ሰሞነኛ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮችም ሆነ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ትኩረት እና መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ቀደም ሲል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ‹ሕወሓት› እና ‹ሸኔ› የተባሉ ቡድኖች በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡ ነው። ይህንንም ተከትሎ ኀሙስ፣ ሚያዚያ 28 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ድምጸ ተኣቅቦ በስተቀር በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ኹለቱ ቡድኖች ሽብርተኛ በመባል ተፈርጀዋል።
አንዳንዶች የሚኒስትሮች ምክር ቤትን የውሳኔ ሐሳብ በሰሙበት ቅጽበት ‹‹አልዘገየም ወይ?›› የውሳኔ ሐሳቡ መቅረቡ ተጠባቂ ብቻ ሳይሆን የዘገየ ነው በሚል ሂሳዊ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ሌሎች ደግሞ የዚህ ዳርዳርታ የቀደመውን የሕወሓት መንግሥት መድገም እንዳይሆን ሲሉ ‹‹ንጹሃን ተቃዋሚዎችን የማሸማቀቂያ እንዲሁም የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን›› ሲሉ ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል። በሌላ በኩልም የብዙዎች ጥያቄ ‹‹ሕወሓት የሚባል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱን የተነጠቀ ድርጅት ሲሆን ‹ሸኔ› የሚባለው ደግሞ ጭርሱኑ ሕጋዊ ሰውነት ያልነበረው ቡድን ሆኖ ሳለ እንዴት ሽብርተኛ ተብለው ይፈረጃሉ?›› የሚለው ጎልቶ የተሰማ ጥያቄ ነበር። በተለይ መረራ ጉዲናን (ፕሮፌሰር) ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ‹ሸኔ› በሚል ሥም የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት በሌለበት አሸባሪ ብሎ መሰየም ተገቢነት የለውም ሲሉ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የፌደራል ዋና ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቴሌቪዠን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አንድን ድርጅት ሽብርተኛ ለማለት የግድ ሕጋዊ ሰውነት ሊኖረው አይገባም በማለት የሕወሓት ቀደም ብሎ ከምርጫ ቦርድ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር መሰረዝም ሆነ ‹ሸኔ› በሚልና በሌሎች ሥሞችም የሚታወቀው፥ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ያልተሰጠው ስብስብ መሆን ውሳኔውን ሊያስቀለብስ የሚችልበት ሁኔታ የለም ሲሉ የፈጸሟቸው የወንጀል ድርጊቶች ናቸው ታሳቢ የሚደረገው ሲሉ የብዙዎችን ብዥታ በግልጽ ቋንቋ አስቀምጠዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሓትን እና ሸኔን ሽብርተኛ ብሎ ከመሰየም ባሻገር ልዩ ትኩረት በመሳብ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃው አንድ የምክር ቤቱ አባል ድምጸ ታኣቅቦ ማድረጋቸው ነው። ድምጸ ታኣቅቦ አድርገዋል የተባሉት የምክር ቤት አባል የኦሮሞ ብልጽግና አባል ወይዘሮ ሌሊሴ በቀለ ሲሆኑ እጃቸውን አጣምረው፣ የፊትና አፍንጫ ጭንብላቸውን አጥልቀውና ጸጉራቸውን ሸፍነው እንደተቀመጡ የትዝብት ከሚመስለው የፊት ገጽታቸው የሚያሳይ እዛው በምክር ቤቱ ውሳኔ ወቅት የተነሱት ፎቶ በሰፊው በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ተሰራጭቷል።
ከፎቶው መሰራጨት ጎን ለጎን የምክር ቤቱ አባል በሰጡት ድምጸ ተኣቅቦ ምክንያት የብዙዎች ሙግትና ክርክር ርዕሰ ጉዳይ ሆነዋል። በርግጥ ጌታቸው ሽፈራው የሚባሉ አንድ የፌስቡክ ታዋቂ ተጠቃሚ ‹‹ትህነግ እና ኦነግ ሸኔ በአሸባሪነት እንዲፈረጁ የቀረበው ውሳኔ ሲጸድቅ ብቸኛዋ የተኣቅቦ ድምጽ ያስመዘገበችው . . . ጋዜጠኞች ለምን ተኣቅቦ እንዳደረገች ሲጠይቋት መልስ ሳትሰጥ በጥድፊያ ወጥታለች ተብሏል።›› በሚል ጉዳዩ ጋር የተያያዘውን ያገኘውን መረጃ አጋርቷል።
የሕግ ባለሙያ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት መሐመድ አሊ መሐመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ‹‹So what? ድምጸ ተኣቅቦ ማድረግ መብቷ ነው። ይሁንና ድምጸ ተኣቅቦ ያደረገችበትን ምክንያት ግልጽ ማድረግ ይጠበቅባታል። ሐሳቧ በልዩነት ተመዝግቦ በክብር ይቀመጣል። እንደ ሕዝብ ተወካይ ዝም ብሎ እጅ አጣጥፎ መቀመጥ አይነፋም። ምናልባትም የመናገር ዕድሉን አላገኘችም ይሆናል።›› የሚል አስተያየታቸውን አስነብበዋል።
ውብሸት ታዬ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚም በበኩላቸው፥ የሴትየዋ ድምጸ ተኣቅቦ እንዲህ ሊያነጋግር ባልተገባ ሲሉ በምክር ቤቱ አባላት መቶ የተቃውሞ ድምጽ እንኳን ቢሰጥ ውሳኔውን የመቀልበስ ኀይል የለውም የሚል መከራከሪያ አንስተው የጉዳዩን ቀሊልነት አስገንዝበዋል። ይህ እውነታ ባለበት ተቃውሞ ያላሰሙ አንድ ሴት እንዴት ይህንን ያክል ትኩረት ሊስቡ ቻሉ በማለት የሚጠይቁት ውብሸት፥ ‹‹ለእኛ አጀንዳ ለመስጠት የተቀመረች ጨዋታ ናት ብሎ መጠርጠር ይቻላል ነበር።›› ሲሉ የልዩነት ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ብዙዎች ግን አሁንም የሚጠይቁት የኹለቱ ድርጅቶች በሽብርተኛነት መፈረጅ የዜጎችን ሰቆቃ፣ ግድያ፣ ስደት፣ ዘረፋ፣ የሀብት ውድመት፣ የሰላም መደፍረስ ያስቆመው ይሆን ሲሉ ይጠይቃሉ። የኹለቱ ቡድኖች በሽብርተኝነት መፈረጅ በርግጥም በየቦታው የሚታየውን የዜጎች መኖር እና በነጻነት መዘዋወር መብቶች በተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ይሆን ሲሉ አሁንም ይጠይቃለሁ። ይዋል ይደር እንጂ ለሁሉም ጊዜ ሚዛን መልስ ይኖረዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013


