የመንግሥት ግዢ እና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በ5 ተቋማት ላይ ባደረገው ጥናት በርከታ ንብረት ተከማችቶ ያገኘ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በ189 የመንግሥት ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ደግሞ ቢሸጡ 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የሚያወጡ ንብረቶች ተከማችተው እንደሚገኙ አስታውቋል።
በተጨማሪም በትንሽ ወጪ ተጠግነው አገልግሎት ላይ መዋል የሚችሉ ንብረቶች ያለ አግባብ በመቀመጣቸው ሊወገዱ መሆኑን ሰጠኝ ገላን የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይህ የማስወገድ ዘመቻ የሚካሄደው በ 189 ባለ በጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ሲሆን፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ማለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቴሌ-ኮሚኒኬሽን፣ መብራት ሀይል፣ ባንኮች እና ኢንሹራንሶችን አይመለከትም ተብሏል።
እስከ አንድ ቢሊየን የሚደርስ ንብረት የማስወገድ ስራ ከተሰራ ገቢ ከማግኘትም በላይ የስራ እድል ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ሰጠኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የመንግስት ንበረት ምዝገባው ከሚያዚያ 4 አስከ 8/2013 በሀገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በምዝገባው ከሚካተቱ ዋና ዋና ንብረቶች መካከል ከትንሽ ጀምሮ እስከ ትልቅ ተሽከርካሪዎች፣ ማሽነሪዎች፣ ቁርጥራጭ ብረታብረቶች፣ ያገለገሉ ኮምፒውተሮች እና ላፕቶፖች፣ ማባዣ ማሽኖች እና ፕሪንተሮች እንዲሁም የቢሮ ቁሳቁሶች (ፈርኒቸሮች) ናቸው።
ይሕ ምዝገባ መካሄዱ በዋናነት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣በብልሽት ምክንያት አገልግሎት የማይሠጡ በርካታ ንብረቶች በፌደራል ተቋማት በመኖራቸው እና ወቅቱን የጠበቀ የአወጋገድ ስርዓት ባለመኖሩ የሚባክነውን የመንግስት እና የህዝብ ሃብት ለመታደግ፣ የአየር ንብረትን ለመከላከል እና የመንግስት ገንዘብ ማስገኘት የሚችለውን ጥቅም ለማስገኘት ሲሆን ለወደፊቱም ወቅቱን የጠበቀ የአወጋገድ ስርዓት ለመዘርጋት የታሰበ መሆኑን አቶ ሰጠኝ ጠቁመዋል።
በአብዛኛው የፌደራል መስሪያ ቤቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው የንብረት አስተዳደር ስርዓት ችግሮች ያሉበት ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ሀብቶች በየቦታው ወድቀው ለብክነት እየተዳረጉ በመሆኑ ማስወገድ ተገቢ መሆኑ ታምኖበታል።
የማስወገድ ዘመቻው የሚመለከታቸው ኤጀንሲው በስሩ የሚያስተዳድራቸው በአዋጅ 649/ 2001 መሰረት ባለበጀት መስሪያ ቤቶችን ብቻ እንደሆነ አቶ ሰጠኝ ተናግረዋል። ባለበጀት መስሪያ ቤት ማለት በገንዘብ ሚኒስቴር አመታዊ በጀት ተበጅቶላቸው በበጀቱ የሚተዳደሩ ተቋማት ሲሆኑ ከላይ የተጠቀሱት የልማት ድርጅቶችን አዋጁ አያካትትም።
ይህ አዋጅ ለ12 ዓመታት ያገለገለ በመሆኑ መሻሻል ስለሚያስፈልገው ኤጀንሲው አዋጁን በማሻሻል አዲስ ደንብ አውጥቶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ተመልክቶት፣ ጠቅላይ አቃቢህግ አፅድቆት፣ ለሚኒስትሮች ምክርቤት ባለፈው ህዳር ወር መላኩን አቶ ሰጠኝ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ይህ አዋጅ ሲጸድቅ የልማት ድርጅቶችም በኤጀንሲው እንደሚታቀፉ ተጠቁሟል። እንደ መብራት ሀይል እና ቴሌኮሚኒኬሽን ያሉ መስሪያቤቶች ውስጥ ሰፊ የሆነ የገመድ እና የትራንሰፎርመር ክምችቶች ይታያሉ።
በአዲሱ አዋጅ እነዚህ መስሪያ ቤቶች ሲካተቱ ኤጀንሲው ንብረቶችን በማስወገድ ገንዘቡን ጥቅም ላይ የማዋል ሰፊ ስራ እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ ነግረውናል።
በተጨማሪም ይህ የሚሻሻለው አዋጅ በክልሎች በየመንገዱ የሚገኙ ባለቤት የሌላቸው ሀብቶችን በማስወገድ ለመንግስት ትልቅ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
የአለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ የአገሪቱ የመንግስት 70 በመቶ የሚሆነው በጀት ለግዢ አገልግሎት የሚውል ሲሆን ቀሪው 30 በመቶ ለሰራተኛ ደሞዝ የሚያገለግል ነው።
ሀገሪቷ ከፍተኛ ግዢ የምትፈጽምባቸው ንብረቶች መካከል መድሃኒት፣ኬሚካሎች፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት እና የዩኒቨርስቲ ግብዓቶች ዋነኞቹ ናቸው።
ኤጀንሲው በመመሪያ ቁጥር 3/2003 መሰረት 6 የማስወገጃ መንገዶች ያሉት ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ሊጠቀምበት የታቀደው የማስወገጃ መንገድ መሸጥ እና ወደ ሌላ ተቋም ማስተላለፍ እንደሆነ ከኤጀንሲው ሰምተናል።
ለግብርና የሚውሉ ኬሚካሎች የመመረዝ ባህሪ ስላላቸው ለማስወገድ ተጨማሪ ዶላር የሚከፈል ሲሆን ይህንን ወጪ ለመቀነስ አካባቢን በማይበክል መልኩ ኬሚካሎቹን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ አቶ ሰጠኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፣ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት በተወጣጡ አጥኘዎች ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወጪን በቀነሰ መልኩ እንዴት ንብረትን ማስወገድ እንደሚቻል ጥናት እየተካሄደ ይገኛል ተብሏል።
ጥናት ከሚካሄድባቸው ጉዳዮች መካከል ኬሚካልን ማስወገድ በተመለከተ፣ አግሮ ኬሚካል ማለትም ለግብርና ምርቶች የሚውሉ ኬሚካሎች እና ኤሌክትሮኒክስ ውስጥ የሚገኙ እና የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች የሚወገዱበት መመሪያ ተዘጋጅቶ በኤጀንሲው አስተባባሪነት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተጠና መሆኑን አቶ ሰጠኝ ተናግረዋል።
በተያያዘ ተቋማት በዓመት እስከ ግማሽ ሚሊየን ብር የሚያወጡ ንብረቶችን ማስወገድ እንዲችሉ የሚፈቅድ መመሪያ ተዘጋጅቷል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ እንደገለፁት፣ ቀደም ሲል የነበረው መመሪያ በርካታ ክፍተት ስለነበሩበት ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ዕቃዎች ማስወገድ ላይ ችግር ፈጥሮባቸው ቆይቷል።
አዲስ የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ካልሆኑ በስተቀር ነባር ተቋማት በርካታ ንብረቶችን ያለ አገልግሎት አከማችተው እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ሐጂ፣ ግብርና፣ ጤና፣ ገንዘብ፣ ንግድ፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ከተቋቋሙበት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ንብረቶችን አጠራቅመው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
አዲሱ መመሪያ ከዚህ በፊት በነጠላ እስከ አንድ ሺህ ብር በጥቅል ደግሞ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚያወጡ ንብረቶችን ተቋማት እንዲያስወግዱ ይፈቅድ እንደነበር አመልክተው፣ በተሻሻለው መመሪያ በነጠላ ዋጋ አምስት ሺህ በጥቅል ደግሞ እስከ ግማሸ ሚሊየን ብር ማስወገድ እንዲችሉ ሥልጣን ይሰጣቸዋል ብለዋል።
የተሻሻለው መመሪያ ተከማችተው የሚገኙ ንብረቶችን በዘላቂነት ለማስወገድና ወደፊት ክምችት እንዳይኖር እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ መመሪያው በገንዘብ ሚኒስቴር ተፈርሞ በ185 የፌዴራል ተቋማት መሠራጨቱን አስታውቀዋል።



