በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤት መምህራን አንበሳ አውቶብስ የሚጠቀሙበት መታወቂያ ሊቀየር ነው

0
981

በአዲስ አበባ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተቀጥረው የሚሰሩ መምህራን ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረው የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኛ መታወቂያ በአዲስ ሊቀየር መሆኑ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚሰሩ መምህራን ሲጠቀሙበት የነበረው የአንበሳ አውቶቡስ መገልገያ መታወቂያ የሚቀየረው ከታለመለት አላማ ውጭ ጥቅም ላይ በመዋሉ ነው ተብሏል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና አንበሳ የከተማ

አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በጋራ ባደረጉት የመስክ ክትትል መታወቂያው ከተፈቀደላቸው የትምህርት ቤት መምህራንና የትምህርት አካላት ውጪ መታወቂያውን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት መታወቂያውን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ተገደናል ብለዋል።

ትምህርት ቢሮው ከአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ባደረገው ማጣራት፣ በርካታ መምህራን ያልሆኑ እና ጭራሹንም የመንግሥት ሰራተኛ ያልሆነ ሰው መታወቂያውን እየተጠቀመ እንደሆነ ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህር ቢሮ የመምህራን ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጌታሁን ለማ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ከሆነ መታወቂያውን መጠቀም የሚችሉት የመንግሥት ትምህርት ቤት መምህራንና ርዕሰ መምህራን ብቻ ቢሆኑም፣ በተመሳሳይ ታትሞ ግለሰቦች ሲጠቀሙበት እንደተገኘ ገልጸዋል።

መታወቂያን መጠቀም ከተፈቀደላቸው መምህራንና ርዕሰ ምምህራን ውጪ እንዳይጠቀሙበትና በተመሳሳይ ታትመው ግለሰቦች ሲገለገሉባቸው የነበሩ መታወቂያዎችን ከጥቅም ውጭ ማድረግ አስፈላጊ ሆኑ መገኘቱን ነው ዳይሬክተሩ የጠቆሙት። በተጨማሪም ከዚህ በፊት መምህራን ሲጠቀሙበት የነበረው መታወቂያ የትምህርት ቢሮው መለያ የሌለው እንደነበር ያስታወሱት ጌታሁን፣ አዲስ የሚታተመው መታወቂያ የትምህርት ቢሮወን መለያ የያዘ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራንና ርዕሰ መምህራን የትራንስፖርት አገልግሎት መታወቂያ መምህራን ከአንድ ትምህርት ቤት ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ሲዘዋወሩ የሚቀየር መሆኑን ጌታሁን አስታውሰዋል። አዲሱ መታወቂያ ማንኛወም በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚሰራ መምህር ከአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ወደ ሌላ የመንግሥት ትምህርት ቤት ሲዘዋወር መቀየር ሳያስፈልገው መጠቀም እንዲችል ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ መፊት መምህራን ሲጠቀሙበት የነበረው መታወቂያ ከአራት ዓመት በላይ ማገልገሉን የገለጹ ጌታሁን፣ አዲሱ መታወቂያ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንደሚያገለግል ጠቁመዋል። አዲሱ የመምህራን የትራንስፖርት አገልግሎት መታወቂያ በሚቀጥሉት ኹለት ሳምንታት ውስጥ ህትመቱ እንደሚጠናቀቅ ጌታሁን ጠቁመዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት የታተመው መታወቂያ ለ19 ሺሕ መምህራን እንደነበር ጌታሁን አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ ትምህርት ቢሮው የሚያስተዳድራቸው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራን ቁጥር በአሁኑ ስዓት 25 ሺሕ 734 መድረሱ ለአዲስ መለዳ ተጠቁሟል ። ኮቪድ-19 መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት ቢሮው ሦስት ሺሕ 500 ጊዜያዊ መምህራንን እንደቀጠረም ተገልጿል።

አዲስ የሚታተመው የመምህራንና የርዕሰ መምህራን የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ የትራነስፖርት አገልግሎት መታወቂያ ለ25 ሺሕ 734 ቋሚ መምህራን ለሦሰት ዓመትት የሚገለግልና በጊዜያዊነት ለተቀጠሩ ደግሞ ቅጥራቸው እንስከሚጠናቀቅበት ድረስ የሚጠቀሙበት እንደሆነ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ጋር በገባው ውል መሰረት ለአንድ መምህር በቀን ስምንት ብር እንደሚከፍል ጌታሁን ጠቁመዋል። ቢሮው አዲሱን መታወቂያ ለማሳተም 60 ሺሕ ብር ወጪ እንደሚደርግም ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 129 ሚያዚያ 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here