ከመተከል ዞን ተፈናቅለው ቻግኒ የሚገኙ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ቦታ ለመኖር አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገለጹ

0
969

በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ የታጣቂ ኃይል ጥቃቶች ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ዞን ቻግኒ በሚገኘው ራንች መጠለያ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ቦታ ለመኖር አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ተፈናቃዮች ከመተከል ዞን ቤት ንብረታቸው ትተው ተፈናቅለው በአማራ ክልል አዊ ዞን ቻግኒ ላይ የተጠለሉበት ራንች መጠለያ በዝናብ ምክንያት በውሀ መጥለቅለቁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በዝናብ ምክንያት በውሃ የተጠቃው የተፈናቃዮች መጠለያ ተፈናቃዮቹን ለከፍተኛ ችግር እንዳጋለጣቸው ተመላክቷል።

ተፈናቃዮቹ ሰሞኑን በጣለው ዝናብ ምክንያት የተጠለሉበት መጠለያ ውስጥ ውሃ በመግባቱ ለሶስት ቀናት በዝናብ ውሃ በተጥለቀለቀ መጠለያ ውስጥ ለማደር መገደዳቸወን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ተፈናቃዮቹ ተጠልለው የሚገኙበት መጠለያ ምቹ አለመሆኑን ተከትሎ የተፈናቃዮች ችግር እየተባባሱብን ነው ብለዋል። ተፈናቃዮቹ ያሉበተን ሁኔታ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፣ “ከስቃዩ ወጥተን ወደ ሌላ ስቃይ ገብተናል” ብለዋል። ተፈናቃዮቹ ይህን ያሉበት ምክንያት ያሉበት ሁኔታ በረካታ ፈተናዎች የተደቀኑበት መሆኑን በመጥቀስ ነው።

በመጠለያ ጣቢያው በዝናብ ምክንያት ካጋጠመው ችግር በተጨማሪ ለኑሮ የሚሆኑ መሰረታዊ ነገሮች አለመሟላታቸው ለተፈናቃዮች ሌላ ፈተና መሆኑንም ተናግረዋል። በአካባቢው የመንግሥት አካላት በኩል ያለው የስደተኞች አያያዝ ጥሩ የሚባል እንዳልሆነም ተመላክቷል።

በአዊ ዞን ቻግኒ ተጠልለው የሚገኙ የመተከል ተፈናቃዮች የገጠማቸውን የመጠለያ ቦታ አለመመቸት ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት አማራጭ ሀሳብ ያለውን ማቅረቡን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ይሄውም ከተፈናቃይ ተወካዮች ጋር በተደረገ ውይይት ተፈናቃዮቹ ካሉበት ችግር እንዲወጡ ያስችላል የተባለ ሀሳብ መቅረቡ ተነግሯል።

አማራጭ ሀሳቡም ተፈናቃዮቹ አሁን ላይ ከተጠለሉበት መጠለያ ቦታ በማንሳት ወደ ተለያዩ ወረዳዎች መበተን እንደሆነ አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ተፈናቃዮቹ በተለያዩ ወረዳዎች ተጠልለው እንዲቆዩ በቀረበው ሀሳብ መነሻነት ተፈናቃዮቹ በሚሄዱበት ቦታ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተመላክቷል።

ይሁን እንጂ ተፈናቃዮቹ ጥያቄውን እንዳልተቀበሉት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ወደ ተለያዩ ወረዳዎች መበታተኑን ያልተቀበሉት ተፈናቃዮቹ፣ ከተበተን በኋላ የሚጠይቀንና ድጋፍ የሚያደርገልን አካል እናጣለን በሚል ስጋት እንደሆነ ገልጸዋል። በመሆኑም ተፈናቃዮች ካሉበት ቦታ ሳይበታተኑ የተሻለ መጠለያ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ተፈናቃዮች ከመንግሥት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ አነስተኛ እንደሆነም ጠቁመዋል። በአንጻሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ የተራድኦ ድርጅቶች የመጠለያ እና የተለያዩ ድጋፎች እያደረጉላቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። አሁን ላይ የገጠማቸውን የመጠለያ ችግር ለመፍታት ‹አክሽን ፎር ዘ ኒዲ ኢትዮጵያ› ለ1000 ሺሕ አባወራዎች የድንገተኛ መጠለያ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ተገልጿል። በቻግኒ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ40 ሺህ አስከ 50 ሺሕ እንደሚሆን ተገምቷል።

በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ወደ ተሻለ ሁኔታ በመመለስ ከመተከል የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አከባቢያቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው ቢባልም እስካሁን ችግሩ እንደቀጠለ ነው። የሰላም ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በአስቸኳይ እንዲመለሱ አደርጋለሁ ቢልም ችግሩ እየተባባሰ አስካሁን ቆይቷል።

የተፈናቃይ ዜጎችን ሕይዎት በችግር ላይ ችግር የሚያደረገው ሌላኛው ጉዳይ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ አካባቢያቸው ተመልሰው የእርሻ ሥራ ለማከናወን አለመቻላቸው ወደፊትም ለተረጅነት የሚያጋልጣቸው መሆኑም ጭምር እንደሆነ ጠቁመዋል። ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው እርሻ ሥራ የማያከናውኑ ከሆነ ችግራቸውን የተራዘመና የተባባሰ እንደሚያደርገው ሥጋታቸውን ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here