በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በተፈጠረው ግጭት የተጠረጠሩ 81 ግለሰቦች በበላይ አካል ትዕዛዝ ተለቀዋል ተባለ

0
594

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ሥር የዋሉ 81 ተጠርጣሪ ግለሰቦች ከበላይ አካል በተሰጠ ትእዛዝና ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲለቀቁ መደረጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።

ተቋሙ መጋቢት 29/2013 ባወጣው መግለጫ በሰሜን ሽዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት የተጎዱ ዜጎችን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት መሰረት 303 ንጹሀን ዜጎች መሞታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ከትላንት ወዲያ ተቋሙ ባወጣው መግለጫው እንዳለው ከሆነ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 369 ሰዎች ሲሆኑ፣ የተፈናቀሉት ደግሞ ትክክለኛውን መረጃ ማረጋገጥ ባልችልም ኹለቱ ዞኖች በሰጡት መረጃ መሰረት ከ50 ሺሕ በላይ ንጹሐን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል። በግጭቱ ከሞቱና ከተፈናቀሉት ዜጎች በተጨማሪ ከአንድ ሺሕ 539 ቤቶች መቃጠላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ለተፋናቀሉ ዜጎች በሰሜን ሸዋ ዞን በተደራጀ መንገድ የእለት እርዳታ እና ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን በኦሮሚያ ልዩ ዞን ግን እየተደረገ ያለው ድጋፍ ዝቅተኛ ነው ብሏል። ሆኖም ግን በአቅርቦት ደረጃ በሁለቱም ዞኖች በቂ እንዳልሆነ ነው ተቋሙ የገለጸው።
የችግሩን ባለቤት መለየትና ተጠያቂ በማደረግ ረገድ 81 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እንዲያዙ ቢደረግም ከበላይ አካል በተሰጠ ትእዛዝና ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲለቀቁ ተደርገዋል ያለው ተቋሙ፣ በ2010 እና 2011 በተከሰቱ ችግሮች አጥፊዎች ተለይተው ሕጋዊ እርማጃ አለመውሰድ ለሕግ የበላይነት አለመከበር የራሱ ድርሻ ይኖረዋል ብሏል። በመሆኑም ችግሮች ሲፈጠሩ መረጃዎችና ማስረጃዎች ሳይጠፉና ሳይጨመሩ የምርመራ ቡድን እንዲገባ በማድረግ አጥፊዎችን በመለየት የሕግ የበላይነት ሊከበር እንደሚገባ የሕዝብ አንባ ጠባቂ ተቋሙ አሳስቧል።

ተቋሙ በኹለቱ ዞኖች የተከሰተው ግጭት ሕዝብ ለሕዝብ ነበር የሚል ግምገማ የለኝም ብሏል። በመሆኑም በግጭቱ ተሳትፎ የነበራቸው ከመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እስከ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው አካላት በሕግ እንድጠየቁ ጠይቋል።
“በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ከአከባቢው ሕብረተሰብ የበለጠ ባለቤት ስለሌለው የማይመለከታቸው አካላት ከጣልቃ ገብነት ራሳቸውን ቆጥበው ከብሄር አስተሳሰብ በመወጣት ኦሮሞም ይሁን አማራ ትግሬም ይሁን አኙዋክ የሚሞቱት ኢትዮጵያዊያን ናቸው የሚል አሰተሳሰብ በመያዝ ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ ይገባል ብሏል። በአንጻሩ የአንዱ ብሄር መፈናቀልና ሞት የእኔም ነዉ የማይሉና እንደራሳቸዉ ቆጥረዉ የማይጠይቁ ለራሳቸዉም ብሄር አይጠቅሙምና ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል።” ሲል ተቋሙ በመግለጫው አሳስቧል።

በአማራ ብሄራዊ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአማራ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ለዘመናት ተጋብቶና ተጋምዶ የሚኖር ሕዝብ መሆኑን ያስታወሰው ተቋሙ፣ በዘልማድ በግጦሽ እና በድንበር አካባቢ ከሚፈጠር ግጭት ባለፈ የከፋ ችግር ውስጥ ገብተው አያውቁም ብሏል። ሆኖም ግን ከባለፉት ሦሰት ዓመታት ወዲህ ግጭቱ ቅርጽና ይዘቱን እየቀየረ የብሄር እና የሃይማኖት መልክ እየያዘ መምጣቱን ከአካባቢው ሕብረተሰብ አረጋግጫለሁ ብሏል።

መጋቢት 10/2013 በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማ በተከሰተው ግጭት በሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ አመራሮች የችግሩን መንስኤ አስመልክቶ የተለያየ መረጃ ቢሰጡም በአከባቢው ከሚገኙ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኘው መረጃ መሰረት ግጭቱ በታጠቀ ሀይል እና በዘመናዊ መሳሪያ የተደገፈ እንደነበር ማረጋገጡን ተቋሙ ገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here