አስመጪዎች በዶላር እጥረት ከውጪ መኪና እንደማያስገቡ ገለጹ

አስመጪዎች በዶላር እጥረት ከውጭ የሚገባ መኪና እንደማይኖራቸው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናገሩ። ለዚህም ምክንያቱ የዶላር አለመኖር እና የሀገር ውስጥ ምርት ተጠቀሙ የሚለው መመሪያ መሆኑን ነው የገለጹት። የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የባንኮችን ደጃፍ የሚረግጡት አስመጪዎች፤ ‹‹ሌተር ኦፍ ክሬዲት›› ለመክፈት እና ማስመጣት የሚገባቸውን ምርት ለማምጣት ባለመቻላቸው፤ ሥራችን እየተስተጓጐለ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል:: ስም መግለጽ ያልፈለጉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩ ከ10 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የመኪና አስመጪ ድርጅት ባለቤት የዶላር እጥረት አስመጪዎችን ከጨዋታው ውጪ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸውልናል።

‹‹መኪና ካስመጣ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢው በአሁኑ ሰዓት አስመጪ ነኝ ለማለት አፍራለሁ›› ብለዋል። መንግስት አንድ ሰሞን አውጥቶት የነበረውን የሀገር ውስጥ ምርት መጠቀም የሚለው መመሪያ በራሱ ትልቅ የኢኮኖሚ ጫና እያሳደረባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል። ቅሬታ አቅራቢው አክለውም ብሄራዊ ባንክ ዶላር ለማግኘት ወረፋ ከያዝኩ ብዙ ጊዜያት አልፈዋል ሲል ገልጿል። ‹‹መኪና ለማስመጣት ዶላር ስንጠይቅ በጣም ረጅም ወረፋ ጠብቀንም አናገኝም ፤ እሺ የሀገር ውስጥ ምርት እንጠቀም ስንል ደግሞ ከአመታት በላይ ወረፋ መጠበቅ እንዳለብን ይነገረናል›› ሲሉ ያማርራሉ።

ቅሬታ አቅራቢው ከሀዮንዳይ መኪና ለመውሰድ ጠይቆ የነበረ ሲሆን አንድ አመት ተኩል ጊዜ ወረፋ መጠበቅ እንዳለበት ተነግሮታል። በአንድ ወቅት በቂ የውጭ ምንዛሪ ያለ መሆኑ ቢገለጽም፣ አሁን በተጨባጭ የሚታየው እውነታ ግን በተቃራኒው ሆኗል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ተንታኝ የሆኑት ዋሲሁን በላይ እንደተናገሩት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለዓመታት የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግር ሆኖ ዘልቋል። የአገሪቱ የተዛባ የንግድ ሥርዓት በተለይም የወጪና የገቢ ንግድ አለመመጣጠን ለእጥረቱ መባባስ ምክንያትም ሆኗል ይላሉ።

ዋሲሁን አክለውም መንግሥት ለሚያካሂደው ወታደራዊ እርምጃ የዶላር ፍላጎት ስለሚኖረው ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት ወጪ የሚያደርገው ዶላር ለሌሎች ገቢ ንግዶች የሚውለውን ስለሚሆን እጥረቱን ያጎላዋል ብለዋል። ይህ እጥረት በምጣኔ ሃብቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ በማሳረፉ በርካታ ፋብሪካዎችንና ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ፣ እንዲሁም ህልውናቸውን ፈተና ላይ ጥሎታል ሲሉ አንስተዋል። ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ፣ በብድር፣ በእርዳታ እንዲሁም ከውጭ አገራት በሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) የምታገኘው ገንዘብ ተጠራቅሞ ለገቢ ንግድ ከምትፈልገው ዶላር በእጅጉ ያነሰ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ያስረዳሉ።

ብር ከዶላርም ሆነ ከሌሎች የመገበያያ ገንዘቦች አንፃር መድከም በዓመታት ውስጥ የታየ እንደሆነ ምሁሩ ይናገራሉ፤ ይህም አገሪቷ እየተከተለችው ካለው ፖሊሲ አንፃር ብር ተገቢውን ዋጋ እንዲይዝ (ዲቫሉዌት) ከማድረግ ጋርና በተለይም የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት ጋር እንደሚያያዝ ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ 2000 ሚሊኒየም ከመግባቱ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ባንኮች አንድ ዶላርን ከ8 እስከ 9 ብር ገደማ ይመነዝሩ ነበር። በዓመታት ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ የመጣው የምንዛሪ ተመን ንሮ አንድ ዶላር በ42 ብር እየተመነዘረ ነው። ይህ የምንዛሬ ተመን በኢትዮጵያ ይፋዊ የባንክ ግብይት መሰረት ነው። ነገር ግን በተለምዶ ጥቁር ገበያ በሚባለው ምንዛሬ ተመን መሰረት አንድ ዶላር 55 ብር እና ከዚያ በላይ እንደሆነ ተሰምቷል።

ግጭቶች ሲኖሩ አገሪቱ የምታወጣው የውጭ ምንዛሪ ይኖራልና ነጋዴ የሚፈልገውን ያህል አያገኝም” በብዛት ካለ ደግሞ ዋጋው እንዲሁ ያሽቆለቁላል።አለመረጋጋት በሚኖርበት ወቅት የሸቀጦች አቅርቦት ችግርም ስለሚፈጠር፤ እቃ ማከማቸት እንዲሁም የዋጋ መናርም እንደሚያስከትል ዋሲሁን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። አገሪቱ በየወሩ የምታስመዘግበው የዋጋ ግሽበት ከ20 በመቶ በላይ በመሆኑ በዜጎች ላይ እያሳረፈ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ ሆኗል። ከዋጋ ግሸበትም ጋር ተያይዞ መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ዋጋ መናርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ረዥም ተራ በመጠበቅ በሚገኘው ዕድል እንኳን የሚሰጠው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ በመሆኑ፣ ለዕለት ፍጆታ የሚሆኑና አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ምርቶችን አስመጥቶ ወደ ገበያ ለማስገባት አልተቻለም ብለዋል:: የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አክለውም ‹‹ችግሩ ጊዜያዊ ነው እንዳይባል፤ ችግሩ ማጋጠም ከጀመረ ሳምንታት ሳይሆን ወራት ተቆጥረዋል። መቆሚያው መቼ እንደሆነም ለመተንበይ እንኳን አልተቻለም:: ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም በውጭ ምንዛሪ ዙሪያ የተፈጠረውን ክፍተት አስመልክቶ ምንም ዓይነት መረጃ እየሰጠ አለመሆኑ፣ ችግሩ ነገም ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት እያሳደረ ነው›› ብለዋል:: ይህም ፤የሸቀጦችን ዋጋ በማናር፤ እንዲሁም በእጥረቱ ሳቢያ የሚፈለገውን ያህል ምርቶች አለመግባታቸው የምርት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ አጠቃላይ ኢኮኖሚው እንደሚቃውስ ዋሲሁን ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here