የትንባሆ ቁጥጥር እንዲኖር የወጣው የምግብ መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 11 12/2011ን ለማስተግበር የሚያስችል የሕግ ማእቀፍ በክልሎች አለመኖሩን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ አስታወቁ።
አዋጁ ከወጣ ኹለት ዓመት የሞላው ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ በክልሎች ማስተግበሪያ ሕግ አለመዘጋጀቱ፣ በክልሎች ላይ የሰው ኃይል አደረጃጀት አለመኖሩ በክልሎች አዋጁን ለማስተግበር እንደ ተግዳሮት እንደሆነም አክለው ተናግረዋል።
በአዋጁ ትግበራ ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ንግግር ያደረጉት ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመርያ መፅደቁ ፣ የመቆጣጠሪያ መመርያ መውጣቱንና ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን የጠቆሙ ሲሆን በክልሎች ደረጃ ህግ ባለመውጣቱ በራሳቸው አፅድቀው ሥራ ላይ እንዲያውሉ ሞዴል ሕግ ተዘጋጅቶ ወደ ክልሎች መላኩን እንዲሁም በክልሎች ህጉ ፀድቆ ሊሰራበት እንደሚገባምአክለው ተናግረዋል። አብዛኞቹ የአዋጁ አንቀፆች የሚፈፀሙት በክልሎች ነው በዚህም ሞዴል ህግ መዘጋጀት ስላለበት ረቂቁን አዘጋጅተን ለክልሎች ልከናልም ብለዋል።
በሌላ በኩል እንደ ችግር ከተነሳው መካከል አጠቃላይ አዋጁ ትግብራው ዝቅተኛ መሆኑን የተናገሩት ሄራን የክልሎች ህግ አለማውጣት በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ እንደሚገኝበት አክለው ተናግረዋል።
አጠቃላይ አዋድ 11 12ን የሚያስተገብር ረቂቅ መመሪያ እየተዘጋጀ እንደሆነም እንዲሁም ተጠናቆ ሲፀድቅ የተሻለ የቁጥጥረው ስራ እንዲሁም የተሻለ የአዋጅ አተገባበር እንዲኖር ያስችላልም ብለዋል።
አዋጁ ላይ ካሉ ነገሮች ውስጥ የትንባሆ ማሸጊያ ላይ አስተማሪ ምስል ማድረግ ፣ ሆቴሎች ላይ የማጨሻ ቦታን እንዲያዘጋጁ የማድረግ ፣ ከ10 ሜትር ርቀት ላይ ማጨስ የማይቻልባቸው ስፍራዎችን መቆጣጠር ላይ ጥሩ የሚባሉ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ጠቁመዋል።
ክፍተት ያለባቸው የአዋጁ ክፍሎች መካከል ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ልጆች ትንባሆ መሸጥም ሆነ ማሸጥ የማይቻል እንደሆነ በአዋጁ የተካተተ ሲሆን እየተተገበረ እንዳልሆነ ተጠሷል፤በፍሬ መሸጥ እነደማይቻል በአዋጁ ተካቷል ይህም እየተተገበረ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አዋጁ በጸደቀበት ዓመት የነበረው አተገባበር በአዲስ አበባ ከፍተኛ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን መተግበሩ እየቀረ እና አዲስ ማለዳ አሰሳ ባደረገችባቸው አካባቢዎችም ጭራሹኑ ሲተገበር አለመታየቱን ታዝባለች።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የህግ ክፍል ጊዜያዊ ዳይሬክተር ዳግም አለማየሁ አዋጁ ከተዘጋጀ በኋላ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ከነሱም መካከል አዋጁን ለማስተግበር የሚጠቅሙ ማስተግበሪያ ህጎች እንዲሁም መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም የትንባሆ ገላጭ ፅሁፍን በተመለከተ ፣ የትንባሆ ቁጥጥር እንዲሁም የተለያዩ የቁጥጥር ስራውን የሚያግዙ መመሪያዎች ተዘጋጅተው መውጣታቸውንም ጠቅሰዋል። አዋጅ ጠቅለል ያሉ ጉዳዮችን ይዞ የሚወጣ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ለአዋጅ መደገፊያ እንዲሁም ማስተግበሪያ የሚሆን መመሪያ እና ህግ ሊዘጋጅለት ይገባልም ብለዋል።
ምንም እንኳን በአዋጁ 11 12 አገራዊ ተፈፃሚነት ያለው ህግ ስለሆነ ብቻ በአዋጁ ብቻ መስራት ይቻላል ነገር ግን በክልል ከተሞች አዋጁን ማስተግበሪያ ህጎች እንዲሁም መመሪያዎች አለመዘጋጀታቸው የአዋጁ ተግባራዊነት ላይ እንደ አንድ እንከን የሚነሳ እንደሆነ ገልፀዋል።
በዚህም አሁን ከአዲስ አበባ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እንዲሁም ከአዲስ አበባ ምክር ቤት ጋር በጋራ በመሆን የህግ ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ሊያ ታደሰ(ዶ/ር) እንደተናገሩት የአዋጁ አተገባበር ላይ አበረታች ውጤቶች ቢታዩም ሙሉ ለሙሉ እንዳልተተገበረ እንዲሁም ክፍተቶች ያሉ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በዓመት ከትንባሆ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ በሽታዎች መድሀኒትን ለማስገባት እንዲሆን በዓመት 50 ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች፤ይህንን አዋጅ በትክክሉ ሲተገበር ለመድሀኒት የምናወጣው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጤናማ ትውልድ እንዲኖረን ያደርጋል ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 123 መጋቢት 3 2013



