በ‹‹ኢትዮጵያ ሳምንት›› ኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫል 10 ሺሕ ጎብኚዎች ይጠበቃሉ

ከግንቦት 10 እስከ 16 በሚካሄደው የኢትዮጵያ ሳምንት ኤግዚቢሽን እና ፌስቲቫል 10 ሺሕ ጎብኝዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገዛኸኝ አባተ የኢትዮጵያ ሳምንት የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ቡድን አስተባባሪ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህ ፌስቲቫልና ኤግዜቢሽን ለአንድ ሳምንት ክፍት የሚሆን ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ላይ ለመሳተፍ ለአዋቂዎች 200 ብር፣ ለተማሪዎች 50 ብር ለመግቢያ የሚከፈል ሲሆን፣ ህጻናት በነፃ መታደም ይችላሉ ተብሏል። በዚህ የወዳጅነትና የአብሮነት ኩነት የሚገኘው ገቢ በተለያዩ ምክንያት ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ለተፈናቀሉ ዜጎች ማቋቋም ሥራ ላይ ይዉላል በማለት ገዛኸኝ አሳውቀዋል።

ዝግጅቱ ላይ ይታደማሉ ተብሎ ከተቀመጠው ቁጥር ግማሽ ያህሉ ተማሪዎች እና ግማሽ ያህሉ አዋቂዎች ቢሆኑ እንኳን ከፌስቲቫሉ 1 ነጥብ ኹለት ሚሊየን ብር እንደሚገኝ ይገመታል። ለዚህ ፌስቲቫል የሚሆን ወጪ ከተለያዩ አጋር አካላት እና ባለ ሀብቶች የተገኘ ሲሆን፣ ለፌስቲቫሉ የሚሆኑ ጊዜያዊ ስፍራዎችን ለመገንባት እና ለሌሎች አስፈላጊ ወጭዎች 23 ሚሊየን 300 ሺሕ ብር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ሳምንት አስመልክተው የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው(ዶክተር)፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስተሯ ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፣ የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄደው “የኢትዮጵያ ሳምንት” ባለ ፀጋና፣ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት፣ ብዝሃ ባህል ያላት ድንቅ አገር ኢትዮጵያ ! በሚል ይከበራል ብለዋል።

አገራችን የታደለቻቸው ድንቅ የተፈጥሮ ፀጋዎቿ ለዕድገቷና ለልማቷ ውለታቸው ከፍ ያለ፣ ስም ያላትና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች አገር ትሆን ዘንድ ዛሬም የቤት ስራው በኢትዮጵያውያን ላይ የተጣለ ነው። ውብ ባሕሎቿን ማስተዋወቅ፣ እምቅ ታሪኳን ለዓለም ማሳየት፣ የኢንቨስትመንት አቅሟን መግለጥ ዛሬም ለነገ የማንለው ትልቁ የቤት ሥራችን ነው በማለት ተናግረዋል። የኢትዮጵያን ድንቅ ባሕሎች፣ የተፈጥሮ ፀጋዎች፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሁም የኢትየጵያውያንን አንድነት በማስተሳሰር በኩል ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል ተብሎ የታመነበትና ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ትልቅ አጋጣሚን የሚፈጥር ‹‹የኢትዮጵያ ሳምንት›› ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን ከግንቦት 10 ቀን እስከ ግንቦት 16 ቀን 2013 በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ ለማካሄድ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነው ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን አሥሩ ክልሎች እና ኹለቱ የከተማ አስተዳደሮች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የኢትዮጵያውያን ወዳጅነት ይበልጥ ደምቆ የሚታይበት፣እርስ በእርስ በመተዋወቅ ፍቅርና አንድነት ጎልቶ የሚታይበት፣ መላ ኢትዮጵያውያን አንዲት መሰባሰቢያ ስለሆነቻቸው አገራቸው የነገ ዕድገትና የመለወጥ ተስፋ ቆም ብለው የሚያስቡበትና ተስፋቸውንም የሚያጠናክሩበትን አጠቃላይና ዝርዝር ዓላማዎች እንዲያሳካ ይጠበቃል ተብሏል።

ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አንዱ ከአንዱ ከፍና ዝቅ ሳይል፣ ያላቸውን ባህላዊ እሴቶች፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች፣ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ያልተዳሰሱና አዲስ እየለሙና ሊለሙ የሚችሉ ሀብቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ ማስተዋወቅ የሚችሉበት ደረጃውን የጠበቀ የኤግዚቢሽን ማሳያ /Exhibition Stand/ ተዘጋጅቷል። ዝግጅቱ በአዲስ አበባ መሀል ከተማ በተገነባው የወዳጅነት ፓርክ የሚከናወን ሲሆን፣ ቦታው የተመረጠበት ምክንያት ይህ ፓርክ በውስጡ የያዛቸው በርካታ መናፈሻዎች ኢትዮጵያን በሚወክሉና ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊጠቀሙባቸው የሚችሉባቸው፣ የሚሰባሰቡባቸውና አገሪቱ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች የጋራ ቤታቸው መሆኗን የሚገልጹ፣ የሁሉም ብሔረሰቦች ስም የተጻፈበት አደባባይ ያለውና በቀጣይም አገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንዲስተናገዱበት ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ በመሆኑ ነው ብለዋል ።

ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ይህ ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን በሸገር አደባባይ ሰፊ በሆነው የውጭ ክፍል የሚዘጋጅና የኮቪድ የጥንቃቄ መመሪያዎችን በተከተለ መልኩ የሚከናወን ይሆናል ብለው። በዚህ መልኩም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚጎበኙት ይጠበቃል። ዝግጅቱን የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች፣ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይጎበኙታል ተብሎም ይጠበቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here