በ‹ዞይትስ› የሶስት ዓመት ፕሮጀክት መሰረት በዶሮ እርባታ ላይ ከተሰማራው ‹ኢትዮ ቺክን› ጋር በመተባበር ያዋቀረውን የዶሮ መመርመሪያ እና ክትባት መስጫ ላብራቶሪ ከፍቷል። በግብርና ሚኒስቴር ዋና የእንስሳት ሐኪም የሆኑት አለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) እንደገለጹት ኢትዮ ቺክን ለረጅም ጊዜ በዶሮ ሀብት ልማት ሲሳተፍ የቆየ ሲሆን፣ እስከ አሁን ድረስ ጫጩቶችን በማስፈልፈል ለዶሮ አርቢዎች የማከፋፈል ስራ ሲሰራ ቆይቷል። አሁን ግን አድማሱን በማስፋት የጤና መመርመሪያ ተቋም ለመገንባት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ረጅም ጊዜ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ባለው የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት እና በምን መልኩ መስራት እንዳለበት ዝርዝር ከታየ በኋላ ድርጅቱ ላብራቶሪውን እንዲገነባ ፍቃድ አግኝቷል ብለዋል።
ከ100 በላይ የዶሮ በሽታዎች ያሉ ሲሆን፣ የእነዚህን በሽታዎች ምርመራ ለማካሄድ በመንግስት ደረጃ ያለው የላብራቶሪ ኬሚካል እና ሪኤጀንት በቂ አይደለም ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለበትን ይህን የኬሚካል ውስንነት ይህ ድርጅት ይቀርፋል ተብሏል።
በተጨማሪም አሁን በመንግሰት ደረጃ ያሉት ላቦራቶሪዎች ብቻቸውን ወደፊት የሚከሰቱ የዶሮ በሽታዎችን መለየት አይችሉም የተባለ ሲሆን ስለዚህ የግሉን ዘርፍ በማበረታታት ይህን ችግር የሚቀርፍና ለዶሮ ህክምና እና ክትባት የሚሰጥ ተቋም መኖሩ ለሪኤጀንቶቹ የምናወጣውን የውጪ ምንዛሬ በእጅጉ የሚቀንስ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
ከዚህ በፊት ኢትዮ ቺክን የዶሮዎችን ምርመራ ያደርግ የነበረው ሳምፕል ወደ ደቡብ አፍሪካ እና አውሮፓ በመላክ ነበር። ይህ አዲሱ ላቦራቶሪ ወደ ውጭ ለመላክ የሚወጣውን የውጪ ምንዛሬ ይቀንሳል ሲሉ የኢትዮ ቺክን የሴልስ እና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ፍሰሃ ተስፉ ጨምረው ተናግረዋል።
‹ሻየሾኔ ትሬዲንግ› ኃ.የተ.የግል ማህበር በግብርና ዘርፍ ማማከር አገልግሎት ተሰማርቶ ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የሚሰራ ሲሆን፣ ዞይትስ የተባለ በእንሰሳት መድኃኒት አቅርቦት እና የሕክምና አገልግሎት ላይ የተሰማራ አለም አቀፍ ድርጅት ጋር በጋራ ይሰራል።
ዞይትስ ከዚህ ቀደም በፋይዘር መድሃኒት አምራች ድርጅት ስር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ የእንሰሳት መድኃኒት አቅራቢ መሆን ችሏል። ድርጅቱ በአለም ላይ በ45 አገራት መድኃኒቶችን የሚያመርት ሲሆን፣ በ100 አገራት ላይ ደግሞ ምርቶቹን ያከፋፍላል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2017 ዞይትስ ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት ዘላቂ የሆነ የእንሰሳት ምርታማነት ለማግኘት ሲባል ከ‹ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን› በተገኘ የሶሥት ዓመት ድጋፍ አልፋ የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርጾ በዩጋንዳ እና ናይጄሪያ ሥራ አስጀምራል።
በ2018 ደግሞ በኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ ፕሮጀክቱን ያስጀመረ ሲሆን ዋና ዓላማው የእንስሳት ጤና ለመጠበቅ የመድኃኒት እና የህክምና አቅርቦት በማስፋፋት እንዲሁም የተለያዩ ላብራቶሪዎች እና የምርምር ተቋማት ግንባታ እና ማስፋፊያ ማድረግን ጭምር ነው።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበሽታ መመርመሪያዎችን ሪፖርት የሚደረግበት እና የላብራቶሪ አዲስ የበሽታ ግኝቶች ትክከለኛነታቸውን በማረጋገጥ ስራውን በትክክል መስራቱን ክትትል ያደርጋል ሲሉ አለማየሁ ገልጸዋል። አክለውም የህክምና መስጫ ተቋማት እስከ አሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት እጅ የሚገኙ ሲሆን፣ አሁን መንግስት እያደረገ ያለው ወደ ግል የማዞር ተግባር ነው ብለዋል።
ይህ ፕሮጀክት የዶሮ ሀብት ልማት ላይ የተሰማሩትን የሚያግዝ ፕሮጀክት ሲሆን፣ የአገራችንን የዶሮ ፍላጎት በማሟላት፣ የስራ እድሎችን በመፍጠር፣ የዶሮ እርባታ ላይ ሰዎች እንዲሰማሩ በማድረግ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ዶሮ አርቢዎችን የሚያበረታታ ነው ሲሉ አለማየሁ ገልጸዋል። ዞይትስ ከሚሰራቸው ስራዎች አንደኛው የምርመራ ላብራቶሪዎች ነው። የዶሮ በሽታዎችን መመርመር የሚያስችለው ይህ ላብራቶሪ የክትባት አገልግሎቶችንም ይሰጣል። በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮ ቺክን ብቻ የምርመራ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን፣ በቀጣይ ወደ ክልሎች ለመሄድ አቅዷል ሲሉ የዞይቲስ ዲያግኖስቲክ ማናጀር ብጹዕ ክፍሉ ገልጸዋል።
ኢትዮ ቺክን 10ሺ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፣ ላብራቶሪው በቀን እስከ 500 ናሙና (ሳምፕል) ድረስ መስራት ይችላል ሲሉ ብጹዕ ተናግረዋል።
ኢትዮ ቺክን በፈረንጆቹ 2010 የተመሰረተ ሲሆን፣ አሁን ላይ ወደ 14 የዶሮ ማቀነባሪያ ኢንዱስትሪዎች እና 1600 ሰራኞች አሉት። ከ10 ሺ በላይ ደንበኞቻቸው ስራ አጥ የነበሩ ወጣቶች፣ መካከለኛ አርብቶ አደሮችን እና ፍላጎት ያላቸው የዶሮ አርቢዎች ናቸው።
ኢትዮ ቺክን በዋናነት ሁለት አይነት ጫጩቶችን ማለትም ለእንቁላል ብቻ የሚጠቅሙ እና ለስጋና ለእንቁላል የሚውሉ ዶሮዎችን ያከፋፍላል።
ኢትዮ ቺክን በ2020 ወደ 25 ሚሊየን ዶሮዎችን ማሰራጨት ችሏል።
ኢትዮቺክን በቀጣይ እስከ 29 ሚሊዮን ዶሮዎችን ለማሰራጨት ያቀደ ሲሆን፣ ወደ ጋና እና ሶማሊያ ለመላክም እቅድ ይዟል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



