ስድስተኛውን አገር ዐቀፍ ምርጫ ለማካሄድ በአዲስ አበባና በድሬድዋ ከተማ አስተዳደር የድምጽ መስጫ ቀን ወደ አገራዊ ድምጽ መስጫ ቀን እንዲመለስ ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ጥያቄ አቀረቡ። በኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገር ዐቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፣ አገራዊ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 28/2013 ሲሆን፣ የአዲስ አበባና የድሬድዋ ከተማ አስተዳደር የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 5/2013 መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጅ ምርጫ በኹለት የተለያየ ቀን መደረግ የለበትም የሚል ጥያቄ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ተነስቷል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ የአዲስ አበባና ድሬድዋ ከተማ አስተዳደር የድምጽ መስጫ ቀን አንድላይ እንዲሆን ፓርቲዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን በደብዳቤ እንዲያቀርቡና ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ባቀረቡት ሀሳብ መሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ(ባልደራስ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ(ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የፓርቲዎችን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የቦርዱ ሰብሳቢ ባቀረቡት ሀሳብ ጥያቄያቸውን በደብዳቤ ከገለጹት ፓርቲዎች መካከል ባልደራስ፣ እናት ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ይገኙበታል።
ፓርቲዎች ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ያገኛል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ የባልደራሱ የህዝብ ግንኙት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። ኃላፊው እንዳሉት ከሆነ ፓርቲዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝና የአዲስ አበባና የድሬድዋ ከተማ አስተዳደር የደምጽ መስጫ ቀን ከአገር አቀፍ የደምጽ መስጫ ቀን ጋር ግንቦት 28/2013 እንድካሄድ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሹ “ተስፋ ያለው ይመስላል” ብለዋል። የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ድምጽ መስጫ ቀን ላይ ፓርቲዎች ለቦርዱ ላቀረቡት ጥያቄ የቦርዱን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን በቃሉ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ እና ድሬድዋ አስተዳድሮች ድምጽ መስጫ ቀንን በተመለከተ ባልደራስ ገና ከጅምሩ ሲቃወምና ሲከራከር እንደነበር በቃሉ አስታውሰዋል። ባልደራስ “በተለይ በኹለት ዋነኛ ምክንያቶች የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ አስተዳደሮች ድምጽ መስጫ ቀን ከፌደራል ድምጽ መስጫ ቀን የተለየ እንዲሆን መደረጉ (ማለትም ከግንቦት 28 /2013 ወደ ሰኔ 5/2013 እንዲዛወር መደረጉ) የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ሕዝቡ ነፃ ፍላጎቱን ያለ ተፅዕኖ እንዲገልፅ የሚያደርግ አይደለም።” ማለቱ የሚታወስ ነው። በአንድ አገር ውስጥ የሚደረግ ተመሳሳይ ምርጫ በተለያየ ጊዜ መደረጉ ትክክል ያልሆነ እና የምርጫወን ተዓማኒነትና ፍትሐዊነት የሚያጓድል እንደሆነም ነው በቃሉ የጠቆሙት።
የ2013 አገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ድምጽ መስጫ ቀን በአንድ ቀን አለመሆኑ በምርጫ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ከገለጹትና ከተቃወሙት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ(ባልደራስ)፣ እናት ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ይገኙበታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄውን በደብዳቤ ማስገባታቸውን በማመን፣ ቦርዱ በደብዳቤ የቀረበለትን አዲስ አበባና የደሬድዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫን ወደ ግንቦት 28/2013 ይመለስ አይመለስ የሚለውን ውሳኔ አሁን ላይ እንዳልወሰነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረበለትን የአዲስ አበባና ድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫ ከሰኔ 5 እና 6/2013 አገራዊ ምርጫ ወደ ሚካሄድበት ግንቦት 28/2013 ይቀልበስ ወይስ እንዳለ ይቀጥል የሚለውን ውሳኔ እንደሚሰጥበት ገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



