የምርጫ ስነምግባር አዋጁ ይከበር!

0
720

የኢትዮጲያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 33 ላይ የተቀመጠው በምርጫ ስለሚወዳደሩ የመንግስት ሠራተኞች የተቀመጠው ገደብ ተፈፃሚ እንዲሆን አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች። የአዋጁ አንቀፆች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ሁሉም አካል እየወተወተ በሚገኝበት በዚህ አጣዳፊ ሰዐት ፍትሃዊነትን ለማምጣት ተብሎ ለራሱ አንድ አንቀፅ ተሰጥቶት የተቀመጠ ድንጋጌ ሊዘነጋ አይገባም። አዋጁ የመንግስት ሰራተኞችን በተመለከተ ተወዳዳሪ ዕጩ ሆነው መቅረብ ከፈለጉ በምርጫ ቅስቀሳ ወቀት እና ምርጫው በሚከናወነወበት ጊዜ ያለደመወዝ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ይደረጋል ይላል። እነዚህ የመንግስት ሰራተኞች ለየትኛውም ምክር ቤት ምርጫ እንቅስቃሴ በሚሳተፉበት ጊዜ በማንኛውም የቀጣሪው መንግስት መስሪያ ቤት ንብረት መገልገል እንደማይችሉም በንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ ተቀምጧል። ዳኞች፣ አቃቤ ህጎች፣ ወታደሮችና ፖሊሶች፣ እንዲሁም የፀጥታ ሀይሎችና የደህንነት ሰዎችን ጨምሮ የቦርዱ ሰራተኞች ስራቸውን ካለቀቁ መሳተፍም ሆነ በመደገፍ ተሳታፊ መሆን እንደማችሉ ተደንግጓል።

ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚ አለመሆኑን ማስረዳት ከባድ አይሆንም። ከከፍተኛ ሚኒስትሮች ጀምሮ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ስራቸው ላይ ሆነው ቅሰቀሳ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ደሞዛቸው ታግዶ ፈቃድ ወጥተው በነፃ ነው እንዳይባል፣ ስራ እየሰሩ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሲመርቁ አንዳንዴም ሲጎበኙ ይታያል። በማን ገንዘብ የተገዛ እንደሆነ የማይታወቅም ልገሳ በፓርቲ ስም ሰጥተው በስራ ሰአታቸው ሲቀሰቅሱ ማየት እየተለመደ ነው። አዋጁ የወጣው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ተወካዮቻቸው ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን ታስቦ ቢሆንም፣ አሁን ድረስ ተፈጻሚ ሲሆን አይታይም። አንድ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩ፣ ለምን ከመንግስት ስራቸው በፈቃዳቸው ራሳቸውን እንዳላገለሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “እኔ ብቻዬን ለምን” የሚል አይነት መልስ ሰጥተዋል። “በመመሪያ ለሁሉም ተፈፃሚ እንዲሆን ከተደረገ እኔ ስራዬ ላይ የምቆይበት ምክንያት አይኖርም” ብለዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ፣ አዋጁ በወጣበት ሰሞን በተለይ ከዩኒቨርስቲ ምሁራን ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ከምርጫው ራሳችንን እንድናገል ከስራ ገበታችንም ዞር አንድንል ያደርጋል የሚል ሀሳብ ሰንዝረው እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ቢሆንም፣ አዋጁ ፀድቆ አሁን ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ጊዜዎች ቀርተውታል። ነገር ግን፣ ቅስቀሳው ተፋፍሞም ቢሆን ከየትኛውም ፓርቲ በኩል ቅስቀሳ እያደረግከኩ ስለሆነ ፈቃድ ስጡኝ ብሎ ስራውን ያቆመ ስለመኖሩ አልተሰማም። የመንግስት ዕጩ ሆነው በተለያየ እርከን ላይ ሆነው የመንግስት ተቀጣሪ ሆነው እያገለገሉ ያሉትም ሆኑ የግልና የሌላ ፓርቲ ተወዳደሪዎች ወይ ቅስቀሳቸውን አሊያም ስራቸውን መምረጥ እንደሚኖርባቸው ግልፅ ነው። ይህን በተመለከተ በተለይ ከከተማ ወጣ ሲባል ለበአል እየተባለ ከምርጫ ምልክት ጋር አብሮ የሚያድሉበት የቅስቀሳ ዘዴ መነጋገሪያ ሆኗል። ይህን በተመለከተ ከምርጫው መድረስ አኳያ እንዲህ አይነት የብልጣብልጥ አካሄዶች እንደማያዋጡ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

ምርጫው የሚካሄደው እኩል የሆነ ዕድል ለሁሉም ተሰጥቶ ህብረተሰቡ በነፃነት እንዲመርጥ እንደመሆኑ፣ አንዱ የበለጠ የህዝብ ሃብትን ወይም ስልጣኑን ተጠቅሞ ተፅእኖ ለመፍጠር መንቀሳቀስ የለበትም። በተለምዶ የምርጫ ቅስቀሳ በየመንገዱ ሲካሄድ እናስተውላለን። ተቃዋሚዎች የሕዝብ ሀብትን ጥቅም ላይ እንደማያውሉ የሚታመን ቢሆንም፣ ሥልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ግን ተደጋጋሚ ስሞታ ሲቀርብበት ይሰማል። በተለይ በገጠር ወረዳዎች የመንግሥት መኪናን መጠቀም የተለመደ ይመስላል። አንቡላንስ ላይ ሳይቀር ፖስተር ለጥፈው ሲንቀሳቀሱ የታዩም ነበሩ። ይህ ለምን ሆነ ብሎ አጣርቶ እርምጃ መውሰድ የቦርዱ ኃላፊነት ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲም ሆነ የመንግሥት አካላት ቀስቃሾችን ስለቅስቀሳ መንገድ ማስተማር እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሥልጣን ላይ ያለው ብልጽግና ፓርቲ የራሱ የሆነ ሀብት እንዳለው ይታወቃል። የፓርቲው ሀብት አሁን ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀው ሕወሓት የተወረሰም ነው እንደመባሉ፣ በሽብር የተገኘ ሀብት ተብሎ በመንግሥት ስለመወረስ አለመወረሱ የሕግ ባለሞያዎች ምላሽ ቢሰጡበት የተሻለ ይሆናል። ይህ እስከሚጣራ ድረስ ግን የመንግሥት ሀብትና የፓርቲው ሀብት ተለይቶ ለቅስቀሳ መዋል የሚችሉና የማይችሉ ነገሮች መለየት አለባቸው።

ሥልጣን ላይ ሆነው መሥራት የሚችሉትን ተግባር ከተከለከለው ለይተው መዘርዘር አለባቸው። ተወዳዳሪዎቹ ባለሥልጣናት በሙሉ ፈቃድ ቢወጡ የመንግሥትን ሥራ የሚሰራ ጠፍቶ አገሪቱ ፈቃድ ላይ የወጣች እንደሚመስል ግልጽ ነው። የአብዛኛው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሹመኞች ተወዳዳሪ እጩ መሆናቸው ስለሚታወቅ ይህ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችልበት አጋጣሚ ትንሽ መሆኑን የሚናገሩ አሉ።

ነገር ግን፣ ከሥራ ገበታው መነሳት ባይችሉም ሥልጣናቸውንና ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው በግልጽ ቅስቀሳ ከማድረግ ቢቆጠቡ መልካም ነው። በተለይም የተሾሙበትን ሥልጣን ወክለው በሚገኙበት አደባባይ መንግሥትን ወክለው እንጂ ፓርቲያቸውን ወክለው ስለማይሠሩ ከቅስቀሳ እንዲቆጠቡ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

ሕጉ ያለጥቅም አልተቀመጠምና በተቻለ መጠን ጊዜው ሳይረፍድ ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞከር መልካም ነው። ይህ ጉዳይ ስር እየሰደደ ከሄደ ሥልጣን ላይ ያለ አካል በምርጫ ቢሸነፍ የመንግሥት ሥልጣኑን ተጠቅሞ እስካሁን የሚደረጉ ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን ላለማድረጉ ማረጋገጫ የለም። የፀጥታ አካላትና ሌሎችም እጩ መሆን የተከለከሉት አንዱን እንዲመርጡ ተብሎ ስለሆነ ምርጫውን ተዓማኒና ፍትሐዊ ለማድረግ ከአሁኑ መሥራት አለባቸው።

ምርጫ ቦርድም የመንግሥት ሀብት ለምርጫ መቀስቀሻ ሲውል እያየ ዝም ማለት የለበትም። ይህ የክልከላ አንቀፅ የሚጨምረው ገንዘብና ግዙፍ ቁሳቁሶችን ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ንብረት የሆነ ስልክ እንጨት ላይ ማስታወቂያ መለጠፍን ጭምር በመሆኑ ትንንሾቹንም ከመከልከል መጀመር አለበት። “አውራ ዶሮ በሰው ስጥ ሚስቱን ይጋብዛል” እንደሚባለው፣ በሕዝብ ሀብት ሕዝብን መቀስቀስ ተገቢ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች። ይህን በተመለከተ እስከዛሬ ይደረጉ የነበሩ አድሎአዊ አሠራሮች አሁንም መደገም ስለሌለባቸው ሁሉም ምርጫው ፍትሐዊ እንዲሆን የበኩሉን ማድረግ ይጠበቅበታል።

የመንግሥት ሀብትን ማንም አይጠቀም ማለት ባይቻልም፣ መጠቀም ካለባቸው ሁሉም እኩል ዕድሉን ማግኘት አለባቸው። ከመንግሥት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚለቀቀው የምርጫ መቀስቀሻ ገንዘብ በመዘግየቱ አቅም ላላቸው የበለጠ እድል ስለሚሰጥ፣ መሰጠቱ ካልቀረ በጊዜ እንዲሆን አዲስ ማለዳ ማሳሰብ እንዲሁም ማስገዘንብ ትወዳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here