በክልሎች መካከል የሚታየው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ የሚፈታው በመንግሥት በተቋቋመው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ወደ ፊት በሚያቀርበው ጥናት ላይ ተመስርቶ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።
ፓርቲው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያበረክተውን የቃል ኪዳን ሰነድ ባሳለፍነው መጋቢት 14/2013 ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በተለይም ኢዜማ በሕዝብ ከተመረጠ ነው ብለዋል።
የኢዜማው መሪ ብርሃኑ ፖለቲካ መደራጀት ያለበት በጋራ አንድ በሆንበት ጉዳይ ላይ ተመስርቶ መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል። አክለውም ፖለቲካ በአንድነት ላይ ካልተመሰረተ የኢትዮጵያን ህዝብ በእኩል አይን ማገልገል የሚችል መንግሥት መፍጠር እንደማይቻል ጠቁመዋል።
“ፖለቲካን ከዘር፣ ከቋንቋና በብሔር ማንነት ጋር ማገናኘት የኢትዮጵያን ችግር ከመፍታት ይልቅ ያባብስዋል ።” ብለዋል መሪው።
ኢዜማ በምርጫው አሸንፎ መንግሥት የመሆን እድል ካገኝ በኢትዮጵያ አሁን ላይ የሚታዩትን የብሔርና የድንበር ይገባኛል ውዝግቦች እንዴት እንደሚፈታው ብርሃኑ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ችግሮቹ በኢትዮጵያዊነት ላይ ተመስርተው ካልተፈቱ በዘር ፖለቲካ በፍጹም ሊፈቱ አይችሉም ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
ብርሃኑ አክለውም ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከዘርና ከብሔር ፖለቲካ ወጥታ አንድነት ላይ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አካሄድ ካልተፈጠረ፣ ወደ ፊት የሚፈጠረው ከዘርና ከብሔር ግጭት አልፎ በየሰፈሩ ታጣቂ አሰልፎ ጦርነት መግጠም ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ኢዜማ በምርጫ የመንግሥትነት ስልጣን ከተረከበ የብሔር ፌዴራሊዝምን በማስወገድ የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት የሚያሳድግ ፌዴራላዊ ስርዓት እንደሚፈጥር ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ እድገትና አስተማማኝ ሠላም መፍጠር የሚያስችል የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ከብሄር ፖለቲካ መውጣት ይገባል ነው ያሉት ብርሃኑ።
በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ዜጎች በማንነታቸው ጥቃት ሲደርስባቸው የነበረውና አሁንም የቀጠለው ብሄርን መሰረት አድርጎ በፀደቀው ሕገ መንግሥት መሆኑን ብርሃኑ አስታውሰዋል። ኢዜማ በምርጫ የመንግስትነት ስልጣን ከተረከበ ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ሕገ መንግስቱ እንዲሻሻል እና ሀሳቡም ተቀባይነት ሲያገኝ የክልል [Federal Unit] መንግሥታትን አወቃቀር፣ የመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ ቋንቋ ባህል፣ ታሪክን፣ የሃብት ስብጥር እና ለብሔራዊ መግባባት አመቺ ሁኔታ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን አመላክቷል።
የዘንድሮው የ2013 አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖራት ከማድረግ ባሻገር በሕዝብ የሚመረጠው መንግሥት የሕዝቡን መሰረታዊ ችግሮች መፍታተ የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል። አክለውም በምርጫ ውስጥ መሰረታዊ ውሳኔ የሚሰጠው ሕዝብ ነው ብለዋል።
የኢዜማ የምርጫ 2013 የቃል ኪዳን ሰነድ ኢዜማ በምርጫው ማሸነፍ እድል ካገኘ ለአመስት ዓመት የሚሰራቸውን እቅዶች በዝርዝር አካቷል። ከቀረቡት የቃል ኪዳን ሰነዶች ውስጥ የብሔራዊ ደኅንነት፣ አገራዊ መሰረታዊ ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የውጭ ግንኙነት መሰረታዊ ችግሮችና መፍትሔዎችን አስቀምጧል።
ኢዜማ በብሔራዊ ደህንነት አሻሽላለሁ ብሎ ካስቀመጣቸው አሰራሮች አንዱ በክልሎች ውስጥ ተደራጁ ልዩ ኃይሎች በሙሉ በማፍረሥ አባላቱ በክልል ወይም በፌደራል ፖሊስ እንድካተቱ ማድረግ ይገኝበታል። በፖለቲካ ጉዳይ ኢዜማ አሻሽላለሁ ካላቸው መካከል ሠንደቅ ዓላማ ማሻሻል ሲሆን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ነው ብሏል።
በማኅበራዊ ጉዳይ ኢዜማ በትምህርት ዘርፍ አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ በሆኑባቸው አካባቢዎች ሌሎች የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ከእንግሊዘኛ ጋር ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጡ እንደሚያደርግ በ97 ገጾች አዘጋጅቶ ይፋ ባደረገው በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013



