ብሩክ ታዮ(ዶ/ር) የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ
የኮሚኒኬሽን ባለስልጣን ኹለት የግል ቴሌኮም ኦፕሬተሮችን ፈቃድ ለመስጠት ባወጣው ጨረታ፣ ኹለት ተጫራቾች ብቻ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። ባለሥልጣኑ በሚቀጥሉት ኹለት ሳምንታት ውስጥ አሸናፊውን ለማሳወቅ እየተጠበቀ ቢሆንም መንግሥት ይህንን ውሳኔውን ሊለውጥ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት ብሩክ ታየ (ዶ/ር) ‹‹ጨረታው ሊሰረዝ ይችላል፤ አንዱን ተሳታፊ ልንመርጥ ብቻ እንችላለን ወይንም ደግሞ ለኹለቱም ተቋማት የአሸናፊነት ፈቃድ ልንሰጥ እንችላለን።›› በማለት ከኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2013 ባለሥልጣኑ በመላው አገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት ማቅረብ ለሚችሉ ሁለት ተጨማሪ ኩባንያዎች ፈቃድ ለመስጠት ያወጣው ጨረታ ኩባንያዎቹ በተገኙበት የጨረታ ሰነዱ ተከፍቷል።
በዚህም መሠረት ለጨረታ የቀረበውን ኹለት የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለማግኘት የጨረታ ሰነዶቻቸውን ያስገቡት ኩባንያዎች የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን እና ዓለም አቀፍ ጥምረት ለኢትዮጵያ በሚል መጠሪያ የተመሠረተው የቴሌኮም አገልግሎት ጥምረት ነው። የጥምረቱ አባላት የኬንያው ሳፋሪኮም፣ የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮምና ቮዳፎን ከብሪታኒያ ሲሆኑ፣ ጥምረቱን በፋይናንስ ዘርፍ የተቀላቀሉት ደግሞ ሲዲሲ የተባለ የእንግሊዝ የፋይናስ ተቋም፣ ዲኤፍሲ የተባለ የአሜሪካ የኢንቨስትመንት ተቋምና ሱሚቶ የተባለ የጃፓን ኩባንያ ይገኙበታል።
መንግሥት በ2012 አውጥቶት በነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ ማመልከቻ ላይ ከ12 በላይ ኩባንያዎች ፍላጎት አሳይተው እንደነበር ይታወሳል። ብሩክ(ዶ/ር) ሲገልጹ 12 ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተን የቴሌኮም ቢዝነስ ላይ መሳተፍ እንፈልጋለን ያሉ ሲሆን፣ ጨረታው ላይ ከተቀመጡ ቴክኒካል መስፈርች መካከል አንዱ ጨረታውን ያስገባ የቴሌኮም ተቋም 30 ሚሊዮን ሰብስክራይበር ያለው መሆን አለበት የሚል ነው ብለዋል።
ይህ መስፈርት የተቀመጠበት ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ተወዳዳሪ ለመሆን ኹለት ሚሊየን እና ሦስት ሚሊየን ሰብስክራይበር ይዞ 30 ሚሊየን ለማድረስ ስለሚከብድ በሰብስክራይበር ቁጥር ማነስ ምክንያት ጨረታው ላይ ያልተሳተፉ ድርጅቶች አሉ ብለዋል። ሌሎቹ ደግሞ አፍሪካ ውስጥ በቴሌኮም ዘርፍ ምንም አይነት ልምድ የሌላቸው በመሆናቸው እና በቴሌኮም ዘርፍ ወደ ግል ይዞታ ያላዞረች የመጨረሻዋ አገር ኢትዮጵያ ናት በማለት ብቻ የመጡ ድርጅቶች በመሆናቸው ውድቅ ተደርገዋል በማለት ገልጸዋል።
ይህንን እና ሌሎች መስፈርቶችን አልፈው ከ12ቱ ድርጅቶች ውስጥ መሳተፍ እንደሚችሉ የተረጋገጠው አራት ድርጅቶች ብቻ ናቸው ሲሉ አማካሪው ገልጸዋል። ከአራቱ ውስጥ ኹለቱ በጨረታው መክፈቻ ወቅት መጥተዋል፤ አንደኛው MTN ሲሆን በአፍሪካ ትልቁ የቴሌኮም ድርጂት ነው። ሳፋሪ ኮም፣ ቮዳፎን እና ቮዳኮምን ብንወሰድ በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊየን በላይ ሰብስክራይበር ያላቸው እና በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያ እንዲሁም በእንግሊዝ እጂግ ዘመናዊ የሚባል የቴሌኮም አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
ብዛት ሳይሆን ጥራት ነው መታየት ያለበት ያሉት አማካሪው፣ እነዚህ ድርጀቶች የመስራት ብቃታቸው ታይቶ ነው የቴክኒክ ሂደቱን ለማለፍ የቻሉት። ከዚህ በኋላ ፋይናንሳቸው ታይቶ ውሳኔውን የመስጠት መብቱ የመንግሥት ነው ሲሊ ገልጸዋል።
መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን ለውድድር ክፍት እንዲሆን በወሰነው መሠረት በመካሄድ ላይ የሚገኘው በዚህ ጨረታ፣ አሸናፊ ሆነው የሚገቡ ኩባንያዎች ከ126 ዓመት በላይ በኢትዮ ቴሌኮም በብቸኝነት ተይዞ የነበረው የቴሌኮም ገበያን የሚጋሩ ይሆናል። ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፏን ወደ ግል ካላዞሩ የዓለማችን አገሮች መካከል መሆኗም ይታወቃል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



