ከ150ዎቹ ተወዳዳሪዎች 40ዎቹ በሚቀጥለው ሚያዚያ ወር ይለያሉ
በኢትዮጵያ ለኹለተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የቡና ውድድር ከተመዘገቡት 1848 ተወዳዳሪዎች 150 ያክሉ ለኹለተኛው ዙር ውድድር ማለፋቸውን ፌድ ዘፊቸር ኢትዮጵያ ቫሊው ቸይን አክቲቪቲይ(Feed the Future Ethiopia Value Chain Activity) ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ለኹለተኛ ዙር ያለፉ ተወዳዳሪዎች ውድድር በሚቀጥለው ሚዚያ ወር እንደሚካሄድ የፌድ ዘፊቸር ቫሊው ቸይን አክቲቪቲይ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሰብለ ተብለብርሃን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። የ150 ተወዳዳሪዎች ውድድር በሚቀጥለው ወር ከሚዚያ አራት አስከ ሚዚያ 8/2013 እንደሚካሄድታውቋል።
የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ለመጨረሻ ዙር የሚልፉ 40 ተወዳዳሪዎችን ለመለየት የአገር ውስጥ ቡና ቀማሽ ባለሙዎች በፌድ ዘፊቸር ኢትዮጵያ ቨሊው ቸይን አክቲቪቲይ ተዘጋጅተዋል ብለዋል። የአገር ውስጥ ቡና ቀማሾቹ የመጨረሻ ተወዳዳሪዎቹን ለመለየት ለውድድሩ የተቀመጡ መስፈርቶችን መሰረት አድረገው እንደሚለዩ ተገልጿል።
ለመጨረሻ ዙር ውድድር በአገር ውስጥ ቀማሾች የሚመረጡ 40 ተወዳዳሪ ቡናዎች እንደሚሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ 40ዎቹ ቡናዎች ለመጨረሻ ደረጃ ውድድር ይቀርባሉ ተብሏል። የ40ዎቹን መርጥ ቡናዎች የመጨረሻ የደረጃ ውድድር የሚለዩት የቡና ውድድር ባለቤት በሆነው አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ(Alliance for Coffee Excellence) የተመረጡ ዓለም አቀፍ ቡና ቀማሽ ባለሙያዎች ይሆናሉ ተብሏል።
በአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ በሚመረጡ ዓለም አቀፍ ቡና ቀማሽ ባለሚያዎች ደረጃ የሚሰጣቸው 40 ቡናዎች በተሰጣቸው ደረጃ መጠን ለዓለም አቀፍ ጨረታ ቀርበው በከፍተኛ ዋጋ እንደሚሸጡ ሰብለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በደረጃ የሚለዩት 40 ምርጥ የኢትዮጵያ ቡናዎች ለጨረታ የሚቀርቡት በሚመጣው ሰኔ ወር ላይ መሆኑ ተመላቷል። ለጨረታ የሚቀርቡት 40 ምርጥ ቡናዎች በኹለት ደረጃ ተከፍለው እንደሚሆን ሰብለ ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው ደረጃ በዓለም አቀፍ ቡና ቀማሽ ባለሙያዎች ከ87 በመቶ በላይ ውጤት የተሰጣቸውመሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ለ24 ስዓታት ብቻ በሚቆይ ገልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚሸጡ ተገልጿል።
ኹለተኛው ደረጃ ደግሞ በዓለም አቀፍ ቡና ቀማሽ ባለሙያዎች ከ85 በመቶ እስከ 87 በመቶ ውጤት የተሰጣቸው ሲሆኑ፣ በዚህ ደረጃ ውስጥ የሚካተቱ ምርጥ ቡናዎች ለአንድ ሳምንት ያክል በግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ የሚሸጡ ናቸው።
የምርጥ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ የጨረታ ሽያጭ በኦንላይን(በቀጥታ በይነ መረብ) እንደሚካሄድ ሰብለ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የቡና ውድድር ለመጀመሪያያ ጊዜ የተካሄደው ባለፈው 2012 ሲሆን የዘንድሮው ለኹለተኛ ጊዜ የሚደረግ የቡና ውድድር ነው። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር፣ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስኢትዮጵያ በጋራ በመሆን በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ልማት የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ የምርጥ ቡና ውድድር ነው።
ዘንድሮ በተዘጋጀው ኹለተኛው የቡና ውድድር ከተመዘገቡት 1848 ቡናዎች 150ዎቹ ለኹለተኛ ዙር ውድድር የተመረጡት ለውድድሩ የተቀመጡ ዝርዝር መስፈርቶች አሟልተው መሆኑ ተመላክቷል።
ባለፈው 2012 በተካሄደው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የምርጥ ቡና ውድድር የተሳተፉት 1400 እንደነበሩ ሰብለ አስታውሰዋል። በመጀመሪያው ውድድር የመጀመሪያ ደረጃ አሸናፊ የሆነው ቡና በግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ አንድ ኪሎ 407 ዶላር መሸጡ የሚታወስ ነው። ቀሪዎቹ ለመጨረሻ ጭረታ ቀርበው የነበሩ ምርጥ ቡናዎች እንደየተሰጣቸው ደረጃ በጨረታ ተሸጠው በአማካኝ አንድ ኪሎ ግራም ቡና በ28 ዶላር መሸጣቸው ተመክቷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጥ ቡና ውድድር ከመጀመሩ በፊት አንድ ምርጥ የተባለ ቡና የሚሸጠው አንድ ኪሎ ከአምስት ዶላር እንደማይበልጥ የጠቆሙት ሰብለ፣ ውድድሩ በኢትዮጵያ መጀመሩ የኢትዮጵያ ቡና ምርጥ መሆኑን የዓለም አገራት እንዳውቁት እድል ከፍቷል ብለዋል።
የምርጥ ቡና ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው ብራዚል ሲሆን፣ አላማውም ምርጥ ቡናዎች በአርፊ ዋጋ እንድሸጡ ማድረግ ነበር። አሁን ላይ የቡና ውድድር ባለቤት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013



