መደበኛ ፓስፖርት የሚሰጥበት ጊዜ መራዘሙ ቅሬታ አስነሳ

0
1119

በኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በኩል መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት ከወራት በላይ እንደሚጠብቁ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሙጂብ ጀማል ቅሬታው ተገቢ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ለመራዘሙ ግን ኤጀንሲው በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት እንደሆነ ገልጸዋል። የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም ይፋ እንዳደረገው መደበኛውን ፓስፖርት ለማግኘት ከ75 ቀናት ወደ 30 ቀናት ማውረዱን ቢናገርም በአሁኑ ወቅት መደበኛውን ፓስፖርት ለማግኘት ወራቶች እየወሰደ ያለው የተገልጋዩ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ነው ሲሉ ሙጂብ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ከዘንድሮ ጥቅምት ወር ጀምሮ ለተጠቃሚዎች በድረ-ገጽ አማካይነት አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት እና ለማደስ ቀጠሮ ማስያዝ የሚያስችል ስርዓት ይፋ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል። ይህንንም ተከትሎ ኤጀንሲው በቀን ውስጥ በአካል ያስተናግድ ከነበረው ከ800 እስከ 1000 የሚደርስ የደንበኞች ቁጥር ወደ 4000 እና 5000 እንዲያድግ አድርጎታል። በዚህም በወር እስከ መቶ ሺ ደንበኞችን እንድናስተናግድ ተገደናል ሲሉ ሙጂብ ነግረውናል። ሙጂብ አክለውም ማንኛውም ግለሰብ ባለበት ቦታ እና ሁኔታ በቀላሉ በኦንላይን ለመመዝገብ መቻሉ የአገልግሎት ፈላጊውን ቁጥር ከፍ አድርጎታል ብለዋል።

ይህን ከፍተኛ ቁጥር ደግሞ ኤጀንሲው ባሉት ውስን መስሪያ ቤቶች፣ የአገልግሎት መተግበሪያ እቃዎች እና የሰው ሀይል አቅም ለማስተናገድ አለመቻሉ የቀጠሮው ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት ሁኗል ብለዋል። ተቋማችን ያለበትን ውስንነት በመቅረፍ መስራት እንዳለበት የሚታወቅ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ተገልጋዮች በትዕግስት በመጠባበቅ በቀጠሮአቸው ቀን መገልገል እንደሚችሉ ሙጂብ ጠቁመዋል። በሁለተኛ ደረጃ የመዝግየቱ ችግር የሆነው ተመዝጋቢዎች ካመለከቱ በኋላ ክፍያ ያለመፈጸም እንደሆነ ሙጂብ አንስተዋል። ኤጀንሲው አንድ ግለሰብ ከተመዘገበ በኋላ እስከ አምስት ቀን ድረስ በባንክ ክፍያ መፈጸም ይኖርበታል።

ሌላኛው ሙጂብ እንደ ችግር የጠቀሱት የኦንላይን ምዝገባው በክልሎችም ላይ ተግባራዊ በመሆኑ ክልል ላይ ያሉት ተገልጋዮች አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልጉት አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ ቁጥሩን በእጅጉ ጨምሮታል። ኤጀንሲው ፓስፖርት ለማግኘት መደበኛውን የወረፋ ግዜ ሳይጠበቁ እንዲስተናገዱ እና ከተቀመጠው ግዜ አስቀድሞ በአፋጣኝ አገልግሎት ለሚፈልጉ፣ አስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት የተገደዱበትን ምክንያት እንዲያቀርቡ አሰራር እንዳለው በድህረ ገፁ ላይ ይጠቅሳል። ለአስቸኳይ ህክምና፣ የትምህርት እድል ለሚያገኙ አመልካቾች፣ እንዲሁም የዲቪ ሎተሪ እድለኞች ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ አሰራር እንዳለው ያስቀምጣል። የውጪ ሀገር የመኖሪያ ፈቃድ እንዲሁም ከተፈቀደለት ተቋም የሚፃፍ የድጋፍ ደብዳቤ አስቸኳይ ፓስፖርት ለማውጣት የሚያስችሉ ማስረጃዎች ሆነው ተገልፀዋል።

ፓስፖርትን በአስቸኳይ ለማውጣት ተያይዘው የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ማግኘት ያልቻሉ እና በተለያየ ምክንያት ፓስፖርትን በፍጥነት ለማውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች በደላላ በኩል የሚከፍሉት ክፍያ መኖሩን ሙጂብ አረጋግጠዋል። ነገር ግን ይህ ከመስሪያ ቤቱ ውጪ ከመሆኑም በላይ ህገወጥ ተግባር ስለሆነ ኤጀንሲያችን ሕብረተሰቡን የመጠበቅ ስራ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየሰራ እንደሚገኝ ሙጂብ ነግረውናል። ተገልጋዮች በቀጥታ የመስሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋ በመሄድ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በውጭ ባሉ ደላሎች በአቋራጭ ለመጨረስ የሚያደርጉት ጥረት ያለ ሲሆን፣ ለእንደዚህ አይነት ወንጀል እንዳይጋለጡ መስሪያ ቤታችን በር ላይ ተጠንቀቁ የሚል መልዕክት በሬዲዮ እያስተላለፉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እንዲህ አይነቱን ችግር በቀላሉ እንደማይመለከተውና በማስረጃ ከቀረበለት እርምጃ እንደሚወስድ ሙጂብ ገልጸዋል። ሕብረተሰቡ ማናቸውንም አገልግሎት ከመስሪያ ቤቱ ውጪ ባሉ ደላሎች ለማስፈፀም እንዳይሞክርና ገንዘብም እንዳይከፍል ኤጀንሲው መክሯል።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here