ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሟቾች ቁጥር መበራከት የሬሳ ሳጥን፣ የቀብር አስፈጻሚ ትራንስፖርት አገልግሎት እና የቀብር ቦታዎች ዋጋ በመወደዱ መቸገራቸውን አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የዕድር ኃላፊዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ብዙ የአካባቢዎቻችንን ሰዎች እያጣን ነው፡፡ በዚህ ቫይረስም ሆነ በሌሎች በሽታዎች ወይም አደጋ የሚሞተውን ሰው ቀብር ለማስፈፀም የሚያስፈልገው ወጪ ደግሞ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል አቅም እየተፈታተነ ነው ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የተለያዩ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች እና የሬሳ ሳጥን ሻጮች በበኩላቸዉ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸዉን ገልጸዋል፡፡
በከተማችን ከሚገኙ ቀብር አስፈጻሚ ድርጅት አንዱ የሆነዉ አቤኔዘር ቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የመኪና ሰርቪስ ማድረጊያዉና የነዳጅ ዋጋ ቢጨምርም በአገልግሎቱ ላይ የተጨመር ዋጋ የለም ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን አሁን ላይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከሚሞተዉ ሰዉ ጋር ተያይዞ የቀብር ሰአት መደራረብ በአገልግሎታቸዉ ላይ ችግር እየፈጠረባቸዉ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ስራ አስኪያጁ ለቀብር ስርዓት ከ2000 -5000 ብር ድረስ፣ የዲኮርና አበባ ዋጋን ጨምሮ፣ በየደረጃዉ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ተናግረዋል፡፡ አክለውም የሬሳ ሳጥን ዋጋ የጨመረው ሕብረተሰቡ እንደሚለዉ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ ሳይሆን የሚስማር ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩና ይህም ከእንጨትና ከሰራተኛ ዋጋ ጪማሪ ጋር ተደምሮ ወጪውን በማናሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹ኤም .ዲ .ኤፍ› የሬሳ ሳጥኖች ደግሞ ከዉጪ ሲገቡ ከቀረጥና ከዶላር መጨመር ጋር ተያይዞ ዋጋቸው እንደተወደደ ዳዊት ሞገስ አስታዉቀዋል፡፡
በድርጅታቸዉም ከ1200- 10000 ብር ድረስ የሚያወጡ የሬሳ ሳጥኖች መኖራቸዉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንን ለመግዛት በጣም አቅም ላጠራቸዉ ዜጎች አልፎ አልፎም ቢሆን በነፃ በመስጠትም ጭምር እንደሚተባበሩ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ልዩነት አለ። ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ሬሳ ተሸካሚዎቻችን በአንድ ቀብር ለአንድ ሰዉ 150 ብር እንከፍላቸዉ የነበረ ሲሆን፣ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተና ሰዉ መሞት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግን ለተሸካሚ በነፍስ ወከፍ 400 ብር መክፈል ጀምረናል ። ይህን ካላደረግን ደግሞ ዩኒፎርም አይለብሱልንም፤ በአንድ ስራ ብቻ ለጓንት (ግላቭ) እና ሳኒታይዘር እስከ 300 ብር ልናወጣ እንችላለን።
በተጨማሪም በፊት 1 ብር የሚገዛዉ አበባ አሁን ላይ ወደ 4 ብር ከፍ ማለቱን ገልፀዉ፣ ለቀብር አስፈፃሚዎችም ከ350-2000 ብር የሚደርስ የጉንጉን አበባ እና አንደኛ ደረጃ ትራንስፖርት አገልግሎትም 1200- 1500 ብር ድረስ ከእድሮች ጋር ጭምር በትብብር እንደሚሰሩ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የቤተሰብ ቀብር አስፈፃሚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዳንኤል ከበደ አስታዉቀዋል። ከቀብር ቦታ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የተለያዩ የእምነት ተቋማት አስተዳዳሪዎች እንደገለፀት፣ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የመሬት ላይ ቀብር እንደሌላቸዉ እና በተለምዶ ፉካ በመባል የሚታወቁት በማህበር የሚሰሩ የቀብር ቤቶች(ኪስ) ብቻ ያላቸዉ እና የደብሩ( የአካባቢዉን) ሰዉ ብቻ የሚያስተናግዱም መሆናቸዉን አዲስ ማለዳ በቦታዉ በመገኘት ካሰባሰበችው መረጃ ለመረዳት ችላለች።
የመሬት ቀብር በሌለባቸዉ ቤተ እምነቶች አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችም እንደገለፁት ፉካዉ ከ30- 80 ሺህ ብር የሚደርስ ዋጋ መጠየቁ ብቻ ሳይሆን የተገነቡት የማህበር ቀብር ቤቶች (ፉካዎች) እጥረት እንዳለም አስታዉቀዋል። የመሬት ላይ የመቃብር ቦታዎች እየተጣበቡ መምጣታቸዉ እና ያሉትም ቦታዎች ላይ ቀብር ለመፈጸም ሲሄዱ የቦታ መጣበብ እና የዋጋ ዉድነት መኖሩ ተገልፃል። ይህንንን በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የሰሚት ምስራቅ ፀሀይ ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅድስት አርሴማ ዋና አስተዳዳሪ መላእከ ሰላም ቀሲስ ተክሌ ግዛቸዉ የእምነት ተቋማት አገልግሎት ሰጪ እንደመሆናቸዉ ለቀብር ቦታዉ እንደማያስከፍሉ፣ ነገር ግን የቀብር ቦታዎችን ሰርተዉ ከሚያስረክቡ ኮንትራክተሮች ጋር ዉል እንደሚፈፅሙ ገልፀዋል። ኮንትራት ከእምነት ተቋማቱ ጋር ወስደዉ የሚሰሩ ኮንትራክተሮች ደግሞ የሚያስከፍሉት ለሚያወጧቸዉ የማስቆፈሪያ፣ የእምነበረድ፣ የሲምንቶ ፣ የብረት እና የመሳሰሉት ወጪዎች መሆኑን አስታዉቀዋል ። ለነዚህም ክፍያ በተለያዩ የእምነት ተቋማት የዋጋ ልዩነት እንዳለ ገልፀዉ፡፡ በእነሱ ግቢ ኮንትራክተሮቹ ከ10,000 እስከ 70,000 ድረስ ሀዉልት ለማሰራት እንደሚጠይቁና ከዚህ ዉስጥም የእምነት ተቋሙ ከኮንትራክተሮቹ 50% ገቢ እንደሚያገኝ ገልፀዋል። ይህ ነገር የሕብረተሰቡን ችግር ባገናዘበ መልክ ለመቅረፍም ሰበካ ጉባኤዉ እየተወያየበትና ሕብረተሰቡንም ለማወያየት እና የአስተያየት መስጫም ለማዘጋጀት በዕቅድ ላይ መሆናቸዉን ነግረውናል፡፡ ከወጪውም ጋር በተያያዘ በደብሩ የሚኖረዉ ማኀበረሰብ የተለያዩ የቅሬታ ሃሳብ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።
አያይዘዉም ቤተክርስቲያኗ ከዚህ በፊት ለደብሩ ኗሪ ብቻ የቀብር ቦታ የምትፈቅድ የነበረ ቢሆንም አሁን በተከሰተዉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ህይዎታቸውን ላጡና ለተቸገሩ ከደብሩ ዉጭ ለሚኖሩም የሕብረተሰብ ክፍሎች የቀብር ቦታ መፈቀዱን ገልፀዋል።
መላእከ ሰላም ቀሲስ ተክሌ ከዚህ በፊት በነበሩበት የኮልፌ ተክለሐይማኖት ደብር ከ3,000- 17,000 የሚደርስ ብር ለቀብር ቦታዎች ዝግጅት ኮንትራክተሮች ከወጪዎቻቸዉ አንፃር አስልተው እንደሚያስከፍሉም አስታዉሰዋል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ ከቤተ እምነቶች ጋር ኮንትራት በመዉሰድ የሚሰሩ የኮንትራክተር ኃላፊዎች እንደገለጹት የሚያስከፍሉት ክፍያ ለቦታዉ ሳይሆን መሬቱን ከእምነት ተቋማቱ ወስደው የመቃብር ቦታዎቹን በሚሰሩበት ወቅት ለሰራተኛ፣ ለሲሚንቶ፣ ለቫዞላ፣ እምነበረድ፣ ብረት እና ለመሳሰሉት ለሚያወጡ ወጪ መሆኑን ገልጸው፣ የነዚህ ወጪዎች ከጊዜ ወደጊዜ መናር ደግሞ የቀብር ቦታ ስራ(ሐዉልት) ውድ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
ይህም እንዳለ ሆኖ አቅም ለሌላቸዉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የቆፋሪ ብቻ 500 ብር እንዲከፍሉ እንደሚያደርጉና አልፎ አልፎ እንደሚተባበሩ ጠቁመዋል። ስራዉ ከባድና የሰብአዊነት ከመሆኑ አንፃር ብዙ ለማትረፍ የሚሰራ ስራ አይደለም ሲሉ ከየተቋማቱ ኮንትራት ወስደዉ የሚሰሩ ኮንትራክተሮች ተናግረዋል። የቀብር ቦታዎች ማሰሪያ ወጪ መናር በተጠቀሱት ችግሮች የመጣ መሆኑን ገልፀዉ፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ የእምነት ተቋማትና ኮንትራክተሮች በጋራ በመናበብ የሕብረተሰቡን ሁኔታ ባማከለ መንገድ ችግሮቹን መፍታት እንደሚገባቸው መላእከ ሰላም ቀሲስ ተክሌ ግዛቸዉ በተቋሙ ግቢ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አስታዉቀዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



