የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ልዩ ባህሪና አሰራር ያገናዘበ የግዥ ሕግ እንዲወጣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ አቀረቡ።
የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶቹ ጥያቄውን ያቀረቡት አገሪቱ የምትጠቀምበት የግዥ ሕግ ከዩኒቨርሲቲዎች አሰራር ጋር የማይሄድ መሆኑን በመግለጽ ነው።
ጥያቄው የቀረበው መጋቢት 27/2013 የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማሳያ ይሆኑኛል ያላቸውን 10 ዩኒቨርሲቲዎች በአካል ተገኝቶ በተመለከተበትና ከየዩኒቨርሲቲዎቹ ማኅበረሰብ ጋር በመነጋገር ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ባላቸው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ጋር በመከረበት ጊዜ ነው።
ዩኒቨርሲቲዎች የአሰራር ባህሪያቸውን ያገናዘበ የራሳቸው የግዥ ሕግ እንድኖራቸው ከጠየቁት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሀና(ፕ/ር) አንዱ ሲሆኑ፣ ዩኒቨርስቲዎች በፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት አሰራር ከተቋማቱ ባህርይ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ የኦዲት ግኝቶች ለማስተካከል አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ብለዋል።
“የፌደራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ሥራዎችን የሚሰራው በተቀመጠው ሕግ መሰረት በመሆኑ እና ይህ የግዥ ሕግ ደግሞ ከዩኒቨርሲቲዎች ባሕርይ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው የግዥና የሰው ሀብት አስተዳደር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል” ሲሉ ተናገረዋል ። ምክር ቤቱ ሕጉን ለማስተካከል ጥረት እንዲየደርግም ጠይቀዋል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ብርሃኑ ገድፍ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰውን(ፕ/ር) ሀሳብ በመጋራት፣ የግዥ ሕጉ ከዩኒቨርሲቲዎች ባህርይ ጋር ካለመጣጣሙም ሌላ ዩኒቨርስቲዎቹ በተመሰረቱበት አከባቢ ላለው የማኅበረሰብ ክፍል የአቅራቢነት እድል የሚከለክል በመሆኑ ማተካካያ እንዲደረግበት የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል።
ለአብነትም ዩኒቨርሲቲያቸው በማእቀፍ ግዥ ሰበብ በአከባቢያቸው ሊያገኙ የሚችሏቸውን ትናንሽ የሚባሉ እንደ ሶፍትና እስኪርቢቶ የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ሳይቀር ከአዲስ አበባ እንዲገዙ መገደዳቸውን አንስተዋል።
በዚህም የተነሳ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግዥ ሕግና መመሪያ መጣስ በሚል ተጠያቂ እየሆነ ነው ብለዋል ። ብርሃኑ አክለውም መሥሪያ ቤቶች ባለመናበባቸው ችግር ውስጥ ገብተናል ብለዋል።
“የፌደራል ዋና ኦዲተር ችግሩ የዩኒቨርስቲው ባይሆንም ችግሩ እስከሚፈታ የኦዲት ግኝቱ ዩኒቨርስቲው ላይ ይቆያል ብሎናል” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል። በሕግና በመመሪያ መጣረስ ዩኒቨርስቲው የባንክ አካውንቱ እስከመዘጋት ድረሰ ችግር እየገጠመው መሆኑን ተመላክቷል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ታፈረ መላኩ(ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገጥማቸው የማይስተካከል የኦዲት ግኝት አሰራራቸውና ሕጉ ያልተናበበ በመሆኑ እንደሆነ አንስተዋል። ታፈረ እንደ ምሳሌ የሚያነሱትም ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎችን አገልግሎት ለማሟላት አስቸኳይ የምግብና ሌሎች አቅርቦቶች ሲያስፈልጋቸው የሚፈጽሙት ግዥ እንደ ኦዲት ግኝት እየተቆጠረ የተቸገሩ መሆናቸውን በማንሳት ነው። ታፈረ እንደሚሉት በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሚታየውን የኦዲት ግኝት አሰራር ለማስተካከልና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አሰራሩን በቅድሚያ መፈተሸ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲዎችን ልዩ ባህሪና አሰራር ተረድቶ የግዥና ፋይናንስ እንዲሁም የሰው ሀብትን የሚመለከት ሕግ ያስፈልጋል ብለዋል። ዩኒቨርስቲዎች የሚገለገሉበት የግዥ ሕግ እንደሚያስፈልግ የፕሬዝዳንቶቹን ሀሳብ የደገፉት ሚኒስትር ዴኤታው የግዥ ችግሮችን በ2014 በጀት ዓመት እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በዩኒቨርስቲዎች ላይ በሚደርገው የኦዲት ማጣርት በርካታ ግኝቶችን ማግኘቱና ማስተካካያ እንዲደረግባቸው በተደጋጋሚ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ አንዳንድ የኦዲት ግኝቶች የማይስተካከሉበት ሁኔታ እንደሚገጥም ዩኒቨርስቲዎቹ ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013


