በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ምመህራን የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ ሊሰጣቸው መሆኑ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸው መምህራን ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት በመዝጋጀት ላይ መሆኑን በአዲስ አበባ ትምህርተር ቢሮ የትምህርትና መምህራን ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጌታሁን ለማ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ ትምህርት ቢሮው ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር መምህራን የመታወቂያ ተጠቃሚ እንድሆኑና የመምህራን መረጃ በተደራጀ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ውስት ላማካተት ያለመ ነው ብለዋል። ከተለያዩ አከባቢዎች መጥተው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሥር ተቀጥረው የሚሰሩ መምህራን ከሥድስት ወር በኋላ የነዋሪነት መታወቂያ እንዲያገኙ እየተደረገ እንደነበር ያስታወሱት ጌታሁን፣ አሰራሩ በየወረዳው የተለያየ፣ ወጥነት ያልነበረውና ሁሉንም መምህራን የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ ተጠቃሚ ያላደረገ ነበር ብለዋል።
አዲስ በመዘጋጀት ላይ ያለው የዲጂታል መታወቂያ ሁሉንም መምህራን ወጥነት ባለው አሰራር ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል። በዚህም ማንኛውም በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተቀጥሮ የሚሰራ መምህር ማግኘት ያለበትን አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችለው ነው የተገለጸው። ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር መምህራን ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ እያገኙ እንዳልነበር ነው የተመላከተው።
ትምህርት ቢሮው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጄንሲ ጋር በጋራ የሚያዘጋጀው የመምህራን ዲጂታል መታወቂያ ለአራት ዓመታት እንሚያገለግል ጌታሁን ገልጸዋል። በአዲሱ ዲጂታል የመምህራን የአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ በዋናነት ዓላማው መታወቂያ የሌላቸው እንድኖራቸው ማድረግ ቢሆንም፣ የነዋሪነት መታወቂያ የነበራቸው መምህራንም የዲጂታል መታወቂያው ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
ዲጂታል መታወቂያው አላማ መምህራን የነዋሪነት መታወቂያ ኖሯቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻል በተጨማሪ በአዲስ አበባ ትምህረት ቢሮ ሥር ያሉ መምህራንን ሙሉ መረጃ በዘመነ- ሥርዓት ለማደራጀት እንደሚጠቅም ተመላክቷል። በዚህም በትምህርት ዘርፉ ምን ያክል መምህራን እንዳሉ ከነ ሙሉ መረጃቸው ለማወቅ ያስችላል ተብሏል።
ለመምህራኑ የሚሰጠው ዲጂታል መታወቂያ መምህራን ባሉበት ቦታ በመታወቂያ የሚገኝ ማንኛውንም አይነት አገልግሎት ማግኘት እንደሚስችላቸው ተመላክቷል። ዲጂታል መታወቂያው በአሻራ የሚሰራ መሆኑን ጌታሁን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የመምህራን ዲጂታል መታወቂያ የማደራጀት ሥራው ሲጠናቀቅ ትምህርት ቢሮው የመምህራንን የተደራጀ ሙሉ መረጃ ማግኘት ያስችለዋል ተብሏል። እንዲሁም በመምህራን በኩል የሚነሳውን ወጥ የሆነ የአዲስ አበባ የነዋሪነት የመታወቂያ ተጠቃሚነት ጥያቄ ያስቀራል ተብሎለታል።
መምህራን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለመሆኑ ማቅረብ ያለባቸውን መረጃዎች በየትምህርት ቤቱ እያቀረቡ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያገኘችው ደብዳቤ ያስረዳል። መምህራን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለመሆን በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤት ሠራተኛ መሆናቸውን የሚገልጽ የቋሚነት ቅጥር ደብዳቤ፣ የደም ዓይነትና አንድ ጉርድ ፎቶ ማቅረብ እንዳለባቸው ተመላክቷል።
ከተማ አስተዳደሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘመናት በመምሀራን በኩል ሲነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ጌታሁን ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013



