በ2013 የአስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና ወስደዉ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ነጥብ ያመጡና በተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተመደቡ ተማሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል። ላነሱት ቅሬታም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለቅሬታቸው እየተቀበለ መሆኑን የተቋሙ የሕዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተሯ አመለወርቅ ህዝቅኤል ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። አክለውም በአገሪቱ በሚገኙ 52 ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ ከ147ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎች መመደባቸዉንም አስታዉቀዋል። ከምደባዉ ጋርም ተያይዞ ተማሪዎች የሚኖራቸዉን ቅሬታ በስልክ፣ ኢ-ሜልና ድረ-ገፆችን በመጠቀም እንዲያቀርቡ መደረጉንም ዳይሬክተሯ አስታዉቀዋል።
መረጃዉ ለሁሉም ተማሪ እንዲዳረስ በተለያዩ ዋና ዋና መገናኛ ብዙኀን እንዲነገር መደረጉና መረጃዉ ሊደረስባቸዉ በማይችልባቸዉ ገጠራማ ክፍሎች የሚገኙ ተማሪዎች በየትምህርት ቤታቸዉ እየሄዱ መረጃዉን ማግኘት እንደሚችሉ አመለወርቅ አስታዉቀዋል።
በኮቪድ19 ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው የ2013 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዘግይቶ መሰጠቱን በማስታወስ፣ ይህንንም ተከትሎ ከሚያዝያ 25/2013 ጀምሮ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርስቲ ምደባን ይፋ አድርጓል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የተለያዩ ቅሬታዎች እንዳሉባቸዉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በር ላይ አግኝታ ያነጋገረቻቸዉ ተማሪዎች እንደገለጹት በየተመደቡባቸዉ ዩኒቨርሲቲዎች ለመሄድ የተለያዩ የጤናና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ችግሮች እንዳሉባቸዉ በመናገር ቅያሬም ፈልገዉ እዚያ እንደተገኙ ገልፀዋል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት የጸጥታ ችግር በሚገኝባቸዉ አካባቢ የተመደቡ ተማሪዎች ወደ አካባቢዎቹ ለመሄድ የደህንንት ስጋት እንዳለባቸዉና ከርቀትም አንጻር አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው አንስተዋል። በተለይም በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ የተመደቡ ተማሪዎች የደህንነቱ ሁኔታ ሲለሚያሰጋ መሄድ እንደፈሩ ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።
በየትኛዉም የአገሪቷ አካባቢ ወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ለመሄድ የደህንነት ስጋቶች፣ የኢኮኖሚና የጤና ችግሮች ቢኖሩብንም፣ ከሁሉም የሚያሠጋን ግን የሰላም ሁኔታ ነዉ ሲሉ የምስካዬሕዙናን እና የከፍተኛ 23 ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ ቅሬታ ለማቅረብ በአካል መገኘት እንደማይቻል መስማታቸውን አስታዉቀው ፤ነገር ግን ስልክ ስንደዉል አይሰራም(አይነሳም)፤ በኢሜልም ስንሞክር አስቸገሮናል፤ ሁላችንም ያሉብንን ችግሮች እንዴት ማቅረብ እንዳለብን ለማወቅ ተቸግረናል ሲሉ ሃሳባቸዉን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።
የተማሪዎቹን ቅሬታ የሚቀበሉት ኃላፊ በበኩላቸው እስከ ሚያዚያ 28 ድረስ ወደ 15000 የሚደርሱ ቅሬታዎች እንደሚኖሩ ገልጸዉ፣ የስልክ መስመሮቹ በብዛት ስለሚጨናነቁ ካልሆነ በስተቀር አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ተማሪዎቹ ጥሩ የኢንተርኔት አገልግሎት ባለበት ቦታ በመሆን የኢሜልና የተቋሙን ድረ ገጽ በመጠቀም ያላቸዉን ቅሬታ ማስታወቅ እና መሞከር እንደሚችሉ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችና የመምህራን ጉዳይ ኃላፊ ኢዶሳ ተርፋሳ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታዉቀዋል።
ከተማሪዎች የደረሱንን ቅሬታዎች እስከ ሚያዚያ 28 /2013 ባለዉ ተቀብልን ከዛ በኋላ የተዋቀረዉ ኮሚቴ የተማሪዎችን ቅሬታ በማየትና በመገምገም ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል ሲሉ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል ። ነገር ግን በአካል በመገኘት ቅሬታ ማቅረብ መጀመሪያ እንደማይቻል የገለጽን ቢሆንም ቀኑን በማራዘም ተማሪዎች በአካልም በመገኘት እስከ ሚያዝያ 29 ድረስ ቅሬታቸውን እያቀረቡና ተቋሙም ቅሬታቸውን እየተቀበለ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
አገሪቷ አሁን ላይ ካለችበት የደህንነት ሲጋት አንጻር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ ተቀናጅቶ እንደሚሰራና ዩኒቨርስቲዎችም አዳዲስ ተማሪዎቻቸዉን ሲቀበሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆናቸዉን አውስተዋል። ለምሳሌ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው እንደ ወላይታ ሶዶ፣ አሶሳ ፣ብሌ ሆራ፣ ሰመራና ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች እየተሰራ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከተቋሙ ባገኘችዉ መረጃ ለማወቅ ችላለች።
ብዙ ተማሪዎች የጸጥታ ስጋት አለብን ካሏቸዉ አካባቢዎች ዉስጥ አንዱ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ በጦርነቱ ወቅት ወድሞ የነበረዉ የእንሰሳት ህክምና ኮሌጅም ተመልሶ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ መሆኑን፣ የትራንስፖርት እጥረት እንዳያጋጥም ሰርቢሶችን በማዘጋጀትና፣ የአካባቢዉም ማኀረሰብ ተማሪዎቻችንን እንደበፊቱ የብቸኝነት ስሜት ሳይሠማቸዉ እንዲቀበላቸዉ ለማድረግ፣ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር ዩኒቨርሲቲዉ በመስራት ላይ መሆኑንም ከዩኒቨርሲቲዉ ባገኘነዉ መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች መካከል በአንጻራዊነት መቐለ ዩንቨርሲቲ በከተማ ዉስጥ እንደመገኘቱ የተሻለ የጸጥታ ሁኔታ ያለው መሆኑን በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የአልሙናይ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ኤፍሬም ሰይፋ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አስታዉቀዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



