራ እንዳለም ጠቁመዋል።

በቀጣይም ነፃ የሚሆኑት ምርቶችን ለይተን ስናበቃ እንዲሁም ለአፍሪካ ህብረት ካስገባን በኋላ ንግዱ ይጀመራል ብለዋል።ስለዚህም የዝግጅት ስራ እየሰራን ነው እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ ንግድ ሲጀመር በተከፈተው ዘርፍ ላይ ቀረጥ እየቀነሰ ስለሚመጣ ከፍተኛ የሆነ ውድድር ጫና በኢንዱስትሪዎች ላይ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

መንግስት እንደዚህ አይነት ስምምነቶች ውስጥ ሲገባ የፖሊሲ ስኬታችንን እናጣለን ምክንያቱም ዛሬ የቀነስነውን ታሪፍ ነገ ደግሞ ልንጨምረው አንችልም ብለዋል። በሌላ መልኩ ደግሞ የአገርን ግንባታ ከመገንባት አንፃር አስተማማኝ ገበያ ስለሚሆን አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ንግዱ ሲጀመር ከቀረጥ ነፃ ስለሚገቡ መንግስት ከቀረጥ የሚያገኘውን ገቢ ያጣል ይሁን እንጂ ብዛት ያላቸው እቃዎች ከሌሎች አገራት ሲገቡ ከቀረጥ ያጣውን ከሌሎች የአገር ውስጥ ታክሶች ለአብነትም ከኤክሳይስ እንዲሁም ተጨማሪ እሴት ታክስ ሊያገኛቸው ይችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ተካዮች ምክር ቤት መጋቢት 2011 ዓመት የነፃ የንግድ ቀጠናውን ማፅደቁ ይታወሳል።በዚህም ጥር /2013 ወደ ስራ የገባውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን 54 አባል አገሮች ፈርመው የተቀበሉ ሲሆን ጋና ግን ቀድማ ወደ ስራ ምግባቷ ይታወቃል።


ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here