የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኮቪድ-19 ምክንያት ኪሳራ ላይ የወደቁ እና ተጨማሪ ወጪ ላጋጠማቸው ዩኒቨርሲቲዎች ያወጡት ወጪ እንዲተካላቸው ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትና ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ።
ኮቪድ-19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁንም ድረስ የኮቪድ-19 አገልግሎት የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ መኖራቸውን እና በተለይም በለይቶ ማቆያነት ያገለገሉ ዩኒቨርስቲዎች የተማሪ መኖሪያ ክፍሎቻቸው ጥገና እንደሚስፈልጋቸው እና ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ያወጡት ተጨማሪ ወጪ ምክንያት የበጀት ጉድለት እንደገጠማቸው ገልጸዋል።
ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ የበጀት ችግር የገጠማቸው የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ተጨማሪ በጀት እንደሚስፈልጋቸው ገልጸው፣ ላጋጠመው የበጀት ጉድለት ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ጥናት ማድረጉን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ጠቁመዋል።
በኮቪድ-19 ማቆያነት የተማሪ መኖሪያ ክፍሎች ላይ ጉዳት አጋጥሞናል ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሲሆን፣ ዩንቨርሲቲው በኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ ጉዳት የደረሰባቸውን የተማሪ መኖሪያ ክፍሎች ጠግኖ ወደሥራ ለማስገባት 26 ሚሊዮን ብር ፣ገንዘብ ሚኒስቴር እንድፈቅድለት ቢጠይቅም እስካሁን እንዳልተፈቀደለት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሀና(ፕ/ር) ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የጠየቀው በጀት ምላሽ ባለማግኘቱ ጥገና የሚስፈልጋቸው የተማሪ መኝታ ክፍሎች ሳይጠግኑ ባልተሟላ መሰረተ-ልማት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መገደዱን ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት። በዚህም የተማሪዎችን አገልግሎት ማሟላትና ማርካት አለመቻሉን የጠቆሙ ሲሆን፣ አሁንም ችግሩ ታይቶ መፈታትና ጥገና መደረግ አለበት ብለዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎችና ለሰራተኞች መስጠት የቻለው የኮቪድ-19 መከላከያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ፌስ ማስክ) ኹለት ኹለት ብቻ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በላይ ለማዳረስ የበጀት እጥረት እንዳለበት ተጠቁሟል።
ሌላኛው ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኛ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት አጋጥሞኛል ያለው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው ከኮቪድ-19 ጋር የተገናኙ ሥራዎች ላይ በጀቱን በማፍሰሱ ያለፉት ሦስት ወራት የሰራተኞች የደህንነት/ሪስክ/ ክፍያ አለመክፈሉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አያኖ በራሶ(ዶ/ር) ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በሪፈራል ሆስፒታሉ በሚሰጠው የኮቪድ-19 ሕክምና የኦክስጅንና የመድሐኒት እጥረት እንደገጠመውም ጠቁመዋል። በዚሁ የተነሳ ዩኒቨርሲቲው በሪፈራል ሆስፒታሉ መደበኛ ሕክምና ለመስጠት መቸገሩ ተመላክቷል።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም በበኩሉ የገጠመውን የበጀት እጥረት ለገንዘብ ሚኒስቴር በማስረዳት በጀት እንዲለቀቅለት ቢጠይቅም ገንዘብ ሚኒስቴር በጀት የለኝም የሚል ምላሽ መስጠቱን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።
የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶቹ በዘንድሮው በጀት ዓመት ኮቪድ-19 እና የኑሮ ውድነት ተደማምሮ ዩኒቨርሲቲዎችን ከፍተኛ የበጀት እጥረት ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲዎች አንድ ተማሪ ለመመገብ በቀን የሚያወጡት ወጪ 16 ብር ቢሆንም፣ አሁን ባለው የምግብ ፍጆታ የዋጋ ንረት ምክንያት ለአንድ ተማሪ በቀን የሚያወጡት ወጪ በኹለት እጥፍ እንደጨመረ ገልጸዋል። በአማካይ የአንድ ተማሪ የቀን ወጪ ከ30 እስከ 40 ብር መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህ የተነሳ የተማሪ በጀት የጨረሱ ዩኒቨርስቲዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
“አንድ ኪሎ በርበሬ በፊት እንገዛበት ከነበረው ከ75 ብር አሁን ላይ 250 ብር እየገዛን ነው። የተማሪ በጀት አልቋል። ምን እንደምንሆን አላውቅም።” ሲሉ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ብርሃኑ ገድፍ ገልጸዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013



