ሚያዚያ 27/2013 ለ80ኛ ጊዜ የተከበረውን የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ቀን በማስመልከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ያዘጋጀው አርበኞችን የሚዘክር ዐውደ ርዕይ ለተመልካች ዕይታ ክፍት ሆኗል።
በኤጀንሲው ተጠብቀው የሚገኙ፣ በጦርነቱ የተሳተፉ እና የጀግኖች አርበኞችን ፎቶ ግራፎች እንዲሁም መዛግብቶች በዐውድ ርዕዩ ላይ ለዕይታ የበቁ ሲሆን፣ ይህ መሰናዶ እስከ ግንቦት 1 ቀን 2013 ቆይታ እንደሚኖረው ተነግሯል።
በኤጀንሲው የመዛግብት እና የጽሑፍ ቅርስ አስተዳደር ዳይሬክተር ገረመው ከበደ፤ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ ‹‹ይሄ ቤት ትውልድ አገናኝ ነው።›› ሲሉ ንግግራቸውን ጀምረዋል። አያይዘውም አውደ ርዕዩ ቀደምት አባቶች የሠሩትን ገድል፣ ጀግንነት እና ድል የሚያሳዩትን ፎቶግራፎችን በማቅረብ አሁን ያለው ትውልድ እንዲያውቀው አልሞ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹አሁን ያለው ትውልድ አውቆ እንዲሁም ተምሮ የዚህችን አገር አንድነትና ክብር እንዲያስጠብቅ በማሰብ እንዲማርባቸው አውደ ርዕዩን ማዘጋጅት አስፈልጓል›› ሲሉም አክለዋል። ዐውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡ ፎቶግራፎችም ይሁን መዛግብቶች፤ በኹለተኛው የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት ጀግና የኢትዮጵያ አርበኞች የሠሩትን ድል ለማሳየት የተዘጋጅ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። እንዲሁም ያለፈውን ትውልድ እና አሻራ አሁን ያለው ትውልድ እንዲያስቀጥል ለማድረግ መነሻ ይሆነው ዘንድ ታስቦም ተዘጋጅቷል ብለዋል።
በአውደ ርዕዩ ከሚታዩ ፎቶግራፎች መካከል ጣሊያን ኢትዮጵያን በ1928 ወርራ በነበረበት ወቅት የተሳተፉ አርበኞች ምስል የሚያሳዩ ይገኙበታል። የፎቶግራፉ እና የመዛግብቱ ስብስብ በዋናነት ጦርነቱ እንዴት ተጀመረ? ሂደቱ ምን ይመስል ነበር? ፍጻሜውስ ምን ይመስላል? የሚለውን የሚተርክም ነው።
ዐውደ ርዕዩ ከኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን የተነሱ አርበኞች የነበራቸውን ተሳትፎ የሚሳይ እንደሆነ ገረመው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንዲሁም በአድዋ ጦርነት እና በኹለተኛው የኢትዮጵያ ጣሊያን ጦርነት ላይ የተሳተፉት እንደ ባልቻ አባ ሳፎ እና የሃዲያው ተወላጅ ፊታውራሪ ጌጃ ጋርቦም በዓውደ ርዕዩ ለታሪክ ምስክርነት ምስላቸው ቀርቧል።
ኤጀንሲው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የያዘውን ክምችት ለሕዝብ ተደራሽ የሚያደርግባቸው መንገዶች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ ዐውደ ርዕይ ማዘጋጀት ነው።
‹‹ይህ ዐውደ ርዕይ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ሌሎች ዝግጅቶችን በማቅረብም ኤጀንሲው ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከትላንት ያገናኛል። የትውልድ አገኛኝ በመሆኑም ዘላለማዊት ኢትዮጵያ እንድትኖረን ተቋማችን ትልቅ ሚናውን ይጫወታል›› ብለዋል፤ በኤጀንሲው የመዛግብት እና የጽሑፍ ቅርስ አስተዳደር ዳይሬክተር ገረመው።
የአርበኞች ቀን
ጣልያን በአድዋ ድል ከተመታች በኋላ ሽንፈቷን በጸጋ አልተቀበለችም። ይልቁንም ከ40 ዓመታት በኋላ በ1928 ኢትዮጵያን ወርራለች። ኢትዮጵያውያን አርበኞችም ወራሪውን ኃይል ለአምስት ዓመታት በፅናት በመታገል ድልን አግኝተዋል።
አምስቱ የወረራ ዓመታት ታድያ ቀላል አልነበሩም። ወራሪው ጣልያን በኢትዮጵያውያን ላይ እጅግ አስከፊ ግፎችን ሲፈጽም ነበር። የተለያዩ ሰነዶችን ስናገላብጥ ይህን በሚመለከት ‹‹ዓለማቀፋዊ ኅብረት ለፍትህ – የኢትዮጵያ ጉዳይ› የተባለ ድርጅት የአምስቱን ዘመን የጣልያንን ግፍና የኢትዮጵያውያንን መከራ በተመለከተ ያዘጋጀውን ጥናታዊ ጽሑፍ አገኘን።
በዛ መሠረት በአምስቱ ዓመታት አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። እጅግ በርካታ አብያተ ክርስትያናት እንዲሁም ከግማሽ መሚሊዮን በላይ የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋልም ይላል። ከተፈጸመው ዘረፋ በተጨማሪ 1 ሚሊዮን እንስሳት ሲገደሉ፣ የጣልያን ጦር በረጨው የመርዝ ጋዝ የአካባቢ ብክለትን ጨምሮ ብዙ ጥፋቶች ደርሰዋል።
እዚህ ላይ የካቲት 12ን መርሳት የሚቻል አይደለም። በአዲስ አበባ ብቻ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተደረገ ግድያና ማሰቃየት ከ30 ሺሕ በላይ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ይታወቃል። አርበኞች ግን ለዚህ ሁሉ መከራ እጅ አልሰጡም። አንዱ ሲሰዋ ሌላው እየተተካ፣ በጽናት ተጋድለው በመጨረሻም ለአሸናፊነት በቅተዋል።
ዘንድሮ ማለትም 2013 የአርበኞች ቀን 80ኛ ዓመቱ ነው። ይህንንም በዓል ምክንያት በማድረግ ረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን ጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ላይ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል። እንዲሁም እንደ ወትሮው በድል ሐውልቱ ስር አባትና እናት አርበኞች፣ የአርበኞች ማኅበር ተወካዮች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የአበባ ጉንጉን ተቀምጧል፣ አርበኞች ታስበዋል።
በዚሁ እለትም ጀግኖች አርበኞች የሚገባቸውን ክብር እንዲሰጣቸው ለማስቻል በከተማዋ በሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መፈቀዱን ምትክል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013