ተወልደው ያደጉት ደሴ ከተማ ነው፤ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ መሐመድ። ከልጅነታቸው ጀምሮ በንግድ ሥራ ውስጥ አሳልፈዋል። በ2004 የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ቢሆንም፣ በወቅቱ የነበረው መንግሥት በሚፈልገው መንገድ ባለመሄዳቸው ምክንያት አሸባሪ የሚል ስያሜ ሰጥቶ የ22 ዓመት የእስር ትዕዛዝ አውጥቶባቸው ነበር።
የስምንት ልጆች አባት የሆኑት ኡስታዝ አቡበከር ለአራት ዓመት ከስድስት ወር በእስር ቆይተዋል። ለአራት ወራት ሳይቤሪያ በሚባለው ጨለማ ቤት የታሰሩ ሲሆን፤ ከቂሊንጦ እስከ ማዕከላዊ እስር ቤቶች ገፈት ቀማሽ ሆነው ነበር። በአሁኑ ሰዓት የፌዴራል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቋቋሙት ዘጠኝ የኮሚቴ አባሎች ውስጥ ምክትል ሰብሳቢ ናቸው።
ኡስታዝ አቡበከር የእስልምና ሀይማኖታዊ ትምህርቶችን በማስተማር እና ወጣቶችን በማነቃቃት ይታወቃሉ። በግንቦት ወር መጀመሪያ ፍጻሜውን የሚያገኘው የረመዳን ወርን እንዲሁም መቋጫውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ፣ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት የአዲስ ማለዳዋ ሰላማዊት መንገሻ ከኡስታዝ አቡበከር ጋር ቆይታ አድርጋለች።
የረመዳን ፆም እንዴት ነበር? በእስልምና አስተምህሮ ውስጥ ዘካ እና ሰደቃ የሚባል የስጦታ ዓይነት አለ። በተለይ ለረመዳን ጾም በልዩ ስጦታ ኅብረተሰቡን ማገዝ ይታያል። አሁን ምነው ተቀዛቀዘ?
እንደሚታወቀው አሁን የመጨረሻዎቹ የጾም ቀናት ላይ ነው የምንገኘው። የዘንድሮ ረመዳን ለየት የሚያደርገው የራሱ ድባብ አለው። ባለፈው በዚህ የረመዳን የጾም ወቅት በተከሰተው የኮሮና ወረርሺኝ ብዙ መስጂዶች ተዘግተው፣ አምልኮተ ስርዓት ማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ነበር። አሁን ወረርሺኙ ቢኖርም ጥንቃቄዎች እየተደረጉ ሁሉም መስጂዶች አገልግሎት እየሰጡ ኅብረተሰቡ በጋራ እንዲያፈጥር መሆኑ ለየት አድርጎታል። ስለዚህ ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልካም የረመዳን ጾም ወቅት ነበር።
ሌላው ያነሳሽው ጉዳይ ስለዘካ እና ሰደቃ ነው። በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘካ እና ሰደቃ የሚባሉ የስጦታ መተግበሪያዎች አሉ። ሰደቃ ማለት በማንኛውም ጊዜ የሚሰጥ ስጦታ ሲሆን በረመዳን ጊዜ ደግሞ ከተለመደው በበለጠ አብሮነት የሚያሳይ፣ ለተቸገሩ ወገኖች የሚሰጥ ነው። ከእስልምና አስተምህሮ አንዱ ‹የገሀነም እሳትን፣ ለሌሎች በማካፈልም ቢሆን ተጠበቋት› ይላል። ይህ ደግሞ በጋራ መንፈስ ለሌሎች መኖርን ማሳያ ነው።
በዚህ ጊዜ የሚሰጠው ሰደቃ መስዋዕት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ነው። ዘካ ወይንም አስራት ደግሞ በእያንዳንዱ አቅም ባለው፣ የንግድ ሥራ ውስጥ በተሰማራ ወይም ቋሚ ገቢ ባለው ሰው ለሰባት ለተለያዩ ዘካ ለሚገባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሰጥ ነው።
ረዳት የሌላቸው፣ አቅማቸው የደከመ፣ የተቸገሩ ሰዎች፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መስጠት ይገባል። ምክንያቱም የነሱ ሀቅ ነው። ዋና ዓላማው በማኅበረሰብ ውስጥ ያለን ችግር መቅረፍ ነው። ሁልጊዜ ተመጽዋች እና ተረጂ እንዲሆኑ ሳይሆን ሰዎችን ማብቃት፣ ወደ ሥራ ማሰማራት ነው ዓላማው።
በዓለማችን በዓመት 400 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለዘካ ይወጣል። ይህ ዘካ በአግባቡ በትክክለኛ ተቋም ወርዶ ማኅበረሰብን ለመታደግ፣ የሥራ አጥነትን ለመቀነስ እና ለሚገባቸው ሰዎች ቢውል ብዙ ችግሮችን መሸፈን ይቻል ነበር። በተለይ እኛ አገር ላይ መስመሩን በትክክል ባለመጠቀማችን ብዙ ክፍተቶች አሉ።
ዘካው በተደራጀ መልኩ መሄድ አለበት። ዘካ ተቀባዩ ሰው ዘካ ሰጪ እንዲሆን እና ዘካ ተቀባይ በቀጣይ ጊዜ ገቢውን በማሳደግ ረጂ ይሆናል። ዘካ ከአምስቱ የእስልምና መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ነው። ዘካ መስጠት ግዴታ ነው ማለት ነው።
አሁን ላይ ያለው ጫና በጣም በዝቷል። በብዙ ቦታዎች ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ተቸግረው የወደቁ አሉ፣ ኮሮና ወረርሺኝ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ፈጥሯል። በዚህ ሁኔታ የእርዳታ ሰጪዎችንም ጎድቷል። የችግረኛውንም ቁጥር አብዝቷል። በዚህ የሰጪዎች ገቢ መዳከም ምክንያት ዘካው እንደበፊቱ አልሆነም።
ይህም ሆኖ ለበርካቶች ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ የተሠሩ ሥራዎች አሉ። በረመዳን የፆም ወቅት በተለይ እጥፍ ድርብ ሥራዎች ይሠራሉ። በቅርቡ በየክልሉ የተፈናቀሉ እና አዲስ አበባ ዙሪያ ላይ ከሶማሊያ የተፈናቀሉ አሉ። በአማራ ክልል ወሎ አካባቢ ሰፊ ቁጥር ያለው ተፈናቃዮች አሉ። ትግራይ ላይ በጦርነት ምክንያት ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው አሉ።
እነዚህ አካባቢዎችን ጨምሮ በጎዳና ላይ የሚገኙ የተቸገሩትን ለመርዳት የቤት ለቤት ሥራዎች በየቦታው በተለያዩ የሙስሊሙ የበጎ ሥራ በሚሠሩ ድርጅቶች ተሠርተዋል። ወሎ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ ክልል ላይ ያሉትን ተጎጂዎች ቴምር፣ ለማፍጠሪያ የሚያገለግሉ እህሎች እና ዘይቶችን ተደራሽ ለማድረግ ተሞክሯል። ችግሩ ከመብዛቱ አንጻር ግን ምን ያህል በቂ ነው የሚለው ራሱ ጥያቄ ነው።
ከእነዚህም አልፎ በየእስር ቤቱ ያሉትን ሁሉንም ለማዳረስ ሙከራ አድርገናል። ማፍጠሪያ የሆነ ምግብ እንዲያገኙ እና እንዲሠራላቸው ተደርጓል።
ለበዓሉ እለትስ የታሰበ ነገር አለ?
በዓል ሰው ብቻውን ሲደሰት፣ አዲስ ሲለብስ አይደለም በእስልምና አስተምህሮ ኢድ የሚባለው፣ ለሌሎች በመኖር እና ለሌሎች ደስታ በመፍጠር ነው።
በረመዳን ፆም ዘካ እንደሚደረገው የጾሙ ማብቂያ ላይ ደግሞ ጾመኞች በጾም ጊዜያቸው ውስጥ የተበላሸባቸው፣ የጠፋባቸው፣ በጾሙ ወቅት ማሟላት የሚገባቸውን ነገር ሳያሟሉ ሲቀሩ ለማሟላት የሚሰጥ አለ። ይህ ደግሞ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በቁጥራቸው፣ ቤት ውስጥ በሚኖረው ሰው ልክ ድርሻቸውን በእህል እና በገንዘብ ይሰጣል። የዚህ ዋና ዓላማ በበዓል ቀን ሙስሊም የሆነው ችግረኛው ወገን የሰው ፊት እንዳያይ ደጅ እንዳይጠና በማድረግ ተደስቶ በዓልን መዋል አለባቸው የሚል ነው።
ይህ ደግሞ ኢድ ከመሰገዱ በፊት ነው መሆን ያለበት። ከኢድ በኋላ ከወጣ ራሱ ያስጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪም የኢድ እርዶች አሉ። በተለያየ ዓይነት የሚሰጡ ስጦታዎች አሉ። ስለዚህ ለበዓል በየአካባቢው ለተፈናቀሉትም ተደራሽ ለመድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። ከዛ ውጭ በአቅራቢያችን የምናገኘውን ለመርዳት ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን።
አሁን ወደ ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ልውሰድዎት። አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የባንኮች የሸሪዓ ሕግ መውጣት አለበት እያሉ ነው። በዚህ ጉዳይ ምን ሐሳብ አለዎት?
ከወለድ ነጻ ባንክ የሚባለው አካታች እና አሳታፊ የሆነ የባንክ ስርዓት አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው። ሁሉም የኢኮኖሚ ስርዓት፣ የራሳቸው የሆነ የኢኮኖሚ ፍልስፍና አላቸው። ሸሪዓን መሠረት ያደረገ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ስርዓት፣ ለእምነት ተከታዩ ብቻ የመጣ አይደለም። በየትኛውም እምነት ላይ ወለድ የማይጠቀም፣ ለምሳሌ በመለኮታዊ መመሪያዎች እንደሚያመላክተው አራጣ መብላት ኃጥያት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስም የተከለከለ ነው።
ከፍተኛው ቁጥር አማኝ በሆነባት አገር አማኞች ይህንን የፋይናንስ ስርዓት መጠቀም ሳይችሉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ድርሻ እንዳይወጡ የሚያደርገውን አግላይ የሆነ ኢኮኖሚ ስርዓት መጠቀም የማይፈልግ በርካታ ሕዝብ አለ። የሸሪዓ ስርዓት እዚህ አገር የተጀመረ አይደለም። በመላው ዓለም ትልልቅ የሚባሉ እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና አውሮፓ አገራት ላይ ባንኮች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ቅርንጫፎች አሉ።
ስርዓቱ የሸሪዓ ሕግን መሠረት ያደረገ ነው እንጂ የእምነት ጉዳይ አይደለም። የግንዛቤ እጥረት ካልሆነ የዚህ የፋይናንስ ስርዓት አካታች በሆነ መልኩ አይካሄድ፣ ሕጉ ይውጣ/ይቅር ብሎ የሚያስብ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ እና ይህ መሪ ሐሳብ ያለው ካለ፣ ተሳስቷል።
በመጀመሪያ ደረጃ ስላላወቁት ነው። እምነትን ብቻ ያተኮረ አድርገው ስላሰቡት ነው። ባንኩ ለሙስሊሙ ተብሎ ለብቻ የተዘጋጀ ፓኬጅ እና ለክርስቲያን ተብሎ የተከፈለ ነገር የለውም። ይህንን የፋይናንስ ስርዓት ወለድን አልጠቀምም ለሚል ማንኛውም ኅብረተሰብ የየትኛውም እምነትም ሆነ ብሔር ተከታይ የሚያካትት ነው።
ይህ ሕግ አይካተት ማለት አገሪቷ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሆነውን ዜጋ ያገለለ ነው። ወለድ ያላቸው ባንኮች መጠቀም ሃይማኖቴ አይፈቅድም እያለ እነሱን በማግለል አገር እንዴት ነው የሚያድገው? አገር በእኩል ዜጎች በጋራ ተሳትፎ ኖሯቸው የጋራ ጥረት አድርገው እንዲለውጧት ነው የሚፈለገው። ይህ የሸሪዓ የፋይናንስ ስርዓት ተዘርግቶ ተወዳድሮ ሁሉም የመረጠውን እና መፍትሄ አድርጎ ሊጠቀምበት ይገባል።
ጉዳዩን ካለመረዳት፣ ምንድነው የያዘው ነገር የሚለውን ካለማወቅ ካልሆነ በስተቀር፣ ከግንዛቤ እጥረት እና ከእውቀት ማነስ የመነጨ ሐሳብ እንጂ ይህ በማንኛውም መልኩ ሊጠላ ወይም ደግሞ እንዳይኖር ሊደረግ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም። ምክንያቱም የሆነ ቡድንን የሚይዝ አይደለም፣ የሆነ አካል የሚለይ አይደለም። ለሁሉም የማኅበረሰብ አካል ክፍት የሆነ አንድ የፋይናንስ ፍልስፍናን የያዘ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንጂ ሌላ ዓላማ ያለው አይደለም። ሐሳቡ ግማሽ ዜጋ ወለድ የማይጠቀመውን ከኢኮኖሚ ተሳትፎ እና ድርሻ እጅ እንዳይኖረው የሚያደርግ ሥራ ነው።
የአንድ አገር ኢኮኖሚ እድገት ሊኖር የሚችለው ኢኮኖሚ የሚያድግው ሁሉም ዜጎች ባላቸው አቅም እና ድርሻ፤ በሁሉም ዘርፍ ላይ አገሪቱ ላይ በሚያደርጉት የኢኮኖሚ ተሳትፎ ነው። አገር ውስጥ ያሉ ወለድ ያላቸው ባንኮች አገሪቱ ላይ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣ በእነዚህ ባንኮች ብድር እና ድጋፍ የተሠሩ ናቸው።
አገር ላይ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶች የሚሠሩት ይህ የወለድ ስርዓት እኔን አያካትተኝም የሚለው አካል አገሪቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ተሳትፎ፣ አቅሙን አሳድጎ ሠርቶ፣ ራሱን ጠቅሞ ለአገር የሚጠቅሙ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለማድረግ ምን ያስፈልገዋል? ይህንን እድል የሚሰጠው የፋይናንስ ስርዓት ያስፈልገዋል።
የፌዴራል እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት በኹለት ተከፍሏል ይባላል። እውነት ነው? በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ?
የፌዴራል እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት ያዋቀራቸው 24 አባላት፣ መጅሊስ አቋቁመው የተሰጣቸውን ሥራ በሚያፈጽሙበት ጊዜ የተፈጠረ አለመግባባት እንጂ ሌላ የተፈጠረ አንጃ የለም።
የፌዴራል እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት የቋቋመው በ26 ዑለማዎች እና በሰባት የቦርድ ኮሚቴ፣ 33 አባላት ይዞ ነው። በሥራው ውስጥ የተፈጠሩ አለመግባባቶች እና ክፍተቶች ከ33ቱ አባላት 24 የጉባኤ አባል ተሰብስበው በኹለት አቅጣጫ የተሄደ ሂደት አለ።
ሁሉም የአንድ መጅሊስ አካል ናቸው፤ ሁሉም እያወሩ ያሉት ስለ አንድ መጅሊስ ነው። ባለፉት ጊዜያትም 24ቱ የጉባኤው አባላት ጠቅላላ ጉባኤ በኹለት ዓመት ውስጥ ተደርጎ ስለማያውቅ ያሉ ክፍተቶች መስተካከል አለባቸው የሚል አቋም በመያዝ እሰጣገባ ውስጥ ተገብቶ ነበር።
በውስጥ አሠራር ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት ማለትም አንዱ ለማገድ እና አንዱ ለማቆም የተሄደበት ሁኔታ ነው ያለው እንጂ መከፋፈል የለም። ከዛ ውጭ ሁሉም በአንድ መድረክ ላይ ሚያዚያ 23 ሸራተን አዲስ ላይ በነበረ ዘጠኝ አባላት ላለው ኮሚቴ ኃላፊነት ሰጥቶ ሁላቸውንም በአንድ ላይ አፅድቀን ለ26 ዑለማዎች ኃላፊነት ተሰጥቷል። በኋላ ለስድስት ወር ሦስት መሠረታዊ የሆኑ ሰነዶችን አስረክበን እነሱን እንዲያጠናቅቁ እና ከዛ ወደ ማኅበረሰብ ወርዶ ማኅበረሰቡን የሚወክሉ ሰዎች የሚመጡበትን መስመር እንዲያዘጋጁ አድርገን ኃላፊነት ሰጥተናል።
ይህ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሙፈሪያት ካሚል በነበሩበት ወቅት መስመር ላይ ቆመን ተነጋግረን የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰን ይፋ አድርገነዋል። ጊዜያዊ የሆነ ይህንን የሚያደራጅ መጅሊስ ነው የተቋቋመው። ከዚህ በኋላ ዑለማዎቹ እንዴት ይቀጥላሉ የሚለው የጉባኤው ውሳኔ እና በቀጣይ የሚኖረው ከሕዝብ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ውሳኔዎች የሚመጡ ናቸው።
ያን በማስፈፀም ሂደት ውስጥ የተከሰተ ክፍተት እንጂ ሌላ አንጃ ይዞ የመጣ አዲስ መጅሊስ ልፍጠር የሚል የለም። ያ የተሳሳተ መረጃ ነው፤ ትክክልም አይደለም።
የአላህ ፍቃድ ከሆነ በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። አገር ዐቀፍ የሆነ የጋራ መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉ አንድ አቅጣጫ እና መስመር በመዘርጋት ሁሉን ባማከለ መልኩ እንቅስቃሴ ላይ ነው። በቅርቡ ደግሞ ውጤታማ መፍትሄ ይዘን ለኅብረተሰቡ ይፋ እናደርጋለን።
በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታይ እንኳን ለኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ። ኢድ ማለት የመረዳዳት፣ የመተጋገዝ፣ የአብሮነት አቅማችንን በማሳየት ወንድሞቻችንን በመርዳት የተቸገሩትን በመጎብኘት እንደ አገር ደግሞ ለአገር ሰላም እየጸለይን ኃላፊነታችንን የምንወጣበት ነው።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



