የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የአገልግሎት ክፍያ ደንብን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አዲሱን የአገልግሎት ክፍያ ደንብን ከሚያዚያ 1/2013 ጀምሮ ወደ ስራ ሊገባ መሆኑን የቦርዱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበበ ሽፈራው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ደንቡ በሪፖርት አቅራቢ አካላት፣ የሂሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች እና ድርጅቶች በሙያ ማህበራት እና ፋይናንስ ሪፖርት መረጃ ፈላጊዎች አጥኚዎችን ላይ ተግባራዊ የሚሆን ነው።

የክፍያ ተመን ያስፈለገው ቦርዱ የሠው ሀይል በመመደብ እና ግብአቶችን በማሟላት ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ ወጪዎችን ለመሸፈን እና የክፍያ ስርዓቱም የሚከናወነው ማንኛውም ድርጅት፣ ባለሙያ እና ማህበራት አዲስ ፍቃድ ለማውጣት፣ ለማደስ እና ለመተካት ሲመጡ እንደሆነ ነው አቶ አበበ የተናገሩት።

ቦርዱ ለሚሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል የክፍያ ተመን በተመለከተ 11 ለተለያዩ አግለግሎቶች የሚከፈል ክፍያ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን ለፐብሊክ እና ለተመሰከረለት ኦዲተሮች አዲስ ፈቃድ ሲያወጡ 1330 ብር፣ ለእድሳት 780 ብር እንዲሁም ምትክ ለመውሰድ 400 ብር እንደሚከፈል ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም ለሂሳብ/ኦዲት የሽርክና ድርጅቶች እና ለተመሰከረለት የሂሳብ ባለሙያ አዲስ ፈቃድ ሲያወጡ 970 እና 1150 ብር፣ ለእድሳት 670 እና 750 ብር እንዲሁም ለመተካት 400 ብር ይከፍላሉ ተብሏል።
ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ የሒሳብ ሙያ ማህበራት እውቅና መስጠት እና እድሳት ከ6300 ብር እስከ 3500 ዶላር የሚከፍሉ ሲሆን ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ የሂሳብ ሙያ ማህበራት የምስክር ወረቀት መተካት ከ400 ብር እስከ 20 ዶላር እንደሚከፍሉ በአዲሱ አዋጅ ተመላክቷል።

ለሶስተኛ ወገን ሰነዶች መስጠት፣ የህዝብ ጥቅም ያለባቸውን አካላት የሂሳብ እና የአነስተኛ ወይም መካከለኛ ድርጅቶችን የሂሳብ መግለጫ መመዝገብ እንዲሁም የሪፖርት አቅራቢ አካላት የምዝባ የምስክር ወረቀት ከ5 ብር እስከ 685 ብር ድረስ እንደሚከፍሉ አቶ አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጥራት ያለው የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ በሀገራችን በሁሉም የግል፣ የመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተግባራዊ እንዲሆን ቦርዱ የሚሰራ ሲሆን የኢፌዲሪ መንግስት አለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን መተግበር ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት ያለውን ፋይዳ በመረዳት በአዋጅ ቁጥር 847/2006 መደንገጉ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ቦርዱ እንዳሰበው የአገሪቱ የሒሳብ አያያዝ፣ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ብሎም ኦዲት አሠራር የሚፈለገለው ደረጃ ላይ አልደረሰም።
በዚህም ምክንያት በ2006 በወጣ አዋጅ የተቋቋመው ቦርድ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት ሁሉም የመንግሥት ተቋማት እንደሚተገብሩት ይጠበቅ የነበረው አዲስ የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትም እንደሚፈለገው ባለመተግበሩ ባስቀመጣቸው ግዴታዎች ላይ ማሻሻያዎችን በማስቀመጥ ለማስተግበር ተጨማሪ አራት ዓመታት አስፈልገውታል።

ወጥቶ በነበረው የ5 ዓመት እቅድ ውስጥ ዓለም አቀፉን የሒሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ስታንድርድ ተከትለው የሒሳብ መዝገባቸውንም በዚሁ ሥርዓት ቀይረው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የቻሉት የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ናቸው።
ስለዚህ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወይም የበጎ አድራጎትና የሲቪክ ማኅራት ጭምር የሒሳብ አያያዛቸውን ሪፖርት የሚያደርጉበት ሥርዓት ከተዘረጋጋ ዓመታት ቢቆጠሩም እንደታሰበው የአብዛኞቹ ሒሳብ አቀራረብ ባለመለወጡ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ተብለው የተደለደሉና ይህንን የሒሳብ ሥርዓት መተግበር የሚጠበቅባቸው ግን ያልጀመሩ ተቋማት የአራት ዓመታት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።

ቦርዱ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት በማለት የዓለም አቀፉን የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓት እንዲተገብሩ የሚገደዱት በአራት መመዘኛዎችን ማለትም አመታዊ ገቢያቸው፣ እዳቸው፣ ሀብታቸው እና የሠው ኃይላቸው 50 ሚሊየን እና ከዚያ በላይ መሆን ሲችሉ እንደሆነ አቶ አበበ አብራርተዋል።

እንደ ቦርዱ ከሆነ ከፍተኛ የመንግሥት ጥቅም እንዳለባቸው የሚታሰቡ ተቋማት አራት ዋና ዋና መመዘኛዎች ተቀምጠውላቸዋል።
ከአራቱ ሁለቱን የሚያሟሉ ከሆነ፣የሒሳብ ሥርዓታቸው ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፉ የሒሳብ ሪፖርት ሥርዓት መሠረት እንዲሆን ይገደዳሉ።
ሃሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያጋሩት ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ ከፍተኛ ግብር ከፋይ አስመጪ እና ላኪ IFRS ለመተግበር እና አሰልጣኝ ቀጥሮ በድርጅቱ ተግባራዊ ለማድረግ እስከ 300 ሺ ብር ስለሚፈጅ እስከ አሁን ተግባራዊ አለማድረጋቸውን ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here