ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ላይ ያቀረበችው ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ምላሽ ማግኘቱ ተገለጸ

0
692

በሱዳን ላይ እንደየሁኔታው አስፈላጊ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ስታነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ ማግኘታቸውን አስታወቀ። ሱዳን ካነሳቻቸው እና በኢትዮጵያ በኩል የስምምነት ምላሽ የተሰጣቸው ጥያቄዎች የግድቡን አሞላል፣ መረጃ፣ የግድቡን ደኅንነትና በአጠቃላይ የአሞላል አስተዳደሩን በሚመለከት ሙሉ ምላሽ አግኝታለች ተብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን ያነሳቻቸው ጥያቄዎች በስምምነት የተመለሱ መሆናቸውን አመላክቷል። ኢትዮጵያ ሱዳንን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትና በሕዳሴው ግድብ ላይ የምታነሳቸው ጥያቄዎች በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በመልካም ስምምነት ምላሽ እንዳገኙ ቢገለጽም፣ በአሁኑ ጊዜ የሱዳንን ሕዝብ ጥቅም ለማስከብር ሳይሆን የሌሎችን ፍላጎት ለማሳካት ሱዳን ኢትዮጵያን እየተነኮሰች ነው ተብሏል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ ጋር ባለመስማማታቸው ለዓመታት ሳይፈታ የቆየ ውዝግብ ቢኖርም፣ ሱዳን የጠየቀቻቸው ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ሱዳን በህዳሴው ግድብ ላይ ያነሳቻቸው ጥያቄዎች ምላሽ ቢያገኙም፣ ሱዳን የኢትዮጵያን መልካም ምላሽና ጉርብትና ዘንግታ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እየተጋፋች መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚያዚያ 26/2013 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰበብ የኢትዮጵያ ድንበር ጥሳ በመግባት ኢትዮጵያን ሊዓላዊነት እየተጋፋች መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና፣ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ በትዕግስት ያስተናገደችው ለሰላም ካላት ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገው ትንኮሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን የጠቀሱት አምባሳደሩ፣ ትዕግስትም ገደብ አለው ብለዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል የሚደርስባትን የሉዓላዊነት ትንኮሳ ለመመከት እንደየ አስፈላጊነቱ እርምጃ እንደምትወስድ ተገልጿል።
ሱዳን ከሰሞኑ ባወጠችው መግለጫ የኢትዮጵያ ግዛት የሆነውን ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የኔ ነው ማለቷ የሚታወስ ነው። ሱዳን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግዛቴ አካል ነው ማለቷ የአገሪቱን አስነዋሪ ተግባር የሚገልፅ ነው ስትል ኢትዮጵያ ኮንናለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የሱዳን መንግስት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ጋር ተያይዞ እያራገበ ያለው ሀሳብ መሠረተ ቢስ ነው ብሏል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡትጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንዳሉት የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ድንበር መጣሱና ዜጎችን ማፈናቀሉ ሳያንሰው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኔ ግዛቴ ነው ማለቱ አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳንን መንግስት ወቅታዊ አካሄድ እንደምትኮንንና የዓለም አቀፋ ማኅበረሰብም ካርቱም ላይ ጫና እንዲፈጥር ትጠይቃለች ብለዋል አምባሳደር ዲና። ሱዳን በውጭ ጉዳይና በውሃ ሚኒስትሮቿ በኩል ከሰሞኑ እየነዛች ያለው የተሳሳተ መረጃም ፍፁም ተቀባይነት የሌለው እንደሆነም ገልጸዋል። የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ሲገባና አርሶ አደሮችን ሲያፈናቅል የኢትዮጵያ መንግስት የሃይልን አማራጭ ያልተከተለው ችግሩ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል የሚል እምነት ስለነበረው እንደሆነም ተነስቷል።

ይሁን እንጂ ይህ አልበቃ ያለው የሱዳን መንግስት የቤንሻንጉል ክልል ግዛቴ ነው ማለቱ፣ እንዲሁም ግድቡን ከድንበር ጉዳይ ጋር እያገናኘ አሳሳች መረጃዎችን ማቅረቡን ቀጥሏል ብለዋል አምባሳደር ዲና። ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት በአስነዋሪ ተግባር እንደሚፈርጀውና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በይፋ እንደሚያሳውቅ ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል። ሱዳን “የቤንሻንጉል ጉሙዝ መሬት የእኔ ነው” ማለቷ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር መሆኑን በማውሳት፣ በዚህ ሁሉ ትንኮሳ ውስጥ ኢትዮጵያ እስከ አሁን ያሳየችው ትዕግስት ለጎረቤት አገራትና ሕዝቦች ያላትን ክብር የሚያሳይ መሆኑም ተነግሯል።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here