በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባልተጀመረባቸው የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ለማከናወን የጸጥታ ችግሮች እንቅፋት በሆነባቸው አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13/2013 ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲራዘም ወስኗል። በዚህም መሠረት በምዕራብ ወለጋ ዞን (ከቤጊ እና ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል ውጪ)፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን (ከአያና እና ገሊላ ምርጫ ክልል ውጪ)፣ በቄለም ወለጋ ዞን እና በሆሮ ጉድሩ ዞን (ከአሊቦ፣ ጊዳም እና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል ውጪ) ከሚገኙት 31 ምርጫ ክልሎች መካከል በ24ቱ ላይ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በካማሽ ዞን ከሚገኙት አምስት የምርጫ ክልሎች በአራቱ (ከሴዳል ምርጫ ክልል ውጪ) የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13/2013 ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ወስኗል።
ከዚህም በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ በጸጥታ ችግር የተነሳ ሳይከናወንበት የነበረው በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔር ልዩ ዞን የሚገኙት ዳዋ ጨፌ፣ ጨፋ ሮቢት እና ባቲ ምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13/2013 ድረስ ይከናወናል ተብሏል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



