ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ ጀምሮ የሰው ዘርን በቀጥታ በማጥቃት እስካሁን ድረስ የ400 ሺህ ያህል ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፤ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉትን አጥቅቷል። በኢትዮጵያም እንዲሁ ወረርሽኙ የሰዎች ሕይወትን መቅጠፍ የጀመረ ሲሆን ሺዎችን የቫይረሱ ተጠቂ አድርጓል። በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ወረርሽኙ በአገራችን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ወደ መድረስ እየሔደ ለመሆኑ የየዕለቱን ሪፖርት መመልከት በቂ ነው።
ወረርሽኙ በቀጥታ ከሚያደርሰው የጤና ችግር ባሻገር አገራት ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲዳረጉ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ቀስ በቀስ ተጽዕኖው እየበረታ ችግሮቹ እንዲወሳሰቡ እያደረገ ይገኛል፤ በተለይ ምጣኔ ሀብታዊ ተጽዕኖው ጎልቷል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮችም ከማስከተሉ በተጨማሪ በተለይ በሽታውን ለመከላከል አገራት በወሰዱት ከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ከቤት የመቀመጥ እርምጃ ምክንያት በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት መጠን በመጨመሩ ችግሩ አሳሳሰቢ ደረጃ እየደረሰ ለመሆኑ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሚወጡ ሪፖርቶች እና ዘገባዎች አመላካቾች ናቸው።
ሰልጥነዋል፣ ግንዛቤያቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል እንዲሁም የሴቶች መብቶች በንጽጽር ይከበርባቸዋል በተባሉት የአውሮፓ አገራት ጭምር የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተወሰዱ በቤት ውስጥ የመቆየት እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ፆታን መሰረት ያደረገ የሴቶች እና ሕፃናት የቤት ውስጥ ጥቃት ጨምሯል። በሚያሳዝን ሁኔታ ከአካላዊ ድብደባ ባሻገር እስከሞት ድረስ ያጋጠሙ ጥቃቶች መድረሳቸውን መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
በአፍሪካ አገራት ፆታዊ የሴቶች እና ሕፃናት የቤት ውስጥ ጥቃቶች ከአውሮፓ አገራት ጋር ለንጽጽር የሚቀርቡ ባይሆንም ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መጨመራቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካን የወሰድን እንደሆነ የሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ በ37 በመቶ መጨመሩን ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በሌሎች የአፍሪካ አገራትም እንዲሁ በግርድፍ በቀረቡ ሪፖርቶች ከወረርሽኙ በፊት ይደርስ ከነበረው ፆታዊ የቤት ውስጥ ጥቃቶች በሦስት እጥፍ ማደጋቸውን እነዚሁ ሪፖርቶች ያሳያሉ።
ፆታን መሰረት አድርጎ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሱት የቤት ውስጥ ጥቃቶች ከአውሮፓም ይሁን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ባልተናነሰ የማሻቀብ ዝንባሌ አሳይቷል። ከወረርሽኙ ስርጭት ስጋት ጋር በተያያዘ መሥሪያ ቤቶች በሙሉ አቅማቸው ስለማይሠሩ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ለችግሩ መባባስ አስተዋጽዖ እንዳደረጉ ይታመናል።
የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኀላፊ አልማዝ አብርሃ ሰሞኑን ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ በመዲናችን ከሚገኙት ከጋንዲ፣ ከምንሊክ እና ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታሎች ቢሯቸው በሰበሰበው መረጃ መሰረት ባለፉት ኹለት ወራት ውስጥ ብቻ 101 ሕፃናት መደፈራቸው ሪፖርት መደረጉን አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ከሦስት ሆስፒታሎች በተሰበሰቡ ሪፖርቶች 57 ወንድ ሕፃናት በቤት ውስጥ ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው በማስታወቅ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል። እጅግ በጣም ያሳዝናል!
ፆታን መሰረት ያደረጉ የሴቶችን እና ሕፃናትን የቤት ውስጥ ጥቃቶች በተመለከተ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ሴቶቹ በብዛት በትዳር አጋራቸው የሚደፈሩ ሲሆኑ ሕፃናት ሴቶች እና ወንዶች ደግሞ በቅርብ ይንከባከቡኛል፣ ከጥቃት ያስጥሉኛል በሚሏቸው ወላጅ አባቶች ወይም የቅርብ ዘመዳቸው መሆኑ ጉዳዩ ለአደባባይ የመብቃት እድሉ በጣም ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጎታል እንጂ ጉዳቱ ሪፖርት ከተደረገው በላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
በመዲናችን የቤት ውስጥ ጥቃቶች መበራከታቸውን ከሚያሳዩት መካከል በተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ድርጅት እገዛ እና በሰባት መንግሥታዊ ባልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እገዛ የተቋቋመው ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ 27 ሕፃናት ሰለባዎች መገኘታቸው አንዱ ማሳያ ነው።
በርግጥ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ የሚደርሰው ፆታዊ የቤት ውስጥ ጥቃቶች አዲስ ክስተት አይደሉም፤ ያሉና የነበሩ ልብ ሰባሪ ድርጊቶች ናቸው። እነዚህኞቹን ጥቃቶች ለየት የሚያደርጋቸው ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ብዙ አገራት ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል ከቤት ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴን መገደብ በመሆኑ የተነሳ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው አጥቂዎችና ተጠቂዎች በአንድ ላይ እንዲገናኙ ዕድል መፍጠሩ ነው።
የጉዳዩን አሳሳቢነት በተመለከተ ድምፃቸውን ቀደም ብለው ከፍ አድርገው ካሰሙት ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መካከል የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክትር ቴድሮስ አድሃኖም የሚገኙበት ሲሆን በኢትዮጵያ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መአዛ አሸናፊም ድምፃቸውን ቀድመው ካሰሙት መካከል ይገኛሉ። በርግጥም መንግሥታቶች ፆታዊ የቤት ውስጥ ጥቃቶችን በተመለከተ በልዩ ትኩረት ሊሠሩ ይገባቸዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት ፍርድ ቤቶች በከፊል እንዲሠሩ ተደርጓል። ይሁንና ፆታን መሰረት የሚያደርጉ የሴቶች እና ሕፃናት ጥቃት ግን እንዲታይ መደረጉ መልካም ሆኖ ሳለ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ግን ደፍረው ፍርድ ቤት እንኳን ከደረሱ በኋላ ችግሩ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደሆነ ይጠቀሳል። ይህንንም በማስረጃ ለማስደገፍ ከዚህ በፊት በፍርድ ቤት የታዩ ወይም በመታየት ላይ ያሉ ተመሳሳይ ጉዳዮች መጓተት ይታይባቸዋል። በመሆኑም ፍርድ ቤቶች እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ሲቀርቡ አፍጣኝ እና አስተማሪ ፍትሕ ሊሰጡ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። የሙያው ሰዎች አበክረው እንደሚናገሩት የዘገየ ፍትሕ እንዳልተፈጸመ ይቆጠራል የሚለውን ትልቅ መርኅ ስለሚጣረስ ነው።
በተጨማሪም ፖሊስ፣ አቃቤ ሕግ እና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አካላት የኅበረተሰቡ አካል በመሆናቸው ፆታን መሰረት ያደረጉ የሴቶች እና ሕፃናት የቤት ውስጥ ጥቃቶች ዙሪያ ግንዛቤያቸው ከፍ እንዲል በልዩ ትኩረት መሥራት የሚገባቸው ሲሆን በተለይ ሕግን ከማስፈጽም አንጻር ተጠርጣሪ አጥቂዎችን በትክክለኛው ሕግ እንዲቀጡ ማድረግ ላይ ክፍተት መኖሩን አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት እየሰጡ በመሆኑ ይህ ክፍተት በፍጥነት ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል።
በመጨረሻም በተለይ ጥቃቱን ከመከላከል አንጻር ከፍተኛ የግንዛቤ ለውጥ እንዲመጣ ማኅበረሰቡን ተደራሽ የሚያደርግ ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የግንዛቤ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች መሠራት ይገባቸዋል። በዚህ ረገድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራት እና መገናኛ ብዙኀን በቅንጅት መሠራት በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ መካከል ንቃት መፍጠር እና የባሕሪይ ለውጥ እንዲመጣ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013


