በትግራይ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የተረጋጋ ሕዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
አብርሃም እንዳስታወቁት፣ በአገራችን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ጀምሮ በተከሰተው ግጭት መነሻነት በተፈጠሩት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በወገኖች ላይ የደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳት ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፣ መፈናቀሎች ፣ ጥልቅ የስነ ልቡና ጉዳቶች ፣ የንብረት ዘረፋ፣ መጥፋትና ውድመት፣ አላስፈላጊ መገፋፋትና የተካረሩ አመለካከቶች በአጠቃላይም ውጥረት በሕዝቦች ዘላቂ ትብብር፣ በሰላምና መረጋጋት የመኖር ፍላጎት ላይ የተጋረጠውን ጉልህ አደጋ በተመለከተ በግልጽ በመተማመን ተገቢውን ፍትህ መስጠት እንደሚያስፈልግ አብርሃም ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ በተለይም ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና መፍትሔን በመፈለግ ሂደት የችግሮችን ስሪተ ነገር የመረዳት፣ የተያያዥ መሰረታዊ ጉዳዮችን ተጽዕኖ መለየትና፣ ከሙሉ ስዕል እይታ ያልጎደሉ ደረጃ በደረጃ የሚተገበሩ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማፍለቅና በሕዝባዊ ይሁንታ፣ ርብርብና በድፍረት በተግባር የመፈፀም ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ እንደሆነ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013


